Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow በሶማሊያ የቦምብ ጥቃት ሰለባ...
በሶማሊያ የቦምብ ጥቃት ሰለባ... Print E-mail
Sunday, 04 May 2008
በሶማሊያ የቦምብ ጥቃት ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቀሉ

በኃይሌ ሙሉ

በሶማሊያ የወደብ ከተማ ቦሳሶ የቦምብ ጥቃት ሰለባ የሆኑት 33 ኢትዮጵያውያኖች ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን የአለማዐቀፉ ማይግሬሽን ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) ምንጮች ገለጹ፡፡
ከሁለት ወር በፊት ከቦሳሶ ተነስተው በሕገወጥ ጀልባ ወደየመን ለመጓዝ ሲሞክሩ የቦምብ ጥቃት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያኑ በአይ.ኦ.ኤም ሰራተኞች ታጅበው ወደ ድሬዳዋ የተመለሱት በመጋቢት ወር ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት በቅተዋል፡፡

በወቅቱ ከአይ.ኦ.ኤም የተሰጠው መግለጫ እንደሚያመለክተው ፌብሩዋሪ 6/2008 በስደተኞቹ ላይ በተፈፀመው የቦምብ ጥቃት 22 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ 74 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ በጥቃቱ የተገደሉትና የቆሰሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

ከቆሰሉት 33 ሰዎች መካከል 21 ያህሉ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ያስፈልጋቸው ስለነበረ ወደ ድሬዳዋ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ የቦምብ ጥቃት ሰለባዎቹ ቦሳሶ በሚገኘው ሆስፒታል ህክምና የተደረገላቸው ቢሆንም ሆስፒታሉ በመሳሪያ የተደራጀ ባለመሆኑ ቁስለኞች ለኢንፌክሽን ተዳርገዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ነው ወደ ድሬዳዋ የተጓጓዙት፡፡

ከደቡብ ምዕራብና ከሰሜን ኢትዮጵያ የመጡት የአደጋው ተጠቂዎች ከአንዷ በስተቀር ሁሉም ወንዶች ናቸው፡፡ ተጎጂዎቹ የመጡበት አካባቢ ሩቅ በመሆኑና የአካባቢያቸው የግንኙነት መረብም ደካማ በመሆኑ ቤተሰቦቻቸውን ፈልጎ ለማግኘት አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ከአይ.ኦ.ኤም የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡

ቦሳሶ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን የተሻለ የስራ እድል ፍለጋ በሕገወጥ መንገድ ወደ የመንና ከዚያም አልፎ ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት የሚሸጋገሩባት የሶማሊያ የወደብ ከተማ ናት፡፡ በኤደን የባህር ሰርጥ የሚደረገው ጉዞ በጣም አደገኛ ነው፡፡ የዩ ኤን ኤች ሲ አር ጥናት እንደሚመለክተው እ.ኤ.አ በ2007 ብቻ 1400 ስደተኞች በባህር ጉዞ ላይ እንዳሉ ሞተዋል ወይም የደረሱበት አልታወቀም፡፡

በኢትዮጵያውያንና በሶማሊያውያን ስደተኞች ላይ የቦምብ ጥቃት ከደረሰ በኋላ እንኳን በርካታ ኢትዮጵያውያን እዚያው ቦሳሶ በመቅረት ወደ የመን ለመጓዝ ሲዘጋጁ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ያለው የአየር ጸባይ ትናንሽ ጀልባዎችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ቢሆንም የኢትዮጵያኖቹን ስደተኞች ሀሳብ የሚያስቀይር አልሆነም፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ 26..000 ስደተኞች የኤደን ባህርን አቋርጠው በጀልባ ወደ የመን የተጓዙ ሲሆን በዚህ አሰቃቂ የባህር ጉዞ 404 ሰዎች ሞተዋል፤ 393 ደግሞ የደረሱበት አይታወቅም፡፡

ከአይ.ኦ.ኤም የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው እያንዳንዱ ተጓዥ ለሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ከ60-100 ዶላር ይከፍላል፡፡ ስደተኞቹ በጉዞ ላይ ይደባደባሉ፣ በጩቤ ይወጋሉ ከዚያም አልፎ ወደ ባህር ይጣላሉ፡፡ በትናንሾቹ ጀልባዎች የሚጓዙት ሰዎች በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ በመተፋፈግና በውሃ እጥረት ብዙ ሰዎች በመንገድ ላይ ይሞታሉ፡፡ ብዙዎቹ ተጓዦች በጉዞ ላይ ስለሚያጋጥማቸው ችግር የሚውቁት ነገር የለም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በችግር ከመኖር መሞት ይሻላል በማለት አሰቃቂውን ጉዞ ከማድረግ እንደማይመለሱ ይናገራሉ፡፡

ከሚያቃጥለው ሀሩር በተጨማሪ ውሃ ጥሙ፣ ረሀቡ በሽፍታዎች የሚፈፀምባቸው የተለያዩ ጥቃት ስደተኞቹን ለአካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የሚዳርግ ሆኗል፡፡
 
< Prev   Next >