Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ልጅም ሚስትም?
ልጅም ሚስትም? Print E-mail
Sunday, 04 May 2008
በትዕግሥት ዘሪሁን

የቤተሰቡ ስድስተኛና ብቸኛ ሴት ልጅ ናት፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ በእናቷና አባቷ መካከል ስምምነት እንደሌለ ትናገራለች፡፡ የጭቅጭቅ ኑሯቸው የተለመደ ቢሆንም አንድ ቀን ግን እናታቸው ቤቱን ጥላ እንደወጣች ታስታውሳለች፡፡ ከዚያ በኋላ ኑሯቸው ተቀየረ፡፡ አባት ከድሮው በባሰ እየሰከረ ይገባል፡፡ እቤቱ ውስጥ ያለው ኃላፊነት በብዛት በወቅቱ 15 ዓመት ባልሞላት ይህችው ታዳጊ ትከሻ ላይ ወደቀ፡፡ ተመላላሽ ሠራተኛ ቀጥረው የሚያሰሩ ቢሆንም የሚያስፈልጉ ነገሮችን መገዛዛትና እናቷን ተክታ ቤቱን መቆጣጠር ነበረባት፡፡ ሥራ መሥራት ግን አትችልም፡፡ "ቤት መጥረግ እንኳን የለመድኩት ስምንተኛ ክፍል ስደርስ ነው" ትላለች፡፡

 

ታሪኳን ያጫወተችንን ታዳጊ ያገኘናት መተሃራ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ተቀጥራ ስትሰራ ነው፡፡ የ17 ዓመቷ ታዳጊ ስሟን መግለፅ ባትፈልግም ከቤቷ ወጥታ ወደ ቡና ቤት ያመራችበትን ምክንያት አልደበቀችንም፡፡

እናቷ ቤቱን ለቃ ከወጣች በኋላ የቤቱን ኃላፊነት የተሸከመች ቢሆንም እያደር ግን ከአቅሟ በላይ እንደሆነባት ትናገራለች፡፡ አባቷ ሰክሮ ሲመጣ እናቷን ተክታ መደብደብ ጀመረች፡፡ በሰከረ ቁጥር ሌሊት እየገባ በቦክስ እየመታ ያሰቃያት እንደነበር  የፊቷን ጠባሳ በጣቷ እየጠቆመች አሳይታናለች፡፡

በዚህ ብቻ አላበቃም እሷ እንደምትለው ገላዋን እያጠበ በእንክብካቤ ያሳደጋት አባቷ በ15 ዓመቷ አስገድዶ ደፍሯታል፡፡ "በጣም አለቀስኩ፡፡ በጊዜው መጮህ እንኳ አስፈርቶኝ ዝም አልኩ፡፡ የተፈፀመብኝን ለማን እናገራለሁ፤ አሰላ የምትኖረው አያቴ? እሄዳለሁ የሚል እቅድ ነበረኝ" ታዳጊዋ የተፈፀመባትን በደል በውስጧ አምቃ ከመቀመጥ ውጭ ሌላ አማራጭ እንዳልነበራት ትናገራለች፡፡ አባቷ ድርጊቱን የፈፀመው በስካር መንፈስ ነው እያለች በማሰብ ውስጧን ለይቅርታ ብታዘጋጅም በማግስቱ "የብር አምባር ጥሎሽ" ሳይሆን አይቀርም የአንገትና የጆሮ ወርቅ ገዝቶ አመጣላት፡፡ በተደጋጋሚ ከእሷ ጋር ወሲብ መፈፀሙ ምንም ማለት እንዳልሆነ ያስረዳት እንደነበርና እሷም ነገሩን ቀለል አድርጋ ማየት እንደጀመረች አልደበቀችም፡፡

"ከተማሪዎች እንዳታንሺ እያለ በጣም የሚያማምሩ ልብሶችን ይገዛልኛል፡፡ እንደዚያ ባደረገ ቁጥር ለእኔ ያለው ፍቅር እየጨመረ መጣ፡፡ ወንድሞቼ ምስጢሩ ባይገባቸውም ለእኔ ያለው ፍቅር ይገርማቸው ነበር" ትላለች፡፡

ታዳጊዋ እቤት ውስጥ ያላት ህይወት እንደልጅም እንደሚስትም ቢሆንም ለሁለት ዓመት ያህል ነገሮችን ተለማምዳ መኖር እንደቻለች ገልፃለች፡፡ አልፎ አልፎ አባቷ የወሲብ ማርኪያ ቢጠቀምባትም አምርራ ከቤት እንድትወጣ ያስገደዳት ግን ሰክሮ ሲመጣ የሚያወርድባት አሰቃቂ ድብደባ ነው፡፡ "ባልሰከረ ጊዜ በጣም ይወደኛል፡፡ አብሬው ሳድር ምንም አይለኝም፡፡ ከሰከረ ግን ሌላ ሰው ነው፡፡ ይደበድበኛል፣ ይሰድበኛል፣ ወንድሞቼ እቤት ከሌሉ ደግሞ ይደፍረኛል፡፡ ቢያሰቃየኝም ከቤት ለመውጣት አላስብም ነበር፡፡ እንደሚደበድበኝ የሚያውቁ ጎረቤቶቻችን እኛ እናስተምርሻለን እያሉ ሁል ጊዜ ቃል ይገቡልኝ ነበር፡፡ ግን ሰው ቤት ሆኜ መማር አልፈለግኩም"

ለሁለት ዓመት ያህል ከኖረችበት የስቃይ ህይወት ለመገላገልና ከቤት ለመውጣት የወሰነችው ከሁለት ወር በፊት እንደሆነ ትናገራለች፡፡ "የአክስቴ ልጅ ሞቶ ወንድሞቼም እኔም የዋልነው ለቅሶ ቤት ነበር፡፡ ልጁ በእድሜ የወንድሞቼ ጓደኛም ስለነበር የሚያድሩት ሃዘኑ ቤት ነው፡፡ ማታ እኔ ሲደክመኝ ወደ ቤቴ ተመለስኩና ዘጋግቼ ተኛሁ፡፡ ሌሊት ላይ አባቴ ሰክሮ መጣ፡፡ ድምፁን ስሰማ ከፈትኩለትና ገባ፡፡ በጣም ሰደበኝ፡፡ አንቺ ዲቃላ፣ ሸርሙጣ . . . ይለኛል፡፡ ስድቡ ሲያስጠላኝ ለምን ትሰድበኛለህ ብዬ ተናገርኩት፡፡ ለምን ትናገሪያለሽ ብሎ ጨርቅ አፌ ውስጥ ጠቀጠቀብኝና ደበደበኝ፡፡ ሲደክመው ቁጭ ያለበት ሶፋ ላይ እንቅልፍ ወሰደው፡፡ ሳለቅስ ቆይቼ እኔም አንደኛው ሶፋ ላይ እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ሲነቃ ስካሩ ቀለል አለለት መሰለኝ የተኛሁበት ሶፋ ላይ መጥቶ ያዘኘና ደፈረኝ፡፡ ያኔ ድንግል አይደለሁም፡፡ ግን በኃይል ስለሆነ ነው መሰለኝ ደም ይፈሰኝ ነበር፡፡ ከደፈረኝ በኋላ ተመልሶ ተኛ"፡፡ እሷ ግን አልተኛችም፡፡ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ስታለቅስ አደረች፡፡ ሲነጋጋም ለቤት ወጪ ከተሰጣት የተረፋትን 7ዐ ብር ይዛ ልብሷን ጠቅልላ ከቤቷ ወጣች፡፡

አሰላ አያቷ ጋ ለመሄድ ፍላጎት ቢኖራትም ለምን ከቤት ወጣሽ? ብላ ብትጠይቀኝ ምን እመልሳለሁ በሚል ፍርሃት ወደ ማታውቀው አገር ናዝሬት አመራች፡፡ ናዝሬት ከደረሰች በኋላ መተሃራ የሚል መኪና ስታገኝ ወደ መተሃራ አመራች፡፡

መተሃራ እንደደረሰች በደላላ አማካኝነት ሰው ቤት የመቀጠር ፍላጎት ነበራት፡፡ "በተረፈችኝ ገንዘብ አልጋ ይዤ አደርኩና በማግስቱ ለቤት ሰራተኝነት የሚያስቀጥሩት ደላሎችን ፈልጌ ሄድኩ፡፡ እንዲህ ማለት ያሳፍረኛል እንጂ ሙያ ብዙም አልችልም፡፡ እንጀራ ጋግሬ አላውቅም፡፡ ፅዳት ካለ አስቀጥረኝ አልኩት" አንድ ቁርስ ቤት ውስጥ ቢያስቀጥራትም በማግስቱ ሥራ አትችይም ተብላ ተባረረች፡፡ በሦስተኛው ቀን ደግሞ መተሃራ ውስጥ "ብርቱካን ሰፈር" እየተባለ በሚታወቀው አካባቢ በጫት ሻጭነት ተቀጠረች፡፡

ብርቱካን ሰፈር የሚባለው አካባቢ በብዛት ሺሻ የሚጨሱባቸው ጫት ቤቶች የሚገኙበት ነው፡፡ ጫት ቤቶቹ ቀን ቀን ብቻ ሳይሆን ማታም አገልግሎት ሲሰጡ ያድራሉ፡፡ የ17 ዓመቷ ወጣት ጫት የሚባል ከዚያ በፊት ቀምሳ እንደማታውቅ ትናገራለች፡፡ ይሁንና ማታ ማታ እየሸጠች ስለምታድር ለእንቅልፍ ብላ መቃም ጀመረች፡፡ ቀንም ማታም የምታሳልፈው ጫት ቤቱ ውስጥ በማስተናገድ ነው፡፡ በቂ እንቅልፍ አታገኝም፡፡ ስለሆነም ከአንድ ወር በላይ መሥራት አልቻለችም፡፡

ሙያ ባለመቻሏ ሰው ቤት ውስጥ በሠራተኝነት ለመቀጠር አልቻለችም፡፡ ጫት መሸጡም እንቅልፍ ስላሳጣት ከወር በላይ መሥራት አልቻለችም፡፡ የመጨረሻ አማራጭ አድርጋ የወሰደችው መተሃራ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ በአልጋ አከራይነት መቀጠር ሆነ፡፡

በአሁኑ ወቅት የተቀጠረችው በአልጋ ማከራየት ሥራ ቢሆንም በየቀኑ ባይሆንም የሴተኛ አዳሪነት ሥራን ተያይዛዋለች፡፡ "ሥራዬን የምጨርሰው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ቁልፌን አስረክቤ የጠየቀኝ ሰው ካለ ከእሱ ጋር አድራለሁ፡፡ በየቀኑ ጥያቄ ይኖራል ግን በየቀኑ አልወጣም፡፡ ምክንያቱም በግልፅ ሆቴሉ ውስጥ ለወሲብ ንግድ የሚሰሩ አሉ፡፡ አልጋ ክፍሎቹ አካባቢ ለመታየት ብቅ ይላሉ፡፡ በየቀኑ ከእነሱ እኩል መስራት የእነሱን ገበያም መሻማት ይሆናል" ትላለች፡፡  

ሥራውን በቅርብ እንደመጀመሯ ሌሎች ሴተኛ አዳሪዎች እንደሚሉት ኮንዶም አልጠቀምም የሚል፣ ያልፈለገችውን የወሲብ ዓይነት እንድትፈፅም የማያስገድዳት አላጋጠማትም፡፡ "300 እና ከዚያ በላይ የፈለግሽውን እከፍልሻለሁ አድርጊ የምልሽን ታደርጊልኛለሽ የሚሉ አንድ ሰው አጋጥመውኝ እምቢ ብያቸዋለሁ" ብላለች፡፡ ታዳጊዋ ይህንን ሥራ ከጀመረች አንድ ወር ሆኗታል፡፡ እስከ  ዛሬ ለአዳር ሦስት ቀን 15ዐ ብር የተከፈላት ሲሆን ከወንድ ጋር ባደረችባቸው ሌሎች ቀኖች ደግሞ 100 ብር ተከፍሏታል፡፡ ለወደፊቱስ ምን ታስቢያለሽ የሚል ጥያቄ አቅርበንላት ነበር፡፡ "ስለወደፊቱ አስቤ አላውቅም፡፡ ትምህርቴን ብማር ደስ ይለኛል፡፡ የምትተርፈኝን ገንዘብ አስቀምጣለሁ፡፡ ለምን እንደማስቀምጥ ግን እኔም አላውቀውም" በማለት የወደፊት ህልም እንደሌላት ታሰረዳለች፡፡

 
< Prev   Next >