Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ወሳጅ ያጡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች...
ወሳጅ ያጡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች... Print E-mail
Sunday, 04 May 2008
ወሳጅ ያጡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በድጋሚ እጣ ሊወጣባቸው ነው

በታምሩ ጽጌ

በአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ ባላደራ አስተዳደር የቤቶች ኤጀንሲ በሐምሌ ወር 1999 ዓ.ም እጣ ያወጣባቸውና ባለእጣዎቹ ያልወሰዷቸው አምስት ሺ ቤቶች በድጋሚ እጣ ሊወጣባቸው መሆኑ ተጠቆመ፡፡
በአስሩም ክፍለ ከተሞች ውስጥ የተሰሩና እጣ የወጣባቸው አምስት ሺህ ቤቶች፣ ባለዕጣዎቹን እንዲወስዱ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም ባለመቅረባቸው በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ 2000 ዓ.ም ሌላ እጣ ወጥቶባቸው ለባለዕድሎች ለማከፋፈል የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከውሳኔ ላይ መድረሱን ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ አረጋግጠዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ መጨረሻ (ሰኔ መጨረሻ) 2000 ዓ.ም ከአምስት ሺዎቹ ቤቶች በተጨማሪ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ጐፋና ጐተራ አካባቢ እየተገነቡ ያሉ ኮንዶሚኒየም ቤቶችም እጣ እንደሚወጣባቸው ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

አዲስ እየተገነቡ ባሉት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ የሚወጣው ዕጣ ለየት እንደሚል የገለፁት ምንጮቹ፣ 80 በመቶ ሥራቸው የተጠናቀቁትን ብቻ በማውጣት 20 በመቶ የሚሆነውን ሥራ ባለዕድሉ (እጣ የወጣለት) እንዲያስጨርስ ይደረጋል፡፡

ቀደም ብለው በወጡት የኮንዶሚኒየም ቤቶች እስካሁን ተጠናቀው እጣ ለደረሳቸው እንዳልተሰጡና ገና በመሠራት ላይ መሆናቸውን የገለፁት ምንጮቻችን፣ በዚህ ዓመት የሚሠሩትንም ሆነ ወደፊት ጽህፈት ቤቱ የያዛቸውን ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ ወይም 80 በመቶ ሥራቸው ሳያልቅ እጣ እንደማያወጣ ተናግረዋል፡፡

የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አጠቃላይ ሪፖርቱንና (የሚሰራቸውን ፕሮጀክቶች) የእጣ አወጣጡን በተመለከተ በያዝነው ሳምንት ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግ የገለፁት ምንጮቻችን፣ ምናልባትም ከአምስት ሺ ቤቶች በተጨማሪ አዲስ ባስገነባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይም በርካታ እጣዎችን ሊያወጣ ይችል ይሆናል በማለት ያላቸውን ግምት ተናግረዋል፡፡

“በመንገድ ልማትና ለኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ቦታው እንደሚፈለግ ተገልፆላቸውና የኮንዶሚኒየም ቤቶች እንደሚሰጣቸው ቃል ለተገባላቸው ነዋሪዎች ለምን ዕጣ ወጥቶባቸው ወሳጅ ያጡ ቤቶች አይሰጣቸውም?” በሚል ለጽህፈት ቤቱ ጥያቄ ብናቀርብም፣ ምላሽ አላገኘንም፡፡

ነዋሪዎቹን (በልማት ምክንያት የተፈናቀሉት) አነጋግረናቸው “እንኳን የኮንዶሚኒየም ቤት ቀርቶ የቀበሌም አልሰጡንም” በማለት በተደጋጋሚ ችግራቸውን ማቅረባቸውን፣ ነገር ግን የኮንዶሚኒየም ቤት የደረሳቸው ሰዎች፣ ቤታቸውን በማከራየት “በቀበሌ ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ” ገልፀዋል፡፡

የኮንዶሚኒየም ቤት የደረሳቸው ባለዕድሎች የደረሳቸውን ቤት በማከራዬት በቀበሌ ቤት ውስጥ መኖራቸው ለምንድነው ብለናቸው፣ “ይኸ ሀሰት ነው፡፡ አንድ ሰው ዕጣ ከደረሰውና ቤቱን ከተረከበ ከአንድ ወር ባላነሰ ጊዜ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ እንዲሁም ባለዕጣም መሸጥ፣ መለወጥና ማከራዬት አይችልም” በማለት ምላሽ የሰጡን የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በትሩ ላቀው ናቸው፡፡
 
< Prev   Next >