|
ታሪክና አፈ ታሪክ - በገድለ አበበ ቢቂላ |
|
|
|
Sunday, 04 May 2008 |
|
በሔኖክ ያሬድ
ፋሺስት ኢጣሊያ ሚያዚያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባን የተቆጣጠረችበት ዕለት ነው፡፡ መሪዋ ቤኔቶ ሙሶሎኒ ደስታውን ከገለጸበት መንገድ አንዱ በሮም ከተማ በኮንስታንታይ ቅስት አካባቢ ባሉ ድንጋያማ ቅጥር የአዲስ አበባ መያዝን የሚያመለክት ጽሑፍ መኖሩ ነው፡፡ ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላ በ1953 ዓ.ም ሮም ታላቁን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አዘጋጀች፡፡ ነፃይቱ ኢትዮጵያም ተሳተፈች፡፡ መነሻው በጥንታዊቷ ግሪክ ከነበረው ማራቶን በተባለው ስፍራ ከተካሄደው ጦርነትና ከተገኘው ድል ብሥራት ጋር የተያያዘውን የማራቶን ሩጫ አንድ ጥቁር በድል አድራጊነት ፈጸመ፡፡
ከመወዳደሪያው ባሻገር በቅርበት (ከአንድ ማይል ያነሰ ርቀት) ላይ የነበረውን የአክሱም ሐውልት እየሮጠ የተመለከተው ኢትዮጵያዊው ባለ ድል አበበ ቢቂላ ነው፡፡ ከተራራማዋ አገር የመጣው የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ሠራዊት ባልደረባ አበበ በሮም ማሸነፍ እንደ አንድ ታሪካዊ በቀል ይቆጠራል ተብሎም ተጽፎለታል፤ ተነግሮለታል፡፡ የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን አንዱና ቀዳማዊ ገድል የፈጸመበት ነው፡፡
48ኛው ዓመት ላይ ይህንና ሌሎች ገድሎቹን የሚያሳይ ዐውደ ርዕይ ባለፈው ሰኞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ቀርቧል፡፡
በኩር (ዘሌጀንደሪ) አበበ ቢቂላ በዐውደ ሕይወቱ ያተኮረ የምስል ስብስብ ለእይታ መብቃቱ ብዙዎችን ያስደሰተ ነው፡፡ ዐውደ ርዕዩ፣ ሚያዚያ 1953 አቴን በተካሄደውና ከሮም ኦሊምፒክ በኋላ በጫማ ተወዳድሮ ያሸነፈበት 48ኛ ዓመት ላይ መዘጋጀቱ ግጥምጥሙ ታሪካዊ ያሰኘዋል፡፡ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2000 ዓ.ም ድረስ ለተመልካች ክፍት በሚሆነው የፎቶ ግራፍ ዐውደ ርዕይ በባህል፣ በስፖርት፣ በኦሊምፒክ ዙሪያ ታሪካዊ ክንውኖች የሚያሳዩ ልዩ ልዩ ፎቶግራፎች ቀርበዋል፡፡
አበበ የአትሌቶች በኩር መሆኑ የመጀመሪያ ድሉም በባዶ እግሩ በመሮጥ የተፈጸመ በመሆኑ ክንውኑን ከታሪካዊ እውነታ ባሻገር አፈታሪክ (ሌጀንድ) ውስጥም እንዲገባ አስችሎታል፡፡ ኅብረተሰቡ የራሱን ታሪክ ፈጥሮለታል፡፡ ጀግንነቱን ለማጉላትና ለማወደስ ከተፈጠሩት አፈታሪኮች መካከል በባዶ እግሩ የመሮጡ ምክንያትና ሮም ከነበረው የአክሱም ሐውልት ጋር የተያያዙ ይገኙበታል፡፡
አበበ "እኔ በባዶ እግሬ የምሮጥበት ምክንያት ጫማ አጥቼ ሳይሆን ኢትዮጵያ አገሬ ከጥንት ጀምሮ የጀግንነት ሙያ በድፍረትና በቆራጥነት የምትፈጽም መሆኑን ለዓለም በይፋ ለማሳወቅ ነው" ማለቱ በዘመኑ የተወሳ ነው፡፡
በአፈታሪኩ እንዲሁም ሰው እየተቀባበለ አወጋው፡፡ "አበበ ቢቂላ በሮም የማራቶን ሩጫውን ሲጀምር ጫማ ተጫምቶ ነው፡፡ ሩጫውን እያጋመሰ ሳለ እንዴ" የአገሬን ዳገት ቁልቁለት የወጣሁት፣ የወረድሁት በባዶ እግሬ አይደለም እንዴ? ሶላቶ ጣሊያን ባለበት አገር ጫማዬን አውልቄ ነው የምሮጠው ብሎ አሽቀንጥሮ ጥሎ በመሮጥ ድሉን ጨበጠ" ይላል፡፡ አሁንም በተለይ ወግና ተረት በሚያተኩሩ ዘንድ ይወሳል፡፡ አበበ ከአሰልጣኙ ስዊድናዊው ኦኒ ኒስካነን ጋር ከውድድሩ ቀናት በፊት የመወዳደሪያው ሥፍራ መመልከቱ፣ በአቅራቢያው የሚገኘውን ታሪካዊው የአክሱም ሐውልትን ማስተዋሉ እውነት ነው፡፡
"አበበም አክሱም ሐውልቱን ተመልክቶ ወኔው ተቀሰቀሰ፤ የዘመኑን ታላቅነትና ኃያልነት አስተዋለ፤ ከኢትዮጵያ ተዘርፎ ሮም መቆሙ ቆጭቶታል፤ አስከፍቶታል፡፡ ግን እንደ አክሱም የዓለም ገናና ታሪክ እርሱም መግነን፣ መንገሥ ሽቷል፡፡ እጅ ላለመስጠት፣ ላለመረታት ቃል ገባ" አፈታሪክ ነው፡፡ ድሉን ዘከረ፡፡ 11 ቁጥር መለያ ሹራቡን ለብሶ ከነፈ፡፡
የባዶ እግረኛውን የሮም ድል 25ኛ ዓመት (ጳጉሜን 3 ቀን 1977 ዓ.ም) በዘከረበት "የብር ኢዮቤልዮ አበቦች" በተሰኘው ድርሳኑ ሔኖክ ያሬድ እንደጻፈው ኢትዮጵያ ድንቅ የሆነ አዲስ "ድርሳነ ማራቶን" አቀለመች፡፡ ብዙዎች ማራቶንን ቢያሸንፉም እንደ አበበ ቢቂላና አበበ ዋቅጅራ (እርሱም በባዶ እግሩ ነው የሮጠው) ለእይታ የበቃ፣ ለድርሳን ያመረቃ ተግባር ያከናወነ የለም፡፡ ድሉም ከሞት ነፃ (እንደ ሬዲፒዲስ ያይደለ) በመሆኑም የአፍሪቃን ስፖርት ገጽታ ጎልቶ እንዲታይ አደረገው፡፡ የጊዜው ርዝመት ለወርቅ ኢዮቤልዩ ሁለት ዓመት የቀረው የሮም ማራቶን ውድድር ምን ይመስል ነበር? ዘመኑ ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም ቅዳሜ ከቀትር በኋላ ነበር፡፡ አስቸጋሪ የነበረው ሙቀት ሻል አለ፡፡
በኦሊምፒክ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድር አዘጋጆች የማራቶን ውድድርን ምሽት ላይ እንዲከናወን አደረጉ፡፡ ውድድሩም የሚካሄደው ከርእሰ ከተማዋ ተነስቶ በኦፒየን አቅጣጫ አድርጎ መድረሻው የኦሊምፒክ ችቦ በሚንቦለቦልበት በኮንስታንታይ ሥር ነበር፡፡ ቅስቱ ላይ በሞሶሎኒ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ጽሑፎች ይታያሉ፡፡ ከእነዚህም ጽሑፎች ውስጥ የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ መያዝዋን የሚገልጽ ጽሑፍ ይታይ ነበር፡፡ የውድድሩም ውጤት ሲገመት ከዚያች ተራራማ አገር የመጣ ሰው ሮም ላይ በባዶ እግሩ ተወዳድሮ ማሸነፉ እንደ አንድ ታሪካዊ በቀል ሊቆጠር ይችላል፡፡
ውብ በሆነችው በካፒቶሊን አደባባይ የማራቶን ተወዳዳሪዎች ተሰበሰቡ፡፡ ልክ 11 ሰዓት ተኩል ላይ ውድድራቸውን ጀመሩ፡፡ ዓለም ሁሉ ዓይኑን ያሳረፈው በሞሮኳዊው አብድሲየም ራህዲ ላይ ነበር፡፡ ላልታወቀው ጥቁር አፍሪካዊ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ምንም ዓይነት ጫማ አልተጫማም፡፡ የእርሱ መሮጫ፣ ያች የተፈጥሮ ጸጋው እግሩ ነች፡፡ የአገሩን ልጅ አበበ ዋቅጅራን ጨምሮ፡፡
"በባዶ እግሩ በእውነት እናስብ" ከ40 ኪ.ሜ በላይ መሮጥ ጨርሶ ያልተለመደ፣ ከእነርሱ በፊትም ሆነ በኋላ ተደርጐም፣ ተተርኮም የማይታወቅ" እንዳለው የኦሊምፒክ ሪቪው አዘጋጅ፡፡
ጀምበሯ ጠልቃ ጨለምለም ባለበት ጊዜ የውድድሩ ፍጻሜ ቀረበ፡፡ ጭለማ ቢሆንም የፁግ (ጭራሮ መሰል መብራት) እና የመብራቶች ብርሃን የኮልሴሙን መንገድ ከማመልከታቸውም በላይ የመግቢያ መስመሩን ጥርት አድርገው ያሳያሉ፡፡
ሁለት አፍሪካውያን አበበ ቢቂላና ራህዲ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች በመራቅ ከመነሻው ስፍራ አካባቢ ደረሱ፡፡ የፍጻሜው መግቢያ መስመር ላይ በ150 ያርድ ርቀት አበበ ተፎካካሪውን ሞሮኳዊ ቀድሞት በመግባት ለስድስት ዓመታት ያልታየ አዲስ የኦሊምፒክ ሪኮርድ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16.2 ሰኮንድ በሆነ ጊዜ በመስበር አስመዘገበ፡፡ ሌላኛው ባዶ እግረኛ አበበ ዋቅጅራ እስከ 30ኛው ኪ.ሜ ከአስሩ የመጀመሪያ አትሌቶች ሳይደባለቅ ቆይቶ ማጠቃለያ ላይ 7ኛ ሆኖ መግባቱም እንደ ትንግርት ታየ፡፡
የወቅቱ የነአበበ አሰልጣኝ ማዦር ኦኒ ኒስካነን ትዝታቸውን ሲያወጉ "አበበ ዞሮ ከመጣና የጣሊያኑ ዶክተር ዳሙንና የልቡን ትርታ ከመረመረ በኋላ ፣ፋንታስቲኮ፣ ብሎ ሲደነቅ ጤነኛ መሆኑን ተገነዘብኩ ካሉ በኋላ ሐኪሙ ለመሆኑ ከየት ነው የመጣው ሲለኝ፣ ከኢትዮጵያ ስለው ፣ኦኦ አሁን ደግሞ በሮም አሸናፊነቱን አስመሰከረ፣ በጣሊያን ሕዝብ፣ አለ መላጣ ራሱን እየነቀነቀ ዶክተሩ""" ብለዋል፡፡
በ1954 ዓ.ም በዚያን ጊዜው በብርሃንና ሰላም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ማተሚያ ቤት የታተመው አጀንዳ የንጉሠ ነገሥቱን ታሪካዊ ገጽታዎች በዘረዘረበት ክፍል እንዲህ ተጽፏል፡፡
መስከረም 5 ቀን 1953 ዓ.ም ከማራቶን ውድድር ረሮም ኦሊምፒክሪ አሸናፊ ኹኖ የተመለሰውን አበበ ቢቂላን በገነተ ልዑል ቤተመንግሥታቸው ተቀብለው እጅ አስነስተው የኢትዮጵያን የክብር ኮከብ የፈረሰኛ ደረጃ ኒሻን ሸለሙት፡፡
የበርሊን ማራቶን መጽሔት ዘጋቢ አበበ ቢቂላ የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን ካሸነፈ ወዲህ የማራቶን ሩጫ በ2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ የማጨርስ ቢኖር ሻምፒዮን ይባላል፡፡ በ2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ የሚፈጽም ከተገኘ ደግሞ ድንቅ ሻምፒዮን ይባላል፡፡ አበበ ቢቂላ ግን በቶኪዮ ኦሊምፒክ (1957) 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11.2 ሴኮንድ በማምጣቱ ምን ብዬ እንደምለው ቃላት አጥቼለታለሁ ብሎታል፡፡
አበበ ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከእርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድል ፈጸመ፡፡ ከትርፍ አንጀት ቀዶ ሕከምናው ሳያገግም ባሸናፊነት የገባበት ሰዓትም በዘመኑ እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባሲል ሔትሌይ በ2 ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሰኮንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ሰዓት (ክብረ ወሰን) በ1 ደቂቃ 43 ካልዒት (ሰኮንድ) 8 ሳልሲት (ማይክሮ ሰኮንድ) የሰበረበት ነው፡፡
"እንደ በረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ፣ ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ" ብለው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914 - 1979) ተቀኝተውለታል፡፡
ለአፈታሪክነት፣ ለባለታሪክነት ገድል የበቃው አበበ የወርቅ ሜዳሊያውን በተሸለመበት ጊዜ አንድ ያልተጠበቀ ከዚያ በፊትም ያልታየ ሌላ አስደናቂ ነገር ተከስቷል፡፡ አበበ ቢቂላ በሮም ከቶኪዮ በኋላ ማሞ ወልዴ በሜክሲኮ በ1961 ላይ ሲያሸንፉ የተዘመረላቸው፡-
"ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ፣ ባምላክሽ ኃይል በንጉሥሽ" ተብሎ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር የጃፓን ባለሥልጣኖችም ሆኑ የሙዚቃ ባንዱ አያውቁትም ነበር፡፡ ዘየዱ፤ የማርሽ ባንዱ አጋጣሚውን ተጠቀመ፡፡ የጃፓንን ሕዝብ መዝሙር ለኢትዮጵያ ድል ማብሰሪያ አደረገው፤ ጃፓናውያኑም ፈነደቁ፡፡ 17 ቁጥር መለያን ያጠለቀው አበበም በጃፓን ሕዝብ ልቦና ውስጥ ታተመ፡፡
አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከ23 ዓመት በፊት እንዳሉት "".አበበ በድጋሚ በማሸነፉ በጃፓን ሕዝብ ለዘለዓለም የማይረሳ ትዝታን ትቷል፡፡ ዛሬም በጃፓን እንደጣዖት ይመለከቱታል፡፡ ማራቶን በጃፓን ውስጥ እንዲህ ተወዳጅ ሊሆን የቻለው ከአበበ ቢቂላ ድል በኋላ ነው፡፡ አሁንም ይኸው መንፈስ ቀጥሏል፡፡ ከጃፓኑ ገድል የወጣም አፈታሪክ አለው፡፡
ከዘጠኝ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውን ፒኮክ መናፈሻ ወደ ኢትዮ-ጃፓን መናፈሻ በመለወጥ ለአበበ ቢቂላ የመታሰቢያ ሐውልት እንደሚቆምለት ተነግሮ የነበረው ሁኔታ ከምን ደርሶ ይሆን?
በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ስፖርትና ኦሊምፒክ መሪዎች ዘመን ለአበበ ቢቂላ መዘከሪያ ለድሎቹ መታወሽያ ይሆን ዘንድ በአዲስ አበባ ስታዲየም ምዕራባዊ በር 11 ቁጥር መግቢያ አጠገብ የተተከሉት ምስሎቹስ የት ደረሱ?
የሻምበል አበበ ቢቂላ አንፀባራቂ ድሎች ለአፍሪካውያን በፋና ወጊነት ጠቅሟቸዋል፡፡ በኩራችን ብለውም ሰይመውታል፡፡ አዲስ አበባ ያዘጋጀችውን 16ኛውን የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አጋጣሚን ምክንያት በማድረግ በ50 ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ አኩሪ ታሪክ የፈጸሙ አትሌቶች ሲሸለሙ ዋነኛው ተሸላሚ አበበ ቢቂላ ነበር፡፡ "የአፍሪካ ማራቶን አባት" ተብሎም በዶክመንታሪው ፊልም ላይ ተሰይሟል፡፡ ታላቁን ሽልማት ልጁ የትናየት አበበ ቢቂላ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እጅ ተቀብሏል፡፡
አፍሪካውያን ለአበበ ያላቸው ፍቅርና አክብሮት እስከ አይባልም፡፡ ዘንድሮ 16ኛው ላይ የደረሰው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴኔጋል መዲና በዳካር በ1971 ዓ.ም ሲጀመር ወደ ዳካር ስታዲየም የሚያስገባውን መንገድ "የሻምበል አበበ ቢቂላ ጎዳና" በማለት መሰየሙ ይታወሳል፡፡
አበበ ከአፈታሪክ ሌላ በሕዝባዊ ዘፈንም ይነሳል፡፡ አንዱ ከስመጥሩ ድምፃዊው ጥላሁን ገሠሠ ጋር የተዛመደበት ነው፡፡ "አበበ ቢቂላ ያገባሻል ጥላሁን ገሠሠ ይድርሻል፡፡" ይሰኛል፡፡
በ1960ዎቹ ሲዘፈን የነበረው "ማራቶን ማራቶን፣ ማራቶን ልዕልቷ አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ" ኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ ሜክሲኮ ላይ በማሞ ወልዴ የማራቶንን ድል ከተቀዳጀች በኋላ የተዜመ ነበር፡፡ ገድለ አበበ ቢቂላ ታሪካዊ የቁጥርና የቀን መገጣጠሞችንም ይዟል፡፡ አበበ ሮም ላይ ያጠለቀውን 11 ቁጥር መለያ ቶኪዩ ላይ በ17 ቁጥር ቢለውጠውም የሮጠበት ቀን 11ኛ (ጥቅምት) ቀዶ ሕክምናውን ረቡዕ (መስከረም 6) ሲያደርግ ድሉን ደግሞ ረቡዕ (ጥቅምት 11) ተቀዳጀ፡፡
አበበ በሮም ማራቶን ለድል እየገሰገሰ ሳለ አንዲት ጣሊያናዊት "አይ ላቭ ዩ" ስትለው፣ "የላቡን ነገር ተይው" ማለቱ ሌላው የአፈታሪክ ገጽታ ነው፡፡ |