|
የዚምባብዌ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ይፋ ሆነ
|
|
|
|
Sunday, 04 May 2008 |
|
ለሳምንታት በውዝግብ የቆየው የዚምባብዌ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት በአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ መደረጉን የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ አመለከተ፡፡
በዘገባው መሠረት የኤምዲሲ ፓርቲ መሪ ሞርጋን ሳቫንጋሪ 47.7 በመቶ ድምጽ ሲያገኙ የዛኑ ፒ ኤፍ መሪ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ 43.2 በመቶ አግኝተዋል፡፡ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ሳንጋሪ ከዚህ በፊት በምርጫው ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘታቸውን በመጥቀስ፤ በሁለተኛ ዙር ውድድር እንደማይሳተፉ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
ሳቫንጋሪ በምርጫው ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ ያልተቆጠረ ድምጽ መኖሩን ጠቅሰው፤ የድምጽ ቆጠራው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አሸናፊ በመሆን የፕሬዚዳንትነቱን ስልጣን የሚጨብጡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የአገሪቱ ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር በበኩላቸው ሁለተኛ ዙር ምርጫ አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ሳቫንጋሪ ቢያሸንፉም ቅሉ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ግድ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ታዛቢዎችም በሚኒስትሩ ሃሳብ እንደሚስማሙ ተገልጿል፡፡
------------ የቲቤቱ መንፈሳዊ መሪ የሰላም መልዕክተኞችን ወደ ቻይና ላኩ
የቲቤቱ መንፈሳዊ መሪ የዳይላላማ ተወካዮች በቻይናና በቲቤት መካከል ያለውን ውዝግብ ለመፍታት ያለፈው አርብ ወደ ቻይና መጓዛቸውን የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ አመለከተ፡፡
በዘገባው መሠረት የሰላም ልዑካኑ በቻይና መንግሥትና በቲቤታውያን መካከል ካለፈው መጋቢት ጀምሮ የተፈጠረውን ግጭት በውይይት ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ ተጠቅሷል፡፡ ልዑካኑ የሚያደርጉት ውይይት በቻይና መንግሥትና በቲቤታውያን መካከል ካለፈው መጋቢት ጀምሮ ከተከሰተው ውዝግብ በኋላ የመጀመሪያ ይፋዊ ውይይት መሆኑ ተዘግቧል፡፡
የቲቤት መንግሥት ቃል አቀባይ ቱብቴን ሳምፋል፤ መልዕክተኞቹ ያለፈው አርብ ሆንግ ኮንግ መድረሳቸውን ከመግለጽ ውጪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
መልዕክተኞቹ የዳይላላማ ትኩረት የሆነውን የቲቤትን የሰላም ሁኔታ ለቻይና መንግሥት እንደሚያሳስቡ ተገልጿል፡፡ በዚህም በቀጠናው ሰላም የሚሰፍንበትን ሁኔታ የሚወያዩ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሂትለርን ለመግደል የሞከሩት አረፉ
በ1944 አዶልፍ ሂትለርን የመግደል ሙከራ በማድረጋቸው መንግሥት ለሞት ፍርድ ይፈልጋቸው ከነበሩት የጀርመን ባለሥልጣናት መካከል አንዱ በቅርቡ በ90 ዓመታቸው ማረፋቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ፍሊፕ ቮን ቦስሌጋር የተባሉት እኚህ ሰው የናዚው መሪ አዶልፍ ሂትለር በምስራቅ ፐርሺያ ጽ/ቤት እንዳለ በሻንጣ የተሞላ ፈንጂ ከጠረጴዛው ሥር አስቀምጠዋል፡፡
ነገር ግን ሻንጣው በጠረጴዛው እግር በመገፋቱ ምክንያት ሂትለር መጠነኛ ቁስለት ደርሶበት ከአደጋው ተርፏል፡፡
ሂትለርን የመግደል ሙከራ ያደረጉት ጓደኞቻቸው ሁሉ የተገደሉ ሲሆን እርሳቸው ግን አምልጠዋል፡፡ ሙከራው ከተፈፀመ ሰዓታት በኋላ ከተገደሉት ውስጥ ሻንጣው አስገብቶ ያስቀመጠው ቮን ሳታሪንበርግ አንዱ ነው፡፡ ሚስተር ቮን ቦስሌጋር ባለፈው ማክሰኞ ሌሊት መሞታቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል፡፡ |