| የአካባቢ ጥበቃና ኢንቨስትመንት... |
|
|
| Thursday, 10 January 2008 | |
|
የአካባቢ ጥበቃና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ተወቃቀሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ለኢንቨስተሮች ፈቃድ ሲሰጥ በግልባጭ ስለማያሳውቀው ለአካባቢ ብክለት ምክንያት ሆኗል ሲል ታህሳስ 17 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በጊዮን ሆቴል ባካሄደው የአንድ ቀን አወደ ጥናት ላይ ወቀሰ፡፡ ምንም የምንወቀስበት ነገር የለም፡፡ ማሳወቅ ያለብንን ሁሉ እያሳወቅን ነው የምንሰራው ሲል ባለሥልጣኑ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ባለሥልጣኑ ታህሣሥ 17 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማትና የአካባቢ ደህንነት በሚል ከሄንሪሽ ቦል ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ባካሄደው የአንድ ቀን አውደ ጥናት ላይ እንደገለፀው ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ለባለሀብቶች ፈቃድ ሲሰጥ በግልባጭ ለአካባቢ ጥበቃ ባለማሳወቁና በመተባበር ባለመሥራታችን የተነሳ የሚቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች ለአካባቢ ብክለት ተቀዳሚ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ ኢንዱስትሪ ከማቋቋማቸው በፊት ስለ አካባቢ ብክለት ግንዛቤ ማስጨበጥ አስፈላጊ ነበር፡፡ ይኸ ደግሞ የአካባቢ ባለሥልጣን ተቀዳሚ ሥራ ነው፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ለባለሀብቶች ፈቃድ ሲሰጥ በግልባጭ ስለማያሳውቀን በአብዛኛው ብክለቱ ከተከሰተ በኋላ ወደ ማስተማሩ ልንገባ እንገደዳለን በማለት በባለሥልጣኑ መስሪያ ቤት የአካባቢ ብክለትና ሥነ ምህዳር ዋና ኃላፊ ወ/ሮ ፋንቱ ሸዋአማረ በአውደ ጥናቱ ላይ ተናግረዋል፡፡ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች ወንዞችንና መንገዶችን ተከትለው የተመሠረቱ በመሆናቸው በነዋሪው ህብረተሰብ ላይ የሚያመጡት ከፍተኛ ተፅዕኖ አለ ያሉት ወ/ሮ ፋንቱ፣ በከተማዋ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን በዳታ አሰባስበው የት የት እንደሚገኙ ለቱሪስትም ሆነ ለአገር ውስጥ ነዋሪው መረጃ ለመስጠት በሚል ቢንቀሳቀሱም ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች ስለራሳቸው የሚገልፅ ማስረጃ (የት ክፍለ ከተማና ቀበሌ እንደሚገኙ) እንደሌላቸው፣ በጥቆማ ያለምንም ማስታወቂያ ቢሯቸውን ፈልገው ቢሄዱም በጥበቃ እንዳይገቡ መከልከላቸውን፣ የባለሥልጣኑን መስሪያ ቤት አርማ የያዘ ደብዳቤ ቢያሳዩም መከልከላቸውን የተናገሩት ኃላፊዋ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ነው፡፡ ምክንያቱም ፈቃድ ሲሰጥ በግልባጭ ለእኛ ቢያሳውቀን ይኸ ሁሉ ችግር አይፈጠርም ነበር ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ባሥልጣን በበኩሉ ማንኛውንም ዓይነት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ስንሰጥ በግልባጭ ለአስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና ለንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ እናሳውቃለን በማለት የኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ማስታወቂያ ቡድን መሪ አቶ አብረሃም ፋንታው ለሪፖርተር ገልፀዋል፡፡ የቡድን መሪው ጨምረው እንደገለፁት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በሥራ ላይ እንዲውሉ ከመፍቀዳቸው በፊት ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በጋራ ካቋቋሙት የጋራ ቡድን ጋር በመሆን እንደሚያረጋግጡ ተናግረዋል፡፡ የአካባቢን ብክለት ለመከላከል በማሰብ የሚገነቡ ኢንዱስትሪዎችን በመከፋፈልና በመለየት እንሰራለን ያሉት አቶ አብርሃም፣ የራስን ስህተትና የአሰራር ድክመትን ለመሸፈን ካልሆነ በስተቀር እስካሁን በመተባበርና በመተጋገዝ በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ ስለ አካባቢ ብክለት አናውቅም የሚሉት ፋብሪካዎች ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ያጠራጥረኛል፡፡ የሚጠጣ ውሃ ቢያጡ ለፋብሪካው ከሚጠቀሙበት ወንዝ ቀድተው የሚጠጡ ባለሀብቶች የሉምና በማለት የተናገሩት አውደ ጥናቱን ሲያወያዩ የነበሩት ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረእግዚአብሔር ናቸው፡፡ መንግሥት የአካባቢን ብክለት በተመለከተ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ነውና እኛም እንጣር ብለዋል ዶ/ር ተወልደብርሃን፡፡ አውደ ጥናቱን የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ከንቲባ ብርሃነ ዴሬሳ በበኩላቸው፤ የአካባቢ ብክለት የሚጀምረው ከድምፅ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን፣ በመስጊድ ውስጥ ያሉ የድምፅ ማጉያዎችንና ሙዚቃ ቤቶችን መመልከት ይቻላል፡፡ የታመሙና ህፃናት መተኛት አይችሉም፡፡ ህግን ተከትለን ብዙ ነገር ማድረግ እንችላለን፡፡ ማንም ዓለም እንደ ኢትዮጵያ ያለ ህግ ያለው አገር የለም፡፡ ግን አንጠቀምበትም፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት መንግሥታት፣ ሚኒስትሮች፣ ከንቲባዎችና ምሁራን ሲገናኙ ዋና መነጋገሪያ አጀንዳቸው የአካባቢ ብክለት ሆኗል፡፡ በመሆኑም እኛም ህጉን ተከትለን ብክለትን መከላከል አለብን በማለት ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |