| በሰመራ የሚገነባው ደረቅ ወደብ... |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
|
በሰመራ የሚገነባው ደረቅ ወደብ የውጭ ምንዛሪን ያድናል
በሰመራ ከተማ የሚገነባው የደረቅ ወደብ ከጎረቤት አገሮች ጋር ካለው ቅርበት አኳያ እቃዎችን በፍጥነት ወደ አገር ውስጥ በማመላለስ የውጭ ምንዛሬን ለማዳን እንደሚረዳ ተጠቆመ፡፡ በሀገሪቱ ሁለተኛ የሆነውን የደረቅ ወደብ በሰመራ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለማስገንባት የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ጋር የግንባታ ኮንትራት በተፈራረመበት ወቅት የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው መንግሥቴ እንደገለፁት፤ በ100 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባው የሰመራ ደረቅ ወደብ ለሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚያገለግል ብቻ ሳይሆን ከጐረቤት ሀገሮች ወደቦች ጋር ካለው ቅርበት አኳያ ዕቃዎችን በፍጥነት አመላልሶ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ይረዳል፡፡ የወደቡ ግንባታ የውጭ ምንዛሬን ለማዳን እና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለፁት አቶ ጌታቸው ደረቅ ወደቡ ከሚኖረው ሀገራዊ ፋይዳ አንፃር የኮንስትራክሽን ድርጅቱ የግንባታ ሥራውን በውሉ መሠረት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል፡፡ የሀገሪቱን ገቢና ወጪ ንግድ የተቀላጠፈ ለማድረግና የተጀመረውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለመደገፍ እንዲሁም የትራንዚት ትራንስፖርትን ውጤታማ ለማድረግ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በ1998/99 በተደረገው ጥናት መሠረት የደረቅ ወደብ ልማትን ለማስፋፋት የታቀደ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር በሞጆ እና በሰመራ በቀጣይም እንደ አስፈላጊነቱ በተመረጡ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ ወደቦች እንደሚገነቡ ታውቋል፡፡ የሞጆው የደረቅ ወደብ ግንባታ በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ እየተካሄደ ከመሆኑም በተጨማሪ ከግንባታው ጎን ለጎን የደረቅ ወደቡን የአስተዳደርና የአደረጃጀት ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የሰመራ የደረቅ ወደብን ለመገንባት የአፋር ክልል መስተዳድር በቂ ቦታ ከመስጠቱም በላይ ለደረቅ ወደቡ አገልግሎት የሚውል የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር እንደሚተባበር ቃል መግባቱ የግንባታውን ሥራ የተቀላጠፈ ለማድረግ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ የኮንትራት ውል ስምምነቱ ዝርዝር ዲዛይን ሥራ፣ የአጥር ግንባታ፣ የመጋዘን፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የኮንቴነር ማከማቻ ዴፖ፣ መጠበቂያ ማማ፣ እንዲሁም ለደረቅ ወደብ ተጓዳኝ አገልግሎት ለሚሰጡ እንደ ጉምሩክ፣ ባንክ፣ ኢንሹራስና ለመሳሰሉት ተቋማት መገልገያ የሚውል ቢሮዎች ያጠቃልላል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ግንባታው የሚጠናቀቀው በጥር ወር 2001 ዓ.ም ሲሆን የኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅም በጊዜ ገደቡ ሥራውን አጠናቀው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው መንግሥቴ እና የኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ጋዲሣ ናቸው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |