| የፓርላማ አባላት በመግቢያ ፍተሻ ተማረዋል |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
![]() ፕሮፌሰር በየነ ![]() አቶ ልደቱ በኃይሌ ሙሉ የተቃዋሚ ፓርቲ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በምክር ቤቱ መግቢያ በር ላይ በሚካሄደው ፍተሻ “የሚያዋርድ” መሆኑን በመጥቀስ ቅሬታቸውን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰር በበኩላቸው የሚካሄደው ፍተሻ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢዴኅህ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ፍተሻውን አስመልክተው ሲናገሩ “ሕዝብ መርጦ ይወክልናል፡፡ እዚህ ያሉት ደግሞ ያወርዱናል” ሲሉ የምክር ቤት አባላት አላስፈላጊ መንገላታት ውስጥ እንደሚገቡ አብራርተዋል፡፡ የኢሕአዴግ ባለሥልጣን የሆኑት አንዳንድ የፓርላማ አባላት ሳይፈተሹ መኪና ይዘው በሌላ በር እንደሚገቡና ሌሎች የፓርላማ አባላት ግን ንጽህናው ባልተጠበቀ የሲሚንቶ ወለል ላይ ጫማቸውን እንዲያወልቁ፣ ቀበቶዋቸውን እንዲፈቱ እየተደረገ የሚዋረዱበት ሁኔታ መኖሩን ኘሮፌሰር በየነ አስረድተዋል፡፡ “በዚህም” ይላሉ ኘሮፌሰር በየነ “በሕዝብ እንደራሴዎች መካከል የሚታመንና የማይታመን እንዳለ ነው ሊነግሩን የሚፈልጉት” ካሉ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የደህንነት ጥበቃም አለም ውስጥ ካለው ሁሉ ገንኖ እንደሚወጣ ገልፀዋል፡፡ የመፈተሻ መሳሪያውን በተመለከተም ፕሮፌሰሩ ቅሬታ አላቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት መዳብና ጥቃቅን ብረታ ብረቶች ሳይቀር የመፈተሻ መሳሪያውን ማለፍ አይችሉም፡፡ በፍተሻው ሂደት ላይ የሚታየውን ውርደት መቀበል የማይፈልግ ሰው፣ ወደ ፓርላማ የመሄድ ፍላጎቱ እንደሚቀንስ የገለጹት ፕሮፌሰር በየነ፣ በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር የተቃዋሚ ፓርቲዎች የምክር ቤት አባላት ወደ ፓርላማ እንደማይሄዱ በዚህም ተሳትፏቸው እየተገታ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ “ጫማ እንድናወልቅ የምንገደድ ከሆነ፣ በስጋጃ ምንጣፍ ላይ ቆመን የምናወልቅበት ሁኔታ መመቻቸት ነበረበት” ያሉት ፕሮፌሰሩ እንደራሴዎቹ ጫማቸውን የሚያወልቁት ሲሚንቶ ወለል ላይ መሆኑ ችግር እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡ የሌሎች አገሮችን ሲናገሩም በአሜሪካ ያለው የፓርላማ ስርዓት የሕዝብ እንደራሴዎች ወደ ምክር ቤት የሚገቡበት የተለየ በር እንዳላቸውና ሌሎች ተመልካቾች ግን ተፈትሸውና መታወቂያ አስቀምጠው እንዲገቡ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት አሜሪካ ያለችበት ደረጃ ላይ ይደረስ ባይባልም አሁን ያለው የፍተሻ ሂደት መስተካከል አለበት፡፡ አያይዘውም “በሌላ አገር የሚገኝ አየር ማረፊያን የደህንነት መቆጣጠሪያ አልፈን የምንሄድ ሰዎች እንዴት ይህንን (የፓርላማውን መፈተሻ) አልፈን መሄድ ያስቸግረናል” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የኦፌድን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳም የፕሮፌሰር በየነን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ ስለፍተሻው ሲናገሩም “በር ላይ ተዋርዶ የገባ ሰው አስቦ መናገር እስኪችል ድረስ ደቂቃዎች ይወስዱበታል” ብለዋል፡፡ የፍተሻው ሁኔታ ሁልጊዜ እንደሚያስደነግጣቸው የሚናገሩት አቶ ቡልቻ 100 ሺህ ሕዝብ የሚወክል እያንዳንዱ የፓርላማ አባል ጫማውን እያወለቀና ቀበቶውን እየፈታ ሲዋረድ ማየት የሚያሳዝን ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አቶ ቡልቻ እንደሚሉት ጉዳዩ የደህንነት ሳይሆን ሰውየውን ለማሳነስና ሞራሉን ዝቅ ለማድረግ የሚሰራ ስራ ይመስላል፡፡ በሌሎች አገራት የገዥ ፓርቲና የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ምንም ልዩነት እንደማይታይባቸው የጠቆሙት አቶ ቡልቻ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ሳይፈተሹ የሚገቡበት ሁኔታ መታየቱ ልዩነት መኖሩን የሚያመላክት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የፓርላማ አባላትን አያያዝ በተመለከተም የውስጥ ደንብ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ቡልቻ እምነት አንድ ሰው የፓርላማ አባል ነው ከተባለ መፈተሽ የለበትም፡፡ የፓርላማ አባላት መቶ በመቶ መታመን አለባቸው፡፡ የኢዴአፓ መድህን ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው አሁን ካለው አጠቃላይ አካባቢያዊ ሁኔታ አንፃር ፓርላማን በመሳሰሉ ተቋማት ላይ ጠበቅ ያለ ፍተሻ ማካሄድ ለሁሉም ወገን አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ልደቱ እንደ ጉድለት ያነሱት በፍተሻ ስራ ላይ የተሰማሩት ሰዎች ለምክር ቤቱ አባላት የሚያሳዩት ክብር ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድም ለፈታሾቹ በቂ ስልጠና ሊሰጣቸው ይገባል የሚል እምነት አላቸው፡፡ “(ፈታሾቹ) ስነ ሥርዓትና አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ ጉዳዩን እንዲያስፈጽሙ ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል” ያሉት አቶ ልደቱ ፈታሾቹ ስራችን መፈተሽ ብቻ ነው፤ ብለው የሰውን ክብር ሊነካ በሚችል መልኩ ፍተሻ ማድረጋቸው አግባብ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የተሰነዘረው ቅሬታ በማስመልከት ያነጋገርናቸው የተወካዮች ም/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰር አቶ አለባቸው መረካ በበኩላቸው አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ሪፖርት እንዲያቀርቡ ሲጠሩ መጉላላት እንዳይፈጠር ባለሥልጣናት በሌላ በር እንዲገቡ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን የገዢው ፓርቲ አባላትም ሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በፍተሻ በር የሚገቡበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል፡፡ የመፈተሻ መሳሪያው ደረጃውን የጠበቀና ብረታ ብረት ካልሆነ በስተቀር የሚያስጮኸው ነገር እንደሌለ የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰሩ የሰዎች ጸባይ የሚለያይ ሆኖ እንጂ የጥበቃ ሀይሉ አሰራር ችግር የሚፈጥር አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ጫማቸውን የሚያወልቁበት ቦታ ንጽህናው የተጠበቀ አይደለም ለሚለው ሲመልሱ “ንጽህና አንፃራዊ ነው፡፡ የጫማ ማውለቂያው ቦታ ምንጣፍ አለው፡፡ የሌሎችንም አገሮች ልምድ አይቻለሁ፡፡ ያን ያህል የከፋ ነው ማለት አይቻልም” ብለዋል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት የጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዳኛቸው በፍቃዱ በበኩላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት አሉ የሚሏቸውን ችግሮች ቢያቀርቡላቸውና ቀርበው ቢነጋገሩ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |