| ኢንቨስትመንታችን ይቀጥላል፤... |
|
|
| Thursday, 10 January 2008 | |
|
ኢንቨስትመንታችን ይቀጥላል፤ የዓለም ታዋቂ አቀንቃኞችም ይመጣሉ ሼህ መሀመድ አላሙዲ ሼህ መሀመድ ሁሴን አልአሙዲ በኢትዮጵያ የተጀመረው አጠቃላይ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደሚቀጥል አስታወቁ፡፡ በ25 ሚሊዮን ብር የኤርፖርት የምግብ ማዘጋጃና፣ ከ140 ክፍሎች በላይ ያሉት ባለአራት ኮከብ ሆቴል እንደሚያሰሩ ተጠቁሟል፡፡ ባለሀብቱ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ኢንቨስትመንታችን ይቀጥላል ታዋቂ የዓለማችን አቀንቃኞችም የኢትዮጵያን መሬት ይረግጣሉ ሲሉ ተደምጧል፡፡ በአዲስ አበባ ኤርፖርት በመገንባት ላይ የሚገኝ አዲስ ኢንተርናሽናል ኬተሪንግ በመባል የሚታወቅ የምግብ ማዘጋጃ ድርጅት በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መገባደጃ ላይ ሙሉ ግልጋሎት እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡ ንብረትነቱ የሼክ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ የሆነ በ54..000 ካሬ ሜትር ላይ በመገንባት ላይ የሚገኘው ባለሁለት ፎቅ የምግብ ማዘጋጃ ድርጅት፣ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በቀን ለ15 ሺህ የበረራ ተሳፋሪዎች የሚሆን ምግብ የማዘጋጀት አቅም እንደሚኖረው ታውቋል፡፡
ድርጅቱ አምስት ያህል አዲስ አበባ ኤርፖርትን የሚጠቅሙ ታላላቅ አየር መንገዶችን ለማገልገል ያነጋገረ ሲሆን አብረውት ለመሥራት የፈቃደኝነት ተስፋ እንደሰጡትም እነዚሁ የድርጅቱ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልፀዋል፡፡ ከምግብ ማዘጋጀት ባሻገርም ለአየር መንገዶች፣ የፅዳት፣ የልብስ እጥበት፣ እንዲሁም ከመደበኛ በረራ ውጭ የሚኖሩ ትዕዛዞችንም ይቀበላል፡፡ በአሁኑ ሰዓት አዲስ ኢንተርናሽናል ኬተሪንግን በመምራት ላይ የሚገኙት ሃሚሽ ሌዲንግሀም ከዚህ በፊት በመስተንግዶና በምግብ ማዘጋጀት ዘርፎች ከ30 ዓመት በላይ ልምድ ያካበቱ ሲሆኑ ካገለገሉባቸውም ቦታዎች መካከል ባሃሬይን አየር መንገድ፣ ገልፍ ኤር ይገኙበታል፡፡ አዲስ ኢንተርናሽናል ኬተሪንግ፣ ከግንባታው ጀምሮ የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎችና የሚኖሩት ባለሙያዎች በአፍሪካ ውስጥ የላቀ ቦታ የሚያሰጠው፡፡ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ምንጮች እንዳስታወቁት አዲሱ የሚሌኒየም አዳራሽ ባለበት ቦታ ላይ 144 ክፍሎች ያሉት ባለአራት ኮከብ ሆቴል ይገነባሉ፡፡ የሆቴል ግንባታውን ለመጀመር የዲዛይን ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሌላ ዜና በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ ዝግጅታቸውን እንዲያቀርቡ የመጡት ኤኮንና ሪሃና ከአገራችን ታዋቂ አርቲስቶች ጋር ዝግጅታቸውን በሚሌኒየም አዳራሽ አቅርበዋል፡፡ ሰኞ ምሽት ታህሳስ 21 ቀን 2000 ዓ.ም እስከ ሌሊቱ አስር ሠዓት ድረስ በቆየው በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት ወጣቷ አቀንቃኝ በሴኔጋላዊው ድምፃዊ ኤኮን ተውጣለች፡፡ ምንም ተወዳጅ ዘፈኖቿን በሚያምር ቅላፄዋ ብታቀርብም ኤኮን በመድረክ ላይ ባሳየው ብቃት አደብዝዟታል፡፡ ታዳሚው ዘንድ በመውረድ ሕዝቡ መሃል ቢቀላቀልም የደህንነት ሰዎች ወደ መድረኩ እንዲመለስ አድርገውታል፡፡ እባካችሁ የሰለጠኑ ታዳሚዎች ናቸው በማለት የተናገረው ኤኮን በዘፈኑ መሃል 5 ወጣት ሴቶችን ወደ መድረክ ጋብዞ አስደንሷል፣ አወዳድሯል፡፡ ባደረገው ውድድር አሸናፊዋን የአፍሪካ ንግሥት በሚል ተምሳሌት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ምልክት መሆኗን ጠቁሟል፡፡ በዕለቱ ጥላሁን ገሠሠ በዊልቸር በመውጣት ሁሉንም ለይቼ አይቼዋለሁን ጨምሮ ተወዳጅ ዘፈኖቹን በማቅረብ ታዳሚውን አስደምሟል፡፡ በአብርሃም ገ/መድህን ሀገሬ ዜማ የተከፈተው ኮንሠርት ላይ እነአሊቢራ፣ ህብስት ጥሩነህ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ፀጋዬ ስሜና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡ ሙሉ ዝርዝሩን በኪንና ባህል አምድ ይመልከቱ፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |