| በህይወት የሌሉ ግለሰብ... |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
|
በህይወት የሌሉ ግለሰብ በአዲስ አበባ ምርጫ አሸነፉ
በተሾመ ንቁ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ምርጫ የቅንጅት ፓርቲን ወክለው በመቅረብ በቦሌ ክፍለ ከተማ ከተቃዋሚ ፓርቲ በብቸኝነት አሸንፈዋል የተባሉት እጩ በህይወት የሌሉ መሆናቸው ተገለፀ፡፡ ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት አልፈለገም፡፡ ሚያዝያ 5 ቀን 2000 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በቦሌ ክፍለ ከተማ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ምርጫ ያቀረባቸውና በውድድሩ 6 ሺህ 37 ድምፅ አግኝተው፣ በአዲስ አበባ ብቸኛ ተቃዋሚ ፓርቲ አሸናፊ መሆናቸው ይፋ የተደረገላቸው ወ/ሮ ቦድዲት አንተነህ ቡጀቴ በሕመም ምክንያት ካረፉ ከ26 ቀናት በላይ ተቆጥረው ነበር፡፡ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ ሳሳሁልህ ከበደ ወ/ሮ ቦድዲት አንተነህ ምርጫው ከመድረሱ በፊት ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ፓርቲው በደብዳቤ ለቦርዱ ማሳወቁን ይገልፃሉ፡፡ ይህንንም ጉዳይ በተመለከተ ለምርጫ ቦርዱ በቁጥር ኦዴፓ/208/2000 በቀን 16-07 - 2000 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ማሳወቃቸውን የሚገልፅ ግልባጭ ለዝግጅት ክፍላችን ልከዋል፡፡ በአቶ ሳሳሁልህ ገለፃ መሰረት ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት በተፃፈ ደብዳቤ ወ/ሮ ቦድዲት አንተነህ ቡጀቴ መጋቢት 9 ቀን 2000 ዓ.ም በህመም ምክንያት ከዚህ አለም መለየታቸውን ተገልጿል፡፡ ፓርቲው በደብዳቤው በዚህም ምክንያት በምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/99 አንቀፅ 55 መሰረት ተተኪ እጩ መመደቡንም ገል..ል፡፡ ዋና ፀሀፊው በደብዳቤው በወ/ሮ ቦድዲት ምትክ፣ ወ/ት ትዝታ ጌታሁን በቦሌ ክፍለ ከተማ እንዲወዳደሩ አሳውቋል፡፡ “ይህ እንዲህ ሆኖ ሳለ” ይላሉ አቶ ሳሳሁልህ “የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስተካከያ ሳያደርግ ቀርቷል”፡፡ በዚህም ምርጫ ቦርድ ባወጣው የምርጫ ውጤት ላይ ወ/ሮ ቦድዲት 6 ሺህ 37 ድምፅ በማግኘት ማሸነፋቸው መገለፁን ጠቁመዋል፡፡ አቶ ሳሳሁልህ በምርጫው ቦርድ ስህተት ምክንያት ፓርቲው ያገኘው ድል ሊሰረዝ እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ በውድድሩ 5993 ድምፅ ያገኙትን የፓርቲውን እጩ ተወዳዳሪ ዶ/ር ለምለም መኮንን እንዲያሳልፍ ዋና ፀሐፊው አሳስበዋል፡፡ የመኢብን ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መስፍን ሽፈራው በበኩላቸው በምርጫው ውጤት ላይ በቅንጅት ፓርቲ ወይም በምርጫ ቦርድ ምክንያት ስህተት መከሰቱን ጠቁመው፤ “የምርጫው ውጤት ሙሉ ለሙሉ ተሰርዞ በጣቢያው የመኢብን እጩ የሆኑት ወ/ት ገነት ይማም ወለሎ ሊያልፉ ይገባል” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡ በምርጫ ጣቢያው የተከሰተውን “ስህተት” በተመለከተ በአዲስ አበባ የምርጫ አስተባባሪ አቶ ደስታ ሀ/ሚካኤል ተጠይቀው የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት በጉዳዩ ዙሪያ ውሳኔ ለመስጠት እየተወያየ መሆኑን ከመጥቀስ ውጪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ በሚያዝያ 5 ምርጫ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ቤት በቦሌ ክ/ከተማ ኢሕአዴግ ያቀረበውን ዕጩ በመሠረዙ ምክንያት (በፎርፌ) የቅንጅት ፓርቲ ዕጩ ማሸነፋቸውን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |