| 109 የሕትመት ውጤቶች በሥርጭት ላይ ይገኛሉ |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
|
በጋዜጣው ሪፖርተር
በኢትዮጵያ በ1995 ዓ.ም በወጣው የፕሬስ አዋጅ 34/85 መሠረት በአሁኑ ወቅት 108 ጋዜጦች፣ መፅሔቶችና ዜና አገልግሎት ተቋማት ፈቃድ ወስደው በሥርጭት ላይ እንደሚገኙ ተጠቆመ፡፡ የዓለም የፕሬስ ቀንን ምክንያት በማድረግ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው ከትላንት በስቲያ በግዮን ሆቴል ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ በማኒስቴሩ የሚዲያ ላይዘን ኃላፊ አቶ ፋንታሁን አስረስ እንደተናገሩት የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ በአዋጅ ከተረጋገጠ ከ1995 በኋላ 760 ጋዜጦች፣ 215 መፅሔቶች፣ እና ለሁለት የግል ዜና አገልግሎት በድምሩ ለ997 ተቋማት የሙያ ማረጋገጫ ፈቃድ መስጠቱን ከነዚህ ውስጥ በድምሩ 780 ያህሉ የፕሬስ ውጤቶች ታትመው ለሥርጭት በቅተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 68 የፖለቲካ፣ የስፖርት፣ የኃይማኖት ጋዜጦች፣ 40 መፅሔቶች እና አንድ የግል ዜና አገልግሎት (ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል) በሥራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የጋዜጣና የመፅሔት ቁጥር ለመቀነሱ የሰጡት ምክንያት በራሳቸው የአቅም ችግር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ “በአሁኑ ወቅት ያለው የጋዜጣና መፅሔቶች ቁጥር እያነሰ ነው በማለት አሉታዊ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች አሉ ያሉት አቶ ፋንታሁን በግሌ ግን አሁን ያለው የፕሬስ ሁኔታ ጤናማነት እየታየበት ነው፣ የተሻለ የድርጅት ብቃትና አሠራር ያላቸው ተቋማት እያሸነፉ ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የሕትመት ዋጋ መናርን በሚመለከት አንዳንዶች መንግሥት ሆን ብሎ የግል ፕሬሶችን ለማዳከም ዋጋ የሚጨምር አድርገው የሚያስቡ መኖራቸውን በመጠቆም የሕትመት ዋጋ እየናረ ያለው ግን የወረቀት ጥሬ ዕቃ በዓለም ገበያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ በአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ከምርጫ 97 በኋላ ከ14 በላይ የህትመት ውጤቶች በመንግሥት መታገዳቸው ለጋዜጦች ቁጥር ማነስ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን፣ አሁን በህትመት ላይ ያሉትም ቢሆን ተሸማቀው እንዲሰሩ መገደዳቸውን አመልክተዋል፡፡ አቶ ፋንታሁን ግን በአሁኑ ወቅት ያለት ጋዜጦች በትክክለኛ መስመር ላይ እየተጓዙ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዕለቱ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ፕሬስ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ስለሚያደርገው አስተዋፅኦ የተለያዩ ማኅበራት የውይይት መነሻ ሃሳቦችን አቅርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የጋዜጠኞች ማኅበራት በማስታወቂያ ሚኒስቴር አስተባባሪነት አብረው መሥራት የሚችሉበትና የሚጠናከሩበት መንገድ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገል..ል፡፡ በተጨማሪም በውይይቱ ሴት ጋዜጠኞች በሙያው ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑ፣ የግሉ ፕሬስ ጋዜጠኞች የተጠናከረ ሥልጠና የማያገኙበት ሁኔታ መኖሩ፣ የመንግሥት ተቋማት መረጃ ለመስጠት በራቸውን ሙሉ በሙሉ በሚከፍቱበት ሁኔታ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ተሰንዝረው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |