Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልቻልንም
የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልቻልንም Print E-mail
Sunday, 04 May 2008
የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልቻልንም አስመጪዎች

-  እንደሁልጊዜው እየተሰጣቸው ነው
ብሔራዊ ባንክ

በታምሩ ጽጌ

ከውጭ አገሮች እቃ የሚያስገቡ ነጋዴዎች (ኢምፖርተርስ) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻላቸው ችግር እንደገጠማቸው ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ "ምንም የተፈጠረ ነገር ስለሌለ ሁልጊዜም እንደሚደረገው እየተሰጣቸው ነው" በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስተባብሏል፡፡
ከተለያዩ አገሮች የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችና ሌሎችም ዕቃዎች የሚያስመጡ ነጋዴዎች (አስመጪዎች) ከመጋቢት ወር 2ዐዐዐ ዓ.ም. ጀምሮ ወረፋ በዝቷል በሚል ምክንያት በተራ ያገኙት የነበረውን የውጭ ምንዛሪ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

ያለ ምንም ችግር በፈለጉበት ጊዜ ሁሉ የውጭ ምንዛሪ ያገኙ እንደነበር የገለፁት አስመጪዎች ሌላ ተጨማሪ ማስገባት ባለመቻላቸው ቀደም ብለው ያስገቧቸው ዕቃዎች ዋጋቸው መጨመሩንና ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አስመጪዎቹ ከአንድ ወር በፊት ቀጥታ ግንኙነታቸው ከኢንተርናሽናል ባንኪንግ ዲቪዥን (አይ.ቢ.ዲ) ጋር እንደነበርና ማረጋገጫም ከዚያው እንደሚያገኙ ገልፀው፣ አሁን አሁን ግን ከዋናው መስሪያ ቤት ማረጋገጫ ካልተላከ እንደማይሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተለያዩ ሥራ በመሥራት ላይ ባለበት ባሁኑ ሰዓት፣ በነሱ ላይ እየተፈጠረ ያለው የውስጥ ለውስጥ የቢሮክራሲ ሥራ የበለጠ የዋጋ ንረት እያስከተለ መሆኑንና መንግሥትም ያለባቸውን ችግር ሊገነዘብላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አንዳንድ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች እንደገለፁት፣ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ “አዲስ አስመጪዎች አትቀበሉ” መባላቸውን ገልፀው፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማጋጠሙንና ቀደም ብለው ኤል.ሲ የከፈቱትም በተራና በወረፋ በዋና መሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው መባሉንና ለነባሮቹ ብቻ እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ንግድ ባንኮች እጥረት ስላለ አያስተናግዱም፤ የሚል ሪፖርት እንዳልደረሳቸውና ሥራቸውን በትክክል እንደሚሰሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማኔጅመንት መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ሎሀ ገልፀዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለሦስት ወር ተኩል የሚሆን ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ (ሪዘርቭ) እንደሚይዝ የገለፁት አቶ ኤልያስ፣ በውጭ ምንዛሪ ላይ እጥረት ሊኖር እንደሚችል ነገር ግን ባለው መጠን እንዲሠሩ መባሉን ገልፀዋል፡፡

ንግድ ባንኮች ነባሮችንም ሆነ አዳዲስ ነጋዴዎችን አስመጪዎችን የመቀበል ግዴታ እንዳለባቸውና፣ የውጭ ምንዛሪ ምንጊዜም ቢሆን ተርፏቸው እንደማያውቅና አሁንም ቢሆን ያለውን አመጣጥም የማስተዳደር ሁኔታ መኖር እንዳለበት ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲፈጠር ያደረገው፣ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ፣ ኢትዮጵያም ለነዳጅ የምታወጣው ከፍተኛ ወጪ በመሆኑ ሊሆን ይችላል በማለት ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡
 
< Prev   Next >