Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ተቋሙን ለመመዘን ይረዳል
ተቋሙን ለመመዘን ይረዳል Print E-mail
Sunday, 04 May 2008
በሪፖርተር ጋዜጣ በተለያዩ ጊዜያት፣ በአገሪቱ ያለውን የሙስና ሁኔታ የሚያመላክቱ በግለሰብም ሆነ በተቋማት ደረጃ በርካታ ዜናዎች ተሠርተዋል፡፡ የግለሰቦችንም ሆነ የተቋማትን ሙስና በሚመለከት የፌዴራል ሥነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተለያየ ጊዜ ላወጣቸው ሪፖርቶች የዜና ሽፋን ሰጥታችኋል፡፡
በረቡዕ ሪፖርተር ጋዜጣ ዜና ገፅ ላይ ደግሞ ኮሚሽኑ የ2000 ዓ.ም የሥራ ክንውኑን በተመለከተ ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን ሪፖርት በመተቸት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሃሳብ መቅረቡ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙስናን ለማጋለጥ ፀረ ሙስና ያከናወናቸውን ተግባራት ለመገምገምና በአገሪቱ ካለው የሙስና ሁኔታ አንፃር የተቋሙ እንቅስቃሴን ለመመዘን ይረዳልና፡፡

(ብሌን፣ ከስድስት ኪሎ)

ኢሠማኮ የኢንዱስትሪ ሰላምን ያስፍን

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ መጋቢት 7 ቀን 2000 ዓ.ም ስለ ባህርና ትራንዚት ተቀናሽ ሠራተኞች የወጣው ዜና ነው፡፡ እኔም በመንግሥታዊ መ/ቤት ውስጥ ተቀጥሬ በማገልገል ላይ የምገኝ ስለሆንኩ የምሠራበት ድርጅት እንደ ባህር ትራንዚት ድርጅት መዋቅር ሰርቶ በመጠባበቅ ላይ ነኝ፡፡ ከላይ የተጠቀሰው መ/ቤት የተቀናሽ ሠራተኞች እጣ ፈንታ እንዳይደርስብኝ ሥጋት ላይ እገኛለሁ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ረቡዕ ሚያዚያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም በገጽ ሁለት በወጣው ዜና ይኸው የባህር ትራንዚት መ/ቤት አሰሪና ሠራተኛ አዋጅ 377/96ን ጥሶ እንዲህ አይነት በደል በዜጎች ላይ ሲፈፀም የሚመለከተው አካል አስቸኳይ የእርምት እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ይሄ እንዲሁ በዝምታ ከታለፈ በመላው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ላይ የሚደርስ ቀውስ ይሆናል፡፡ የሠራተኛው ተጠሪ እንደመሆኑ መጠን በአሁኑ ሰዓት ሠራተኛው  በቢ.ፒ.አር አማካኝነት የሥራ ዋስትናውን እንዳያጣ ኢሠማኮ በመነጋገር የኢንዱስትሪ ሰላም ማስፈን ይኖርበታል፡፡

(ዮሴፍ በላይ፣ ከቴሌ መድኃኒአለም)

መፍትሄ

በቅርቡ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከፊሊጶስ ቤተ ክርስቲያን እስከ አስኮ፣ ከጉለሌ እስከ ሳንሱሲ ሲያሰራቸው የነበሩ መንገዶች ሥራዎችና መስተጓጎላቸውን አንብቤ አዝኛለሁ፡፡ በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ ካሉት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ መንገዶች አንዱ የአስኮ መንገድ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በሰንከላ ምክንያት ተቋርጧል፡፡ የነዋሪው ብዛት፣ የመንገዱ ጥበትና የትራፊክ ጭንቅንቁ ከግምት ውስጥ ቢገባ መንገዱ በምንም ሁኔታ አይታጠፍም ነበር፡፡ በየዓመቱ በመንግሥት የሚያዝለትን በጀት እየታጠፈ ወደ ሌላ ማዛወሩ መልካም አይደለም፡፡ የአስኮ መንገድ ስምንት ያህል ድልድዮች ያሉት ሲሆን አያድርስና አደጋ አጋጥሞ አንዱ ድልድይ እንኳን ቢፈርስ ሌላ ተለዋጭ መንገድ የለውም፡፡ ስለሆነም የተቋረጡት የመንገድ ሥራዎች ቶሎ መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡

(ጉታ፣ ከአስኮ)

ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ድረሱለት

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ችግር የተለየና አሳሳቢ ነው፡፡ በግቢው ውስጥ ጥቂት ጉልበተኞችና ከግቢ ውጭ የሚገኙ አጋሮቻቸው በኅብረት የሚያንቀሳቅሱት ቡድን ሴቶችን ከግቢው አስገድደው እስከማስወጣት የሚደርስበት ጊዜ አለ፡፡ የቡድኑ አባላት ይደባደባሉ፣ ሞባይልና ብር ይቀበላሉ፡፡ ማርክ ከማስጨመር ጀምሮ የተለጠፈ ግሬድን እስከማስለወጥ ደረስ የሚዘልቅ ተግባር ያከናውናሉ፡፡

ዩኒቨርሲቲያችን የተማሪዎቹን ደህንነት ማስጠበቅ ካቃተው ቆይቷል፡፡ ይህንን ክፍተት የተረዱት ጉልበተኞች አሁን አሁን ባደባባይ ሰው መግረፍና መዝረፍ ጀምረዋል፡፡ ለዚህም በቅርቡ በጠርሙስ ተፈነካክቶ ከሞት የተረፈው የተማሪዎች መማክርት አባልና በዋናው የግቢው በር በግድ በፖሊሶች ፊት እየተጎተተች ወጥታ ጉዳት ደርሶባት ትምህርቷን አቋርጣ የሄደችው የሕግ ተማሪ ምስክሮች ናቸው፡፡

የተማሪውን ደህንነት ያስጠብቃሉ ተብለው የተመደቡ አንዳንድ ፖሊሶች ራሳቸው የመብት ጥሰት ይፈጽማሉ፡፡ በእነሱ ይፈፀማል ተብሎ የማይታሰብ ድርጊት ከመፈፀማቸው በተጨማሪ በተለይም ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎችን እንደ ባዕድ ይቆጥራሉ፡፡ በቅርቡ በፖሊሶች ተደብድቦ አካል ጉዳተኛ በሆነ ተማሪ ምክንያት ሰልፍ እስከመውጣት፣ የግቢው ፖሊሶች በፌዴራል ፖሊስ ይተኩልን እስከማለት ተደርሷል፡፡ የመመገቢያ ካርድ እየቀሙ ተማሪው ለቀናት የሚያስርቡ፣ መታወቂያ እየቀሙ መውጫና መግቢያ የሚያሳጡ ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲያችን የብሄር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት ግጭት ብሎ ነገር አይታወቅም፡፡ ከሌላው ዩኒቨርሲቲ የተለየና ጥልቅ መተሳሰብና መቻቻል ያለበት ግቢ ነው፡፡ ነገር ግን ጥቂት ብልሹዎችን መቆጣጠር ስላልተቻለ የሥጋትና የፍርሃት ኑሮ ይኖራል፡፡

(ከባህር ዳር ተማሪዎች)

የሕግ የበላይነት ይከበር


የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን መታሰርን በሚመለከት የተለያዩ ጽሑፎች እየወጡ ነው፡፡ የድምፃዊው አድናቂዎች ሰላማዊ ሰልፍ እስከመውጣት ደርሰዋል፡፡ ሌላ አገር ሰልፍ የሚወጣው ሕግ ይከበርልን፣ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥልን፣ ገለልተኛና ነፃ ፍርድ ቤት ይቋቋምልን በማለት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ይከበር ስንል የምንወደው፣ የምናደንቀውና የምናከብረውም አካል  ጭምር ሕግ ፊት ይቅረብ ማለታችን ነው፡፡ ይህንን ሂደት በምንም መልኩ ሊደናቀፍ አይገባም፡፡

ቴዎድሮስ ካጠፋ የማይታሰርበት ምክንያት የለም፡፡ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው፡፡ አዝማሪ ይሁን ገበሬ፣ ተማሪ ይሁን መምህር፣ ሃብታም ይሁን ድሃ፣ ስልጣን ላይ ያለ ይሁን ስልጣን የሌለው፣ ታዋቂ ይሁን ተራ በሕግ ፊት ሁሉም እኩል ነው፡፡

አደጋው በወንድማችን፣ በዘመዳችን፣ ወይም በራሳችን ላይ ቢሆን ምን እናደርግ ነበር? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ የሕግ የበላይነት በሰው የበላይነት እንዲለወጥ የሚያስገድድ፣ በፍርድ ቤት ላይ ተፅዕኖ ከማሳደሩም በላይ የሕገ መንግሥቱን ልዕልና የሚፈታተን ድርጊት ነው፡፡ የምንወደውና የምናደንቀው ሰው ፍጹም ነው፣ አይሳሳትም ማለት ነው? በሕግ የሚጠየቀው ወገን የሌለው ብቻ ነው ማለት ነው? ሰው ማልቀስ ያለበት ቴዎድሮስ በመታሰሩ ወይስ ሰው በመሞቱ? ቆም ብለን ምን እያደረግን እንደሆነ እናስብ፡፡

(ከበደ በላቸው፣ ከአዲስ አበባ)
 
< Prev   Next >