Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ቀኑ እየጨለመበት የመጣው የኘሬስ ነፃነት
ቀኑ እየጨለመበት የመጣው የኘሬስ ነፃነት Print E-mail
Sunday, 04 May 2008
ዓርብ ሚያዚያ 17 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ "የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ እንዲቀርብ ሦስት ፓርቲዎች ተስማሙ" በማለት ዘግቧል፡፡ ጋዜጣው "ለበርካታ ጊዜያት ጥናትና ውይይት የተደረገበት" ያለው በጋዜጣው ዘገባ መሰረት ዳግም በፓርላማ የገዢው ፓርቲ (የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር) WHIP "ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ጥናት ተደርጐበታል" ያሉት ይህ ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ እንዲቀርብ መስማማታቸውን የገለፁት ሦስት ፓርቲዎች ናቸው ተብሏል፡፡

 

ከ1995 ዓ.ም. የመጀመሪያ አጋማሽ ውስጥ የኢትዮጵያ የኘሬስ ሕግ ረቂቅ ሆኖ ብቅ ያለው እስከ 1996 መጨረሻ ድረስ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ አገር ጭምር ከፍ ያለ ተቃውሞ ያስነሳው በርካታ እና አንኳር "መሠረታዊ ሀሳቦቹ" በአገሪቱ አዲስ የወንጀል ሕግ፣ በንግድ ሥራ ፈቃድና ምዝገባ ደንብ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባር ማሻሻያዎች አማካኝነት ሠርገው ገብተው የፀደቁለት ይህ ረቂቅ ሕግ "ለፓርላማ እንዲቀርብ" እና እንዲፀድቅ የተስማሙት ሦስት ፓርቲዎች አነሰም በዛም ፓርላማ ውስጥ መቀመጫ ያላቸው ናቸው፡፡ ልኩና መልኩ ቢለያይም ትርጉሙና አንደምታው ከሚያሰማው ከሚያስመዘግበው የተቃውሞና የመከራከሪያ ድምፅም ሆነ ከሚያስከትለው ውጤት አኳያ የሚፈይደው ነገር ባይኖርም ፓርላማ ውስጥ የሕዝብ ውክልና ወይም መቀመጫ ያላቸው ፓርቲዎች ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ አልነበሩም፡፡

የተጠቀሰው የሚያዚያ 17/2000 ዓ.ም. የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዜና ራሱ በዘገባው ዜና መሠረትም ቢሆን "ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በእዚህ መድረክ ላይ ላለመሳተፍ ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸውን" የኢህአዴግ ፓርቲ የፓርላማ ዋና ተጠሪ መግለፃቸው ተነግሯል፡፡ ስብሰባ ረግጠው ወጥተዋል፤ ከዚህም የተነሳ "ፓርቲዎቹ ላጠፉት ጥፋት ይቅርታ ከጠየቁ በመድረኩ ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ"ና ይችላሉ፤ እንዲሁም "በመድረኩ ባይሳተፉም በቀጣይ መድረክ ላይ በጉዳዩ ላይ የመወያየት እድል" አላቸው የተባሉት ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች "ስብሰባ ረግጠው" ወጡ የተባሉት የኘሬሱ ሕግ ረቂቅ የተባለው ወይም የእንደዚህ ያለው "መድረክ" አጀንዳ የመሆን እድል ሳያጋጥመው በፊት ነው፡፡

በአዲስ ዘመን እና በሌሎችም የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ዜና ዘገባ መሠረት "ከጥቃቅን የሀሳብ ልዩነቶች" ካገላለፅና ከቅርጽ አኳያ ካልተግባባንባቸው ጥቃቅን ጉዳዮች በስተቀር ሰነዱ የአገሪቷን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በማጠናከር ረገድ አስተዋፅኦ እንዳለው እናምናለን፣ ረክተንበታልም" የተባሉትን ረቂቅ የኘሬስ ሕግ ፓርቲዎቹ እንደቡድን የፓርላማ አባላቱ በየግላቸው ምን ያህል ያውቁታል? ምን ያህልስ ሊያውቁት ይችላሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች የሚነሳው ከሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች አኳያ ነው፡፡

የመጀመሪያው የይዘት ጥያቄና ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ "በአሁኑ ጊዜ ረቂቅ አዋጁ ብዙ ማሻሻያዎች እንደተደረጉበትና አሁን ባለው ደረጃ ጥሩና ጠቃሚ ሆኖ" ስለመገኘቱ የተነገረለት የሕግ ረቂቅ የኘሬስ ነፃነት የሕልውና መገለጫ የሆኑ፤ የሕግ ድንጋጌ መሰረታዊ ሀሳቦችን (ሌድስሌቲቭ ኘሪንሲኘልስ) አካትቷል? ረቂቁ ያካተታቸው የምዝገባ የፈቃድ የብቃት ማረጋገጫ የኘሬስ ባለቤትናትና በኘሬስ ሥራ የመሰማራት መብት እንዲሁም የኘሬስን ውጤት ይዘት ሕጋዊነት የማረጋገጥ ግዴታ በማን ላይ ይጣል ብሎ ረቂቁ የወሰደው የፖሊሲ ምርጫ አገራችን በሕገ መንግሥቷ አማካኝነት የገባችው ኢንተርናሽናል ግዴታ የሚያሟሉ ናቸው ወይ? የሚሉትንና ተመሳሳይ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ ናቸው፡፡

ሁለተኛውና ዓቢይ መሰረታዊ ጉዳይ፣ በዚህ ፅሁፍም ጉዳዬ ብዬ የማሳየው ቁም ነገር የ"አካሄድ" የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት የአገርን ሕግ የሚመለከተው ነው፡፡ ጉዳዩን "ሁለተኛ" አድርጌ በማቅረቤ፣ የ"አካሄድ" ብዬ በመጥራቴ አንባቢ ባጠቃላይ፣ ረቂቁ የኘሬስ ሕግ ፓርላማ እንዲቀርብ የተስሙት፣ ረቂቁ የኘሬስ ሕግ ፓርላማ እንዲቀርብ የተስማሙት፣ ፓርላማ መቅረብ የሚችልበትን ሂደት ሁሉ አልፏል፣ ፓርላማ ሊቀርብ የሚያስችለውን የይዘትና የቅርፅ ልክና መልክ አግኝቷል ብለው ስምምነት ላይ የደረሱ ፓርቲዎች በተለይ ይህንን የዚህ ፅሁፍ ዋና ርዕሰ ጉዳይ ያደረጉትን ጭብጥ እንዳያጣጥሉብኝ በቅድሚያ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ "እውነት" ላይ የመድረስ ጉዳይ በውጤቱ ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም፡፡ መንገዱንም ይጨምራል፡፡ አለዚያ የፍትህም፣ ጥሩ የሚባልም ሕግ የማፅደቅ ጉዳይ "የትም ፍጭው ዱቄቱን ረብቻሪ አምጭው" ነገር ሆኖ ይቀራል፡፡ ከሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት አንፃር ደግሞ ከዚህ የበለጠ የአገርን የሕግና የፍትህ ሥርዓት በቀጥታ የሚመለከቱ ምናልባትም የሚያናጉ ትርጉምና አንደምታ አለው፡፡

ዓርብ ሚያዚያ 18 ቀን የተሰባሰቡ የሦስት ፓርቲዎች መሪዎች ረቂቅ ሕጉ ለፓርላማ እንዲቀርብ ተስማሙ የሚለው ዜና ስድስተኛ ዓመቱ ውስጥ በገባው የኘሬስ ሕጉ ረቂቅ አዋጅ ታሪክ ውስጥ እንደ አንደኛው ተጠቃሽ ቀን ተደርጐ የሚወሰድበት ምክንያት አለ፡፡ በሕግ የተደነገገ የኢትዮጵያ የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ቢኖርም አንድ ረቂቅ ሕግ ፓርላማ ቀረበ ማለት ፀደቀ ማለት ነው፡፡ አለቀለት አበቃለት ማለት ነው፡፡ በአገሪቷ ያለፉት የ17 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ይህን የሁል ጊዜ፣ ከአምስት ዓመት በላይ በረቂቅ ሕግነቱ እያንገራገረ እያወዛገበ፣ "አልፀድቅም" ብሎ ያስቸገረ "መደበኛው"ና የታወቀው አሰራር ቢኖርም ከአስቸጋሪነቱ የተነሳ እንዳለና ፊት ለፊት እንዲፀድቅ ማድረግ አልችል ብሎ በሌሎች ሕጐች ደንቦች ውስጥ "ተሰርቆ" ተደብቆ እየገባ አሁን ብዙ ትርጉም የለሽ ሆኖ የቀረ ብቸኛ የሕግ ረቂቅ ይህ ብቻ ነው፡፡ ያም ሆኖ በኘሬስ ረቂቅ ሕጉ ላይ የሚደረገው ውይይት፣ የሚከፈተውና የሚዘጋጀው መድረክ የመሰረታዊና የዋና ዋና የዲሞክራሰያዊ ተቋማት ግንባታ ዋነኛ ሥራ ነው ተብሎ ከምርጫ 97 ማግስት በኋላ በተነገረው መሪ ቃል መሠረት ረቂቁን እንደገናና እንዳለ የመመልከት ተሟጥጦ ያላለቀ የተስፋ ጭላንጭል በውስጣችን እየተቀጣጠለ መምጣት ጀምሮ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ1998 ዓ.ም. የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ለፓርላማው ባቀረቡትና ፓርላማውም ባፀደቃቸው ሪፖርቶች የገለፁት የኘሬስ ሕጉ የሚከተላቸው የሕግ አረቃቀቅ ሥነ ሥርዓት ከዋሻው ጫፍ ወዲያ ማዶ የሚገኘውን የብርሃን ጭላንጭል አሳየን፤ ይህም ብርሃን እየሰፋ እየገፋ መጣ ስንል አጠገባችን እየደረሰ ያለው የሚያዚያ 16 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ውሳኔ ምንነቱን የገለፀው ብርሃን ለካስ በዋሻ ውስጥ ወደዚህ እየገሰገሰ፣ የኘሬስ ነፃነትን እየዳጠና እየጨፈለቀ የሚመጣው ባቡር ብርሃን እንጂ ከዋሻው ጫፍ ባሻገር ያለው ፀሐይ ብርሃን አይደለም፡፡

የኘሬስ ሕጉን ረቂቅ አካሄድ በሚመለከት ረገድ ከሁሉም አስቀድሜ የምነሳው ሕጉ እንዴት መነጨ? ከሚለው ሕግ የማውጣት ሥነ ሥርዓትና ሥርዓት አካል ከሆነው መሰረታዊ ጉዳይ በመነሳት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚነሱ በርካታ ጭብጦችና ቁም ነገሮች አሉ፡፡

የረቂቁ የኘሬስ ሕግ ደራሲና አመንጪ ሆኖ ብቅ ያለው እንደሚታወቀው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ነው፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የማንኛውም ዓይነት ሕግ ረቂቅ በተለይም የኘሬስ ሕግ ረቂቅ የማመንጨት ሥልጣን አለው ወይ? የሚል ጥያቄ ሊኖረውም አይገባም፣ አይችልም የሚል ተቃውሞ የሚቀርበው ከሕግ ውጭ ሆኖ አይደለም፡፡ ይልቁንም በሕጉ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ነው፡፡

የማስታወቂያ ሚኒስቴር የኘሬሱን ሕግ ረቂቅ ባስተዋወቀበትና ማመንጨት ባቀረበበት ወቅት አገሪቷ የምትተዳደርበትና በሥራ ላይ የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ አወጣጥ ስነ ስርዓት አዋጅ ቁጥር 271/1994 ነው፡፡ "የምክር የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ከህገ መንግሥቱና ከዓለም አቀፍ የፓርላማ መርሆዎች ጋር የተጣጣመ ሆኖ ዲሞክራሰያዊ ባህሪያትን የሚያጐላና ለሕዝብ ግልፅ የሆነ አሰራር መከተል ስለሚኖርበት" ተብሎ የወጣው፣ ይህ ሕግ ተፈፃሚ መሆን የጀመረው ከሚያዚያ 15 ቀን 94 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ የ1994ቱ ሕግ እስኪወጣ ድረስ ይሰራበት የነበረው አግባብ ያለው ሕግ በ1988 ዓ.ም. የወጣው (በዚያው ዓመት በአዋጅ ቁጥር 33/88 እንደተሻሻለ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 14/1988 ነበር፡፡

አሁን ዛሬ ሥራ ላይ ያለውን የፓርላማውን የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት የሚወስነውን ሕግ ዓይነትና ምንነት ለማሳየት የ1988ቱ የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ሕግ አዋጅ በ1994ቱ መሻሩንና መተካቱን የ1994ቱ አዋጅ ደግሞ በ1997 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ቁጥር 470/97 ተሽሮ መተካቱን፣ በ1997ቱ ምርጫ ሂደት ወቅት የወጣው ይህ በአዋጅ ደረጃ የወጣው ሕግ በ1998 ዓ.ም. በወጣ አዋጅ መሻሩን የተተካውም በምክር ቤቱ ደንብ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ የረቂቁን የኘሬስ ሕግ በተለይ የሌሎችንም ረቂቆች የማመንጨት የአወጣጥ ስነ ስርዓት የትኛውም ወቅት ላይ ሆነን ስንገመግምና ሕጋዊነቱንም ስንመረምር በወቅቱ ፀንቶ ሥራ ላይ ካለው ሕግ ወይም ደንብ ጋር መጣጣሙን ብቻ ሳይሆን ደንቡና ሕጉ ራሱ በሕግ አግባብ መወጣቱን ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡

በምርጫ 97 ሂደት ወቅት በተሰናባቹ (ሁለተኛው) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻ የሥራ ዘመን 11ኛ ሰዓት ላይ የወጣው፣ ክፉኛም ያወዛገበው የተሻሻለው የሕዝቦች ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 470/97ን የሻረው አዋጅ ቁጥር 503/98 ነው፡፡ የሻረውም "ምክር ቤቱ ስለአሠራሩም ስለ ህግ አወጣጡ ሂደት ደንቦች እንደሚያወጣ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 59/2 በግልፅ የተደነገገ በመሆኑ በሌሎች አገሮች እንደተለመደው የምክር ቤት አሠራር ህገ መንግሥትን መሠረት በማድረግ በደንብ መደንገግ ተገቢ በመሆኑ፣ የተሻሻለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራርና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ አዋጅ ተሰርዞ በደንብ እንዲተካ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ" ተብሎ ነው፡፡ ስለዚህም አዋጅ ቁጥር 470/1997 በአዋጅ ቁጥር 503/98 "ሙሉ በሙሉ ተሽሯል"

ኢትዮጵያ የምክር ቤቷ የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ከዓለም አቀፍ የፓርላማ መርሆዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ከሚያደርጉ የተቋቋሙ አሰራሮች ጋር ራሷን ማስተዋወቅ የሕገ መነግሥቷም አካል የአሰራርዋም የተለመደ ባሕሪ ማድረግ የጀመረችው ደርግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ በተቋጨውና በተቀለበሰው፣ ምንጊዜም እንደ አዲስ የመቀጠሉ ጉዳይ በእጅጉ እንዲደነግጥ በተደረገው በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ሕገ መንግሥት ውስጥ የተካተተው ይህ መርህ ቢያንስ ቢያንስ በፅሁፍ የሰፈረ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በነበረበት ወቅት ነው፡፡

ስለዚህም በ1948ቱ የተሻሻለው የኢትዮጵያ ሕገ መነግሥት ድንጋጌዎች መሠረት ሕግ የማመንጨት ሥልጣን የመንግሥት (የአስፈፃሚው አካል) እና የፓርላማ አባላት ነው፡፡ አገሪቷ "ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች" የሌላ አገር ልምድ የመቅሰም፣ ሌላው ቢቀር "የመቅዳት" ጥበብ ያላቸው አዋቂዎች ድሀ ያልነበረችበት ወቅት እንደነበረ ምስክርነቱን የሚሰጠው እና የሚያረጋግጠው የዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ውበት ነበር፡፡ በዚህ ሕገ መነግሥታዊ ድንጋጌ መሰረት ሕግ የማመንጨት ሥልጣን ለመንግሥቱ የሥራ አስፈፃሚ አካል እና ለፓርላማ አባላት ጭምር ቢሆንም፣ የበጀት ሕግን የማመንጨት ሥልጣንና ተግባር ግን የመንግሥትና የመንግሥት ብቻ ነው፡፡
 
አዋጅ ቁጥር 271/94 ሕግን በማመንጨት የሕግ ረቂቅ ወደ ምክር ቤቱ ማቅረብ የሚችሉት አካላትን ሲዘረዝር "አስፈፃሚ አካላት" በሙሉ ለየብቻቸው ይህ ሥልጣን እንዲኖራቸው ያደረገው ከላይ የተገለፀውን መሠረታዊ የፓርላማ አለም አቀፋዊ አሰራር ተፃርሮ ብቻ ሳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት (ኦክቶበር 13/2003) ያወጣውን ሕግ መንፈስ ከወዲሁ በሚረግጥ ሁኔታ ነበር፡፡ የ1994 ዓምቱ የምክር ቤቱ የህግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ሕግ ለእያንዳንዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ለእያንዳንዱ ተጠሪነቱ ለፓርላማ ለሆነ አካል ለፍርድ ቤት ጭምር ሕግ የማመንጨት ሥልጣን መስጠቱን አሰራር ኢ-ሕጋዊነት የዚህንም ጥፋትና ክፋት ጐልጉሎና ነቅሶ አውጥቶ ይፋ ሪፖርት ያቀረበው የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ኮንሰልታንት አድርጐ ያሰራው ሌንተር ፎር ኢንተርናሽናል ሊጋል ኮኦኘሬሽን የተባለ የኔዘርላንድስ ተቋም መጋቢት 1997 ዓ.ም. ዳጐስ ባለ መጽሐፍ መልክ አሳትሞ ባቀረበው ሪፖርት አማካኝነት ነበር፡፡
 
የማስታወቂያ ሚኒስቴር የኘሬስ ሕጉን ረቂቅ ማመንጨት አይችልም የምለው የ1994 ዓ.ም. ሕግን የሻረው ሕግ የማመንጨት ሥልጣን ካላቸው አካላት ዝርዝር ውስጥ "አስፈፃሚ አካላት" ያስወጣውና የሰረዘው የ1997 ዓ.ም. ሕግ ስላለ፤ ስለነበረ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ተቃውሞ የገጠመው የፍትህ ስርዓቱ ማሻሻያ ኘሮግራም የ1997 ዓ.ም. (መጋቢት) ሪፖርት በእጅጉ የኮነነው በዚህ መካከል የወጣውና አሁንም በሥራ ላይ ያለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መመሪያ የማይቀበለው አሰራር ቢሆንም በ1994ቱ ሕግ መሠረት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሕግ የማመንጨት ሥልጣን ሊኖረው የሚችለው "በሕግ በተሰጠው ሥልጣን ዙሪያ ብቻ" ነው፡፡

የሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት "በተሰጠው ሥልጣን ዙሪያ" የኘሬስ ጉዳይ ይካተታል ወይ የሚለው ጥያቄ መልስ በየጊዜውና በዚህ አኳያ ይህ ጥያቄ እየተነሳ መከራከሪያ እየሆነ ስለመጣ በ"አዋጅ" እና በ"ደንብ" ማሻሻያዎች በሚሰጡት የእልክ ምላሽ ማዕቀፍ ውስጥ ሊመለሱ ይገባል ማለት መልሶ ያንኑ ጨዋታ መጫወት፣ በዚህ ወጥመድ ውስጥ መውደቅ ነው፡፡

ጉዳዩን ግን የማስታወቂያ ሚኒስቴርን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጡት ልዩ ልዩ ማሻሻያ ሕጐች የተፈፃሚነት ዘመን ውስጥ ማየት ተገቢ ነው፡፡ በ1995 ዓ.ም. የማስታወቂያ ሚኒስቴር የኘሬስ ሕጉን መጀመሪያ አርቅቆ ባወጣበት ወቅት እና እስከ 1997 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚነት በነበራቸው ሕጐች መሰረት የኘሬስ ጉዳይ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥልጣን "ዙሪያ" በጭራሽ አልነበረም፡፡ የማስታወቂያ/የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ራሱ የመንግሥት አፈ ቀላጤ የመንግሥት ኮሚውኒኬተር ነው፡፡ የኘሬስ ህግ ተፈፃሚ የሚሆንበት አካል ነው፡፡ ራሱ የሚያስፈፅመው እንደ ነፃ/ኢንዲፐንደንት ሬጉሌተር ሆኖ የሚሰራበትና ይህንን ግዴታ የኘሬስ ህግን አክብሮ ከመገዛት ጋር "እያጣቀሰ" እያደባለቀ የሚሰራበት ባህሪይ ሊኖረው አይችልም፡፡

ከ1997 መጨረሻ በኋላ ባሉት ጊዜያት ውስጥ የማስታወቂያ ሚኒስቴር አወዛጋቢው የኘሬስ ሕግ የሚያስነሳቸውን ሕገ መንግሥታዊና ሕጋዊ ጥያቄዎች ለመጋተር በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥልጣን ላይ "እየተጣፉ" ወይም እየተደረቱ የመጡ በርካታ "ማሻሻያዎች" መኖርም ጉዳዩን የሚለውጠው አይደለም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሀሳቡን ያመነጨው ማንም ይሁን ማን የሚባል ቢሆን እንኳን ጉዳዩ በፍትህ ሚ/ር በኩል ሳያልፍ፣ የረቂቁ መፅደቁ የነባር እና የሌሎች ተጓዳኝ ሕጐችን መሻሻል መሻር ማጠቃለልና ማዋሀድ፣ የሌሎች አዲሱ ህጐችንና ተቋሞችን የማጠይቅ መሆኑ ሳይመከርበትና ሳይዘከርበት የሚወጣ ሊሆን አይችልም፡፡

በየትኛውም ወቅት ተፈፃሚነት በነበራቸው የኢፌዲሪ የአስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር የሚወሰኑ ሕጐች እንዲሁም አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 471/98 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የራሱ የውስጥ ደንብ እንደሚኖረው ይደነግጋል፡፡ የውስጥ ደንቡ የታተመ ባይሆንም ሕዝብ ያውቀዋል ባይባልም እያንዳንዱ ሚኒስቴር በሕግና የፍትህ ሚኒስቴር ዴስክ ወይም አግባብ ባለው የምክር ቤቱ ኮሚቴ በኩል ሳያልፍ፣ ባጠቃላይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሳይወያይበት ወደ ፓርላማ መሄድ አይችልም፡፡

የኘሬስ ሕጉን ረቂቅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አይቶታል ወይ የሚለውን ጥያቄ የምመልሰው በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ለ"ውይይት" የቀረበው የረቂቁ ሕግ የመጨረሻ ቅጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጥቅምት 96 የውስጥ ደንብ አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ ቁጥር (3) የሚጠይቀውን የይዘት፣ የቋንቋም ሆነ የመልክና የቅርጽ ብቃት የማያሟላ ስለመሆኑ በእርግጠኝነት በመመስከር ነው፡፡

ረቂቁ ፓርላማ እንዲቀርብ የተስማሙት ፓርቲዎች ከሁሉ አስቀድሞ ረቂቁ ሕግ የአገር ሕግና ደንቦችን አሟልቶ እነዚህ ደንቦች በሚጠይቁትና የግድ በሚያደርጉት ሂደት ውስጥ አልፎ ስለመምጣቱ ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጥቅምት 96 የውስጥ ደንብ የሚጠይቀውን መነሻ ቅድመ ሁኔታ ያላሟላ ረቂቅ ፓርላማ ይቀርብ ዘንድ የሚያስችለው የአካሄድ ብቃት አለው ከማለት የበለጠ "የትም ፍጭው" ፖሊሲ የለም፡፡

 
< Prev   Next >