| አሜሪካ ለደሃ አገሮች የምግብ እርዳታ... |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
|
አሜሪካ ለደሃ አገሮች የምግብ እርዳታ 770 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል
በጋዜጣው ሪፖርተር በምግብ ዋጋ መጨመር በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቁ ላሉ ታዳጊ አገሮች አሜሪካ ለምታደርገው የምግብ እርዳታ ለማድረግ 770 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ገልፀዋል፡፡ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን የገለፁት ፕሬዚዳንት ቡሽ እንደ ሃይቲና ቡርኪናፋሶ ባሉ ድሃ አገሮች ይህ የምግብ ዋጋ መጨመር አለመረጋጋትን እንዳስከተለ አመልክተዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ለታዳጊ አገሮች በሚደረገው እርዳታ ግንባር ቀደም እንደምትሆን ቃል ገብተዋል፡፡ “በአዲሱ አለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ረሀብን በመዋጋት በሚደረገው ትግል አሜሪካ ግንባር ቀደም እንደምትሆን ቃል እገባለሁ” ብለዋል፡፡ የስንዴ፣ የሩዝና የሌሎች የምግብ እህሎች ዋጋ እንዲሁም የነዳጅ ዋጋ መጨመር በአለም ዋነኛ የምግብ እርዳታ ሰጪ የሆነችውን አሜሪካ በጀት ትኩረት እንደሳበ ተመልክቷል፡፡ ለምግብ እርዳታና ለልማት ፕሮግራሞች በ2007 የበጀት ዓመት ኮንግረሱ ተጨማሪ የ770 የአሜሪካ ዶላር እንዲያፀድቅላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን በዋይት ሀውስ ለተገኙ ጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ይህ እንዲሳካ የኮንግረሱ ማጽደቅ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል፡፡ ቡሽ የጠየቁት 770 የአሜሪካ ዶላር ለድንገተኛ የምግብ እርዳታ፣ ለምግብ ግዥና ሰነድ እንዲሁም ለምግብ ዋስትና የሚውል ገንዘብ እንደሚያጠቃልል ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል፡፡ ታዳጊ አገሮች ራሳቸውን የመመገብ አቅማቸውን ለማዳበር እንደሚረዳ ከፍተኛ የአሜሪካ የበጀት ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡ ገንዘቡ በኮንግረሱ ከፀደቀ በ2009 አሜሪካ ለአለም የምግብ ዋስትና የምታወጣውን ገንዘብ ወደ 2.66 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ያደርገዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |