|
Sunday, 04 May 2008 |
|
ለሥራ የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን በደል መከላከል እንዲቻል ወደ ቤይሩት /ሊባኖስ/ የሚደረገው የሥራ ሥምሪት ጉዞ ለጊዜው መታገዱን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛዎቹ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች በዜጎቿ ላይ የሚደርስ የመብት ረገጣ የቀነሱ ቢሆንም በሊባኖስ ያለው ሁኔታ ግን እየተባባሰ በመምጣቱ፣ በደልና እንግልት እንዲሁም ሞት፣ አሰሪዎች ፓስፖርት በመንጠቅ፣ በተለያዩ ቦታዎች በማዘዋወር በዝቅተኛ ክፍያ በማሰራት፣ ድብደባ፣ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና እስራት በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ እየተባባሰ በመምጣቱ ጉዞው መታገዱን ገልጿል፡፡
(ኢዜአ)
ጽህፈት ቤቱ 52 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰበሰበ
የጅማ ዞን ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የጽህፈት ቤቱ አስታወቀ፡፡
ገቢው የተገኘው ለዓመቱ ከተያዘው እቅድ ስድስት ሚሊዮን ብር ያህል እንደሚያንስና ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ18 ሚሊዮን ብር ያህል ብልጫ እንዳለው፣ በአጠቃላይ በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች የተሰበሰበው ከንግድ፣ ከግብርናና ከልዩ ልዩ የገቢ አርእስቶች መሆኑን ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡
(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 23 ቀን 2000 ዓ.ም)
በኢሪፕቲ ከተማ ለሦስት ሳምንታት መብራት ተቋረጠ
በአፋር ክልል ዞን ሁለት በኢሪፕቲ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠ ከሦስት ሣምንታት በላይ በመሆኑ ነዋሪዎች መቸገራቸውን ገለፁ፡፡
ነዋሪዎቹ ከተማዋ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆኗ ቢደሰቱም በተደጋጋሚ መብራት ስለሚቋረጥ የዕለት ተዕለት ሥራቸው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
(ዋኢማ)
ባንኩ 16ኛውን ቅርንጫፉን ከፈተ
አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማህበር እና አንበሳ ኢንሹራንስ 16ኛና 9ኛ ቅርንጫፎቻቸውን በትናንትናው ዕለት ከፈቱ፡፡
አንበሳ ባንክና ኢንሹራንስ አዲሱን ቢሮአቸውን የከፈቱት መርካቶ ራጉኤል ቤተክርስቲያን አጠገብ በሚገኘው በአዲስ አበባ የገበያ ማዕከል ህንፃ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
(ጋዜጣዊ መግለጫ)
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት እያገኘ ነው
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የሰብዓዊ መብትና የልማት ጥያቄ እየሆነና ዓለም አቀፋዊ ትኩረትን እያገኘ መምጣቱን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የአካል ጉዳተኛ ዜጎች በሥራ ስምሪት ረገድ የሚደርሱባቸውን መድልዎ ለማስወገድ ይቻል ዘንድ የተሻሻሉ አዋጆችን ለአስፈፃሚው አካላት የማስተዋወቅና የማስፈፀሚያ ስልቶችን የመዘርጋት ተግባራት የሚገኙበት መሆኑን አመልክቷል፡፡
(ኢዜአ)
ለ220 ሰዎች የዓይን ቀዶ ሕክምና ተደረገ
የኢትዮጵያ ዓይን ሐኪሞች ማኅበር ቡድን በጐዴ ሆስፒታል ከአንድ ሺ ለሚበልጡ ማየት ለተሳናቸው ሰዎች ዓይን ሕክምና መስጠቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው ከማህበሩ ጋር በመተባባር በተደረገው የሕክምና አገልግሎት እድሜአቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን፣ በአስር ቀናት ውስጥ ከ650 ለሚበልጡ የትራኮማና ለ347 ሰዎች ደግሞ የዓይን ሞራ ገፈፋ ሕክምና እንዲሁም በደብረማርቆስ ሆስፒታል በዓይን ሞራ ግርዶሽ ማየት ለተሳናቸው 220 ሰዎች የቀዶ ህክምና መስጠቱን ገልጿል፡፡ (ኢዜአ) |