| በዱከም ህፃናቶች እንዲያልቁ ምክንያት... |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
|
በዱከም ህፃናቶች እንዲያልቁ ምክንያት ሆኗል የተባለው አሽከርካሪ ተቀጣ
በአዜብ መሐሪ ከቢሾፍቱ ወደ ዱከም ህፃናት ተማሪዎችን ጭና በመሄድ ላይ በነበረችው ታክሲ (ሚኒባስ) ላይ አደጋ ባደረሰው አሽከርካሪ ላይ የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ የ13 ዓመት ከ8 ወራት ፅኑ እሥራትና የ13 ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ሰኔ 6 ቀን 1999 ዓ.ም. ከቢሾፍቱ ደብረዘይት ወደ ዱከም የሚጓዝ የትምህርት ቤት ሰርቪስን (ኮንትራት ሚኒባስ ታክሲ) በመግጨት አደጋውን ያደረሰው ተሽከርካሪ ቦቴ መኪና ታርጋ ቁጥር 3-22957 ኢት እና 3-07921 ኢት መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ በቁጥር 00519/226 ጥቅምት 25/2000 ዓ.ም. በፃፈው ማመልከቻ መሠረት አሽከርካሪው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 543(3)፣ 559(2) እና 856ን በመተላለፍ የቀኝ መሥመሯን ይዛ ትጓዝ የነበረችውን ሚኒባስ ታክሲ 1-00044 ኦሮ በመግጨት ከ12 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት ላይ አደጋ አድርሷል፡፡ በደረሰውም አደጋ ህፃናትን፣ ሹፌሩን፣ ረዳቱንና ሌላ አንዲት ተሳፋሪን ጨምሮ በጠቅላላው 11 ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡ አሽከርካሪው ፍሬኑ የማይሰራ ተሽከርካሪ ኃላፊነት በጐደለው ሁኔታ በፍጥነት በመንዳት በቸልተኝነት ለፈፀመው ወንጀል ፍርድ ቤቱ ተገቢውን ቅጣት እንዲሰጠው አቃቤ ህጉ ጠይቋል፡፡ ተከሳሹ ህዳር 9/2000 ዓ.ም. ባቀረበው መከላከያ መሠረት ታክሲዋ ከሌላ መኪና ተጨማሪ ተደራቢ ሆና ገብታለች ቢልም አቃቤ ህጉ የራሱን ምስክሮችና የቴክኒክ ማስረጃዎችን በማቅረብ መከላከያውን ውድቅ አድርጐታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 142(1) የተሰጠውን ምስክር የማቅረብ መብት በመጠበቅ የምስክሮቹን ቃል ከመቀበሉም በተጨማሪ ከኦሮምያ ፖሊስ ቢሮ የተገኙትን መረጃዎች አገናዝቧል፡፡ በተገኘው የፖሊስ ሪፖርት መሠረት አደጋውን ያደረሰው መኪና የቀኝ መስመሩን ስቶ ወደ ግራ አንድ ሜትር ከ25 ሣንቲ ሜትር ገብቷል፡፡ አቃቤ ህጉም በ1996 ዓ.ም. በወጣው ሕግ አንቀፅ 543(3)፣ 559(2) እና 856 መሠረት አሽከርካሪው ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ፍርድ ቤቱ እንዲቀጣለት ጠይቋል፡፡ የተከሳሽ ጠበቃም በበኩሉ ተከሳሹ ከዚህ በፊት ምንም የጥፋት ሪከርድ የሌለበትና የብዙ ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ከግንዛቤ እንዲያስገባለት ጠይቋል፡፡ በመጨረሻም ዳኛው አቶ አልዩ ሐሰን፣ የፍርድ ቤቱ አቃቤ ሕግ ከሳሽ አቶ ሽመልስ አሰፋ፣ ተከሳሽ አቶ ኤርምያስ ደስታና ሌሎችም የሟች ሕፃናት ቤተሰቦች በተገኙበት ፍርድ ቤቱ መጋቢት 17/2000 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘባቸው ሦስት ክሶች በጥቅሉ 13 ዓመት ከ8 ወር ፅኑ እሥራትና የ13 ሺህ ብር ቅጣት ተወስኖበት ፋይሉ ለመዝገብ ቤት እንዲተላለፍ ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |