| ፕ/ር መስፍን በወሬ እንጂ፣... |
|
| Thursday, 10 January 2008 | |
|
ፕ/ር መስፍን በወሬ እንጂ፣ ሰርተው ውጤት በማምጣት የሚታወቁ አይደሉም የኢ/ር ኃይሉ ሻወል ተወካይ በኢንጂነር ኃይሉ ምትክ የቅንጅት ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲሰሩ የተሾሙት አቶ አባይነህ ብርሃኑ፣ ፕሮፌሰር መስፍን የወሬ ሰው እንጂ የተግባር ሰው አይደሉም በማለት ነቅፈዋቸዋል፡፡ የፕሮፌሰሩ በቅንጅት ውስጥ መኖርም አለመኖርም ምንም ለውጥ እንደማይኖረው ገልፀዋል፡፡ የቅንጅት ህጋዊ ሰውነት ለአቶ አየለ ጫሚሶ የሚሰጥ ከሆነ ጠቅላላ ጉባኤው አዲስ ስም ያወጣል እንጂ ከእነሱ ጋር አብረው መሥራት እንደማይችሉ አቶ አባይነህ ገልፀዋል፡፡ የቅንጅት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ኃይሉን ተክተው በቅርቡ የተሾሙት አቶ አባይነህ ብርሃኑ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ ፕሮፌሰር መስፍን ከፓርቲው ውጭ በህገ ወጥ መንገድ እየተሰባሰቡ የሚንቀሳቀሱ ያሉዋቸውን እነ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን መደገፋቸውን በመቃወም እሳቸው ረፕሮፌሰሩሪ አንዱን ወገን ስለደገፉና ሌላውን ስላልደገፉ የሚመጣ ለውጥ የለም ብለዋል፡፡ ለውጥ ማምጣት የሚችለው ፓርቲው ብቻ ነው ያሉት አቶ አባይነህ፣ ለጋዜጣ ፍጆታ ከሆነ ጋዜጦቹ በመጠቀም አፈነዳለሁ፣ እንዲህ አደርጋለሁ፣ ሚስጢር አለኝ አወጣዋለሁ.. እያሉ የሚያወሩትም ሆነ የሚያውቁት ምስጢር የላቸውም እንጂ እስከ አሁን ያወጡት ነበር በማለት እየፈፀሙ ያሉትን ተግባር ኮንነዋል፡፡ ለፕሮፌሰር መስፍን ተብሎ የሚሰራ ነገር አይኖርም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሆነውን ያልሆነው በማውራት የሚደሰቱ ከሆነ ማውራት ይችላሉ፡፡ ግን በፓርቲው ላይ ቅንጣት ያህል ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ሰው አይደሉም በማለት ለሚደግፏቸው ለእነ ብርቱካን ቅንጅትም የሚያስገኙላቸው ጥቅም እንደሌለ አቶ አባይነህ ገልፀዋል፡፡ እነ ኢ/ር ኃይሉን በመስደብ የሚያጠፉት ጊዜ በእነሱ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይኖረው አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ እሳቸው ለሚናገሩት ሁሉ አፀፋ እንስጥ ብንል ሰውም ይታዘበናል፤ እሳቸው ግን መሳደብ ይችላሉ እንጂ በፓርቲው ምንም ለውጥ ማምጣት የሚችሉ አይደሉም ብለዋል አቶ አባይነህ፡፡ በብዙ ሰው ተሰሚነት ያላቸው እንደሆኑና በእነሱ ቡድን ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ካለ ተጠየቀው፣ ፕ/ር መስፍንን አብዛኛው ሰው ያውቃቸዋል፡፡ የፈለጉትን ነገር በመናገር እንጂ ሰርተው ውጤት በማሳየት የሚታወቁበት ነገር የለም፡፡ እውነቱ ይሄ ነው በጥቅሉ አሉ አቶ አባይነህ በጥቅሉ ፕሮፌሰር መስፍን ከኋላ ሆኖ በማውራት እንጂ በሥራ የሚታወቁ አይደሉም ኢሰማጉ በማቋቋም ትልቅ ቦታ ይሰጣቸው እንደሆነ እንጂ በፓርቲው (በቅንጅት) ውስጥ የሚያወሩትን ያህል እዚህ ግባ የሚባል አስተዋፅኦ አለማድረጋቸውንም አቶ አባይነህ ለግንዛቤ በሚል ይፋ አድርገዋል፡፡ በፓርቲው ውስጥ ወሳኝ ሰው መስለው መቅረባቸው አስገራሚ ድራማ ነው፡፡ ፕ/ር መስፍን ቅንጅን ለመሸምገል አግባብ እንዳላቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ከእኛ ጋር በተነጋገሩበት ጊዜ ትክክለኛ አካሄድ መሆኑን አመስግነው እንለያያለን፣ ከወጣን በኋላ ደግሞ ሌላውን ቡድን ትክክለኛ ነህ ሲሉ፣ የእኛን ደግሞ የተለያየ ስም ሲለጣጥፉብን እናያለን በማለት እንደሚገረሙ የገለፁት አቶ አባይነህ፣ ፕ/ሩ የፀና አቋም የሌላቸው መሆናቸውን በመናገር ሽማግሌ መሆን ቀርቶ ሽማግሌ ያለበት ቦታም መቅረብ የማይገባቸው ሰው ናቸው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ለማስታረቅ የማይሆኑ ዘወትር ልዩነት በመፍጠር መልካም ነገር ሳይሰሩ እድሜያቸውን የገፉ ብለዋቸዋል፡፡ እንደ እሳቸው ዓይነት ለአገር ታላቅ ሥራ ከመሥራት ይልቅ በእንደዚህ ዓይነት ትርኪ ምርኪ ተግባር ላይ ማተኮር ጥቅም የለውም፡፡ ይልቁኑ ለአገር የሚበጅ እንደ ሀውልት የሚታይ ሥራ ቢሰሩ መልካም ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የቅንጅት ህጋዊነትንና ስያሜን በተመለከተ እኛ ተዋህደናል፣ ህጋዊ ነን ብለን ነው የምናስበው፤ ምርጫ ቦርድ ግን አራት ፓርቲ ናችሁ የምታውቁት ብሎናል በማለት ስሙንም ለሌላ ሰጥተነዋል ብለው የሚያረጋግጡልን ከሆነ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ የፓርቲው ስም መለወጥ፣ ወይም መከራከር ይችላል ብለዋል፡፡ አቶ አባይነህ ስሙ ለሌላ አካል ተሰጥቷል፡፡ ለእናንተ አይገባችሁም፡፡ ከተባለ ይህንን ለሕዝብ አሳውቀን ስሙም ቢሆን በጠቅላላ ጉባኤ የሚቀየርበት ሁኔታ ይኖራል ካሉ በኋላ፣ ስሙ በሌላ አካል መወሰዱ ስለሚኖረው ተፅዕኖ አስመልክተው ፕሮግራማችን እስካለ ድረስ የስሙ መለወጥ የሕዝብ ድጋፋችንን ይቀንሳል የሚል እምነት የለንም ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ጉዳዩ ከስሙ (ቅንጅት) ጋር አይደለም፡፡ ከተግባሩ ጋር ነው ያለው፣ ይህንን ፕሮግራም የሚያራምዱት የፓርቲው መሪዎች ናቸው ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከፕሮግራሙ ጋር እስካሉ ድረስ ሰዎችም ቢቀየሩ የፓርቲው ስምም ቢቀየር ሕዝቡ እንደሚደግፈው ምንም አንጠራጠርም ብለዋል፡፡ ከአቶ አየለ ጫሚሶ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክተው፣ ጥቂት ወንበሮች ለቅንጅት (ለእኛ) ትችያለሁ ማለታቸውን ሰምተናል፡፡ ይሄ በፍፁም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ የፓርቲያችንን የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ የሚጠይቅ ነው በማለት አቶ አየለ በእኛ ስም የተመረጠ ሰው ነበር፣ አሁን ግን ከቅንጅቱ ፕሮግራም ውጪ የተለየ አቋም ያላቸውና በተቃውሞ የቆሙ ሰው ናቸው ብለዋል፡፡ በመሆኑም በእሳቸው አመራር ስር በመግባት አብሮ ለመሥራት የማይታሰብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በየማነ ናግሽ |
|
| Last Updated ( Thursday, 10 January 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |