| እውነተኛ ያልሆነ የአቅርቦት እጥረት... |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
|
እውነተኛ ያልሆነ የአቅርቦት እጥረት የሚፈጥሩ ነጋዴዎችን መቆጣጠር ያስፈልጋል
በቤዛዊት ሥዩም በሰዓታት ውስጥ በምርቱ ላይ ምንም አይነት ለውጥ ሳይኖር አርቲፊሻል እጥረት በመፍጠር በዋጋ ላይ ለውጥ የሚያደርጉት ነጋዴዎችን የንግዱ ማህበረሰብ ስለሚያውቃቸው ሊቆጣጠርና ትኩረት ሰጥቶ ሊለያቸው እንደሚገባ ተገለፀ፡፡ የኢትዮጵያ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ህዝባዊ የምክክር መድረክ ባለፈው ሐሙስ ሚያዚያ 23 ቀን 2000 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንዲሁም ዘላቂ የመፍትሄ ሃሳቦች በሚል ርዕስ በተካሄደ ውይይት ላይ የመድረኩ ምክትል ሰብሳቢና የተስፋ ድርጅት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሚናስ ኅሩይ እንደተናገሩት በዋጋ ንረቱ አነስተኛ አቅም ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ ወገናዊ የንግድ ማህበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ የንግዱም ህብረተሰብ እውነተኛ ያልሆነ የአቅርቦት እጥረት የሚፈጥሩና ዋጋ የሚጨምሩትን መቆጣጠር አለበት፡፡ የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ተሾመ በየነ በበኩላቸው ነጋዴዎችን ከዋጋ ግሽበት ጋር ማገናኘት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረው ስለ ማህበረሰብ እያሰቡ መነገድ አጠቃላይ ንግዱን እንደሚጎዳ ተናግረዋል፡፡ በዋጋ ንረት ላይ ጥቂት ነጋዴዎች ጫና ፈጥረዋል ቢባልም ብዙ ነጋዴዎች ባሉበት ሁኔታ ጥቂት ነጋዴዎች ችግር እንደማይፈጥሩ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ሚናስ በበኩላቸው በነጋዴዎች መካከል ተገቢ ውድድር በመፍጠር አነስተኛ አቅም ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዳይጎዱ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ለመርዳት በመንግሥት እየተደረገ ያለው ድጎማ ተጎጂዎቹን መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበትና የተለየ ድጎማ የሚያስፈልጋቸውን መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ በመከፋፈል ላይ ባለው ስንዴ አንዳንድ ወገኖች አለአግባብ የሚያገኙበት ሁኔታ ገልፀው አነስተኛ አቅም ያላቸው የተለየ ወረቀት እንዲያገኙ በማድረግ ችግሩን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ከሚያካሂደው የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አኳያ በንግድ ውስጥ ጣልቃ ካልገባ ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን ቤት፣ ጤና፣ ትራንስፖርትና ትምህርትን መደጎም እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ ገበሬዎቹ ምርት በሚጨምር ጊዜ በሚፈጠር የዋጋ መቀነስ እንዳይጎዱ በእህል ንግድ ድርጅቶች አማካይነት ገበያውን የማረጋጋት ሥራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ በገጠር ለድህነት ቅነሳ በከፍተኛ ትኩረት ሰፊ ስራ መሰራቱን አስታውሰው በገጠር ያለው ድህነት ሲስተካከል ለከተማ ሸማች ብዙ ትኩረት እንዳልተሰጠ ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአለም ካለው የምግብ ፍላጎት መጨመር፣ ትልልቅ አገሮች ድጋፍ መቀነሳቸው እርዳታ መቀነሱና በዚህ ዓመት በታየው የዝናብ መዛባት የኑሮ ውድነቱ ሊያባብሰው ስለሚችል ችግሩን ለመወጣት የአመለካከትና የልምድ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተገል..ል፡፡ መንግሥት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ለመደጎም በሚያደርገው ጥረት የወጪ ጫናና የንግድ መዛባት ሊፈጥር ቢችልም ችግሩ ከመባባሱ በፊት ከተለመደው ውጪ ፈጠራና ልዩ ትብብር የሚጠይቅ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በአጭር ለመክበር የሚፈልጉ አላስፈላጊ ውዥንብር የሚፈጥሩ ነጋዴዎችን የንግዱ ማህበረሰብ ሊቆጣጠራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት በምርት ወቅትና ከምርት በኋላ ዋጋ የሚለዋወጥበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ብዙ የዋጋ ለውጥ አለመኖሩ በምርት መጠን ላይ ጥርጣሬ እንደፈጠረ ተገል..ል፡፡ ንግድ ነጋዴ ጨምሮ ለመሸጥ ሸማች ቀንሶ ለመግዛት በሚያደርግ ድርድር የሚካሄድ በመሆኑ በአዘኔታ የሚካሄድ ባይሆን የሁለት ወገን ውሳኔ የሚጠይቅ መሆኑን አቶ ተሾመ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ የነፃ ኢኮኖሚ ሥርዓትን የሚያደናቅፉ በነጋዴዎች መካከል ያለ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር፣ ገበያን አላግባብ መጠቀምና አላስፈላጊ ተጽዕኖ በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ ብቻ ቁጥጥር መደረግ ቢኖርበትም ዋጋን እንዲቆጣጠሩ የተቋቋመው ግብረ ሃይል ለንግድ ያላቸው እውቀትና ለመረዳት ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ሕጉን እንዲረዱት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዋጋ ንረቱን በነጋዴው የንግድ ባህልና በፈጠሩት ግለኝነት እንደሆነ ቢገለፅም ነጋዴዎች በዋጋ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር መመካከር አስፈላጊ ሲሆን ይህ ብዙ የሚታይ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ የገበያ ሥርዐቱን ካለፈው ጊዜ ጋር ማነፃፀር እንደማይቻል የገለፁት አቶ ተሾመ የገበያ ተጠያቂነት፣ የተሻለ የገበያ ሥርዐት፣ መሰረተ ልማትና መረጃ ከበፊቱ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የንግዱ ክፍለ ኢኮኖሚ የዋጋ ንረት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥረው ጥቂት ነጋዴዎች ገበያን ሲቆጣጠሩ እንደሆነ ሆኖም ብዙ ነጋዴዎች መኖራቸውን ገልፀው በአዲስ አበባ ብቻ ከ2000 በላይ የእህል ነጋዴ ወፍጮ ቤትና አቅራቢዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለማስተካልና ያለውን የምግብ እህል እጥረት ለማርገብ የአቅርቦት ማበረታቻ ማድረግ እንደሚገባው የገለፁት አቶ ተሾመ ዋጋ ሲጨምርና ሲቀንስ ሕብረተሰቡ እንዳይጎዳ የሚቆጣጠርበት የግብርና ምርት ክምችት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ ነጋዴዎች በመተባበር ዋጋን መወሰን የሚችሉት የገበያ መረጃ በበቂ ሁኔታ ሳይኖር እንደሆነ ገልፀው፣ በገበሬውም ሆነ በነጋዴው መካከል የተሻለ የመረጃ ፍሰት እንዳለ ገልፀዋል፡፡ በማከማቸት ዋጋን ይጨምራሉ በሚል ስጋት በነጋዴዎች ላይ እየተደረገ ያለው ቁጥጥር ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነጋዴዎቹ አከማችተው ገበያውን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት ለሚቀመጠው እቃ የሚመጡትን አደጋዎች ኪሣራና የመጋዘን ወጪ የሚጋፈጥ መሆኑን ገልፀው የንግድ ሥራ አንዱ አካል በመሆኑ ወቀሳ ሊያስከትል እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ ሸማቾች ዋጋ ይወደዳል ብለው ካሰቡ ገዝተው የሚያከማቹበትን ሁኔታና የምግብ እህሎች የዋጋ ንረት ገበሬው ዋጋ እስኪጨምር ምርት በመያዙ /በመከማቸቱ/ የመጣ ነው የሚለው በበጎ ተይዞ በነጋዴው ላይ ትኩረት መደረጉ ነጋዴውን ሊያሸማቅቅ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በበፊት ጊዜያት ተሸማቆ ቆይቶ አሁን እያንሠራራ ባለበት ሁኔታ የኑሮ ውድነቱን በማስተካከል ጫና መፍጠር ንግድና ኢኮኖሚውን እንደሚጎዳ ተናግረዋል፡፡ ግሽበት የአገር ችግር በመሆኑ ቋሚ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ያህል ባይሆንም ነጋዴውን እንደ ሸማች ሲጎዳ የሰራተኛና የነዳጅ ዋጋ ስለሚጨምር በተወዳዳሪነቱ ላይ ጫና እንደሚያሳድርበት ተናግረዋል፡፡ ነጋዴ በውድድር እንዲያምን፣ የሸማቾች ማኅበር በንግድ ሕግ አሠራር ላይ ተገቢውን መረጃ መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |