Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የባንኩ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ...
የባንኩ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ... Print E-mail
Sunday, 04 May 2008
የባንኩ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲከሰሱ ተወሰነ

በጋዜጣው ሪፖርተር

በአዲስ አበባ የሚገኘው የኦሮሚያ የሕብረት ሥራ ባንክ አክሲዮን ማህበር ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በወንጀል እንዲከሰሱ ዐቃቤ ሕግ አዘዘ፡፡
አቶ በላይ ሂርጳ እንዲከሱ የታዘዘው፣ በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅነት በሚሰሩበት የኦሮሚያ የሕብረት ሥራ ባንክ አራት ቢሮዎች ተከፍተው የባንኩን አርማ የያዙ ወረቀቶችና የቀድሞው ዋና ሥራ አስኪያጅ ቲተር በመሰረቃቸውና የቢሮ ማከፋፈያ መስታዎቶች በመሰባበራቸው ድርጊቱን ፈፅመዋል በሚል ጥርጣሬ ነው፡፡

የወንጀል ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ ተጠርጥረው የነበሩት አቶ በላይ ክስ እንዳይመሰርትባቸው ዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡

ባንኩ ጉዳዩ እንደገና እንዲታይለት በጠየቀው መሠረት፣ መረጃዎቹ ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ ናቸው፤ በማለት አቶ በላይ እንዳይከሰሱ ያስተላለፈውን ተዕዛዝ ለውጦ እንዲከሰሱ የፍትህ ሚኒስቴር የወንጀል ጉዳዮች መምሪያ ወስኗል፡፡

የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ዐቃቤ ሕግ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ይኸንን አስመልክተው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን በፃፉት ደብዳቤ በተከሳሹ ላይ ከጥርጣሬ በፀዳ መልኩ የወንጀሉን ድርጊት ስለመፈፀሙ፣ ያልተረጋገጠባቸው ስለሆነ ክስ አናቀርብም፤ ብለው መወሰናቸውን አስታወሰዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ምስክሮች፣ ስርቆት ለመፈፀሙ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ፣ ተከሳሹ በሰጡት ቃል ድርጊቱን አልፈፀምሁም፤ ማለታቸው፣ ቢሮዎቹ የተከፈቱት በኦርጅናል ቁልፎች እንደሆነ መታወቁ፣ ከወንጀሉ ስፍራ የተገኘው አሻራ የአቶ በላይ ሂርጳ የግራ እጅ አሻራ መሆኑ በቂ ማስረጃ ሊሆን ባለመቻሉና የተገኘው የእግር ዱካ ከተከሳሾቹ ጋር አለመመሳሰሉ ከጥርጣሬ የፀዳ የወንጀል ድርጊት ነው ለማለት ባለማስቻሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በባንኩ ማመልከቻ መሠረት በቴክኒክ ማስረጃ እና አካባቢ ማስረጃ ሊረጋገጡ የሚችሉ ወንጀሎች እንዳሉ ገልፆ የተገኘው የአቶ በላይ የእጅ አሻራ በቂ ሊሆን አይችልም፤ መባሉ ከምርመራ ዘዴዎች ጋር ሊጋጭ እንደሚችል ጠቅሷል፡፡ አንዳንድ ወንጀሎች በዓይን ምስክር ማረጋገጥ ሳይቻል በቴክኒክ ማስረጃ እና በአካባቢ ማስረጃ ሊረጋገጡ የሚችሉ የወንጀል አፈፃፀሞች እንዳሉ አስታውቆ የእግር ዱካ ጫማው ተመሳሳይ አለመሆኑም ሌሎች ማስረጃዎችን ውድቅ ሊያደርጋቸው አይችልም ብሏል፡፡

በተጨማሪም ከምስክሮቹ አንዱ፣ ቅዳሜ ከ8፡00 - 1፡30 ድረስ ቢሮ ገብተው፣ ኮሪደር የሚጠብቀውን ጥበቃ ወደ ምድር ቤት እንዲጠብቅ ማዘዛቸውን ከግምት አስገብቶ አቶ በላይ ላይ ክስ አይቀርብም የተባለውን ውሳኔ አንስቶ ክስ እንዲቀርብባቸው ወስኗል፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር የወንጀል ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊም ..በተጠርጣሪው ላይ  ወንጀል ክስ እንዲመሠረት አግባብ ባለው የበላይ አካል የተወሰነ በመሆኑ ቀደም ሲል በመምሪያው የተሰጠው አያስከስስም፤ ውሳኔ ቀሪ ሆኖ ተገቢው ክስ.. እንዲዘጋጅ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ዐቃቤ ሕግ ምኒልክ ምድብ ጽህፈት ቤት ፅፏል፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ የአዲስ አበባ ምድብ ፅህፈት ቤት ኃላፊ፣ ለፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ዐቃቤ ሕግ ምኒልክ ምድብ ፅህፈት ቤት በፃፉት ደብዳቤ “የተሰጡት የሰውና የሰነድ ማስረጃም ለዚህ ወንጀል ድርጊት በተጠርጣሪው አቶ በላይ ሂርጳ መፈፀሙን የሚያስረዱ ስለሆነ . . . ክስ እንዲቀርብ . . . “ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

አቶ በላይ በኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ በመምሪያ ኃላፊነት፣ በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅነት በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅነት አገልግለዋል፡፡
 
< Prev   Next >