| በአዲስ አበባ የክ/ከተማና የቀበሌ... |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
|
በአዲስ አበባ የክ/ከተማና የቀበሌ አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቅሬታ ተነሳ በተሾመ ንቁ በአዲስ አበባ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አስተዳደሮች ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት አቁመዋል ሲሉ ነዋሪዎች አማረሩ፡፡ የአዲስ አበባ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር በሚያዚያ ምርጫው ያሸነፈ አካል ስልጣን እስኪረከብ በአንዳንድ መስኮች ላይ ብቻ አገልግሎት ማቆሙን አስታወቀ፡፡
የክፍለ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በቀበሌ አስተዳደሮች የሚሰጡ አገልግሎቶች ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ መቋረጣቸውን በመጥቀስ አንዳንድ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለሪፖርተር አቀረቡ፡፡ የመስተዳድሩ አካላት “በሚያዚያ ምርጫ ያሸነፈው አካል ስልጣን እስኪረከብ አገልግሎት ተቋርጧል” የሚል ምላሸ እንደተሰጣቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡ በዚህም ከቀበሌና ከክፍለ ከተማ መስተዳድር ማግኘት የሚገባቸውን መሰረታዊ አገልግሎቶች ማጣታቸውን ገልፀዋል፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ፣ አጥር ማሳጠር፣ ቤት ማሳደስ፣ የፍሳሽ መስመሮችን መጠገን፡ የልደት ካርድ፣ የቅጥር ፎርማሊቲ፣ የመሳሰሉ ጉዳዮችን ለማከናወን ከመስተዳድሩ አካላት ፈቃድ መነፈጋቸውን ገልፀዋል፡፡ ተገልጋይ ነዋሪዎች፤ በምርጫው አሸንፎ ስልጣን የሚረከበው አካል እስኪመጣ አገልግሎት መቋረጡ አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ “ቅሬታችንን የሚሰማን አካል አጥተናል” ሲሉ አማርረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ጊዜያዊ የባለአደራ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ውብሸት ብርሃኑ “በምርጫ አሸንፎ ወደ ስልጣን የሚመጣው አካል ኃላፊነቱን እስኪረከብ ድረስ ከመጋቢት 21 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ገደብ ተደርጓል” ብለዋል፡፡ ይህም የተደረገው በሽግግር ጊዜ ውስጥ አላስፈላጊ ስህተት እንዳይከሰት ጥንቃቄ ከማድረግ አኳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ውብሸት ከመጪው የአስተዳደር አካል ጋር የሥራ ርክክብ እስከደረግ ድረስ ከመሬት ይዞታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ ከመሬት የሊዝ ሽያጭ የጨረታ ድርድርና የአዲስ ቅጥር እንዲሁም ሹመት የማይከናወኑ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡ ይህም ኅብረተሰቡ የተዛባ አገልግሎት አግኝቶ በርክክብና በሽግግር ወቅት ችግር ውስጥ እንዳይገባ ከማሰብ አንፃር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ እገዳው እስከመቼ እንደሚቆይ ቁርጥ ያለ የጊዜ ገደብ ባይቀመጥለትም ርክክብ እስኪደረግ የሚፀና መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከተጠቀሱት ውጪ ያለ አገልግሎት ባለበት እንዲቀጥል መደረጉን ዶ/ር ውብሸት አረጋግጠዋል፡፡ በዚህም የእድሳት ፈቃድ፣ የግንባታ ፈቃድ፣ የሽያጭ አጣሪ ፈቃድ፣ የልደት፣ የጋብቻ የመሳሰሉ አገልግሎቶች አለመቆማቸውን በመግለጽ የቀረበውን የቅሬታ አቤቱታ አስተባብለዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |