Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow “ለዋጋ ግሽበቱ መፍትሄ የምግብ...
“ለዋጋ ግሽበቱ መፍትሄ የምግብ... Print E-mail
Sunday, 04 May 2008
Image“ለዋጋ ግሽበቱ መፍትሄ የምግብ እህሎችና ምርቶችን በገፍ እንዲመረቱ ማድረግ ነው”

ዶ/ር ሚናስ ኅሩይ የተስፋ ድርጅት ፕሬዚዳንት

በኢትዮጵያ በዋጋ መናር የተነሳ የተከሰተው የኑሮ ውድነት ህብረተሰቡን ለከፋ ችግር እየዳረገው ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የኑሮ ውድነትን ጨምሮ ህብረተሰቡን የሚጐዱ የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ የሚመለከታቸው አካላት በመሰባሰብ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ይወያያሉ፡፡
በአገራችንም ይህ መጀመር አለበት በሚል ሚያዚያ 23 ቀን 2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ ዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንዲሁም ዘላቂ የመፍትሄ ሃሳቦች በሚል የኢትዮጵያ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሕዝባዊ የምክክር መድረክ ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡

ከ2ኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ትምህርታቸውን በአሜሪካ ተከታትለዋል፡፡ በቢዝነስ ቢ.ኤ ዲግሪ፣ በኢዱኬሽንና በማኔጅመንት የማስተርስ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በፐብሊክ ፖሊሲና በፐብሊክ ማኔጅመንት አግኝተዋል፡፡ ዶ/ር ሚናስ ኅሩይ የተስፋ ድርጅት ፕሬዚዳንትና የምክክር መድረኩ አባል ሲሆኑ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- በአገራችን ያለውን የዋጋ ግሽበት እንዴት ይገልፁታል?

ዶ/ር ሚናስ፡-
አዲስ ችግር እንደሆነ ነው የማውቀው፡፡ የስደት ኑሮዬን ትቼ አገሬ ከመጣሁ በኋላ ሲገርመኝ የቆየው ለኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ለምን ችግር አይደለም የሚለው ነበር፡፡ ከዛሬ 5 ዓመት በፊት የዋጋ ግሽበት ችግር አልነበረም፡፡ የምግብ እህሎችና አትክልቶች ላይ ዋጋ ጨመረ ሲባል በ2 እና 3 በመቶ በመሆኑ ሕዝቡ የሚቋቋመው ዓይነት ነበር፡፡ ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ ከ3 በመቶ ወደ 5 በመቶ እያለም 10 እና 15 በመቶ ዛሬ ደግሞ በአማካይ 29 በመቶ ደርሷል፡፡ ወደ ምግብ በሚመጣበት ጊዜ የዋጋ ግሽበቱ ፈር ለቆ በተለይ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች እየጐዳና እየተፈታተነ ነው፡፡ ችግሩ እንግዳ ስለሆነ እንዴት አድርገን እንቆጣጠረው ለማለትም እንግዶች ነው፡፡ ለጥያቄውም እንግዳ ነን፡፡ በዚህ ምክንያት ጉዳዩ መድረክ ላይ መቅረብ አለበት፡፡ ህብረተሰቡ በግሉ እየተነጋገረበት ነው፡፡ ሆኖም ዘላቂ መፍትሄ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል እየታየ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ግሽበቱ እየባሰ የመጣው ከ5 ዓመት ወዲህ ከሆነ ለምንድን ነው በእነዚህ ዓመታት ልንቆጣጠረው ወደ ምንችልበት ስልት ያልገባነው?

ዶ/ር ሚናስ፡-
አንድ አዲስ ነገር ሲመጣ አዲስ በመሆኑ ዘልቆ ገብቶ እስከሚጎዳን ድረስ ችላ የማለት ጉዳይ ሊኖር ይችላል፡ እንዴት እናድርገው ተብሎ ለችግሩ እልባት ለማግኘት የሚያስቸግርበት ሁኔታ አለ፡፡ በውጭ 29 ወይም 30 በመቶ ግሽበቱ ደርሶ ሳይሆን 2 እና 3 በመቶ ጨመረ ሲባል እሪታ ከየቦታው ይመጣል፡፡ መንግሥትም፣ ፓርላማውም፣ ኮንግረሱም፣ ሚድያውም ያስተጋቡታል፡፡ ሕዝቡም አቤት የሚልበት ሁኔታ አለ፡፡ በአሜሪካም ሲታይ የወተት ዋጋ 6 በመቶ የእንቁላል 7 በመቶ ጨመረ ተብሎ የእሪታ ሁኔታ እያየን ነው፡፡ እነሱ በዚህ ብዙ ስለተመላለሱ፣ ባህላቸውም ጉዳዩን ለማስተጋባት የሚደግፍ ስለሆነ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ መሣሪያዎች አሉዋቸው፡፡ አሰራራቸው ውስጥ የተለያዩ መቋቋሚያ አበጅተው ብቅ በማለት ችግሩን ይፈቱታል፡፡ በአገራችን ችግሩ አዲስ ስለሆነ ምንም ችግሩን የመፍቻ ዘዴ የለንም፡፡ የሲሚንቶ ዋጋ በኩንታል ከ60 ብር 300 ብር ሲሄድ እንዴት ተብሎ መፍትሄ የሚሰጥበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ የነበረው ሁኔታ እሳት የማጥፋት ዓይነት፤ ለተወሰኑ ኩባንያዎች ሲሚንቶ እንዲያስገቡ መፍቀድ ነበር፡፡ ዘላቂነት አልነበረውም፡፡ በኋላም በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ፋብሪካዎች በመቋቋም ላይ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ነገር ተወደደ በተባለ ቁጥር ለተወሰኑ ኩባንያዎች ፈቅዶ ከውጭ የማስገባቱ ጉዳይ ዘላቂ መፍትሄን ያመጣል?

ዶ/ር ሚናስ፡-
ይህ እሳት የማጥፋት ሁኔታ ነው፡፡ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው ወሳኝ ምርቶችን በአገር ውስጥ በስፋት ለማምረት የሚበጀውን ሲደረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የነዳጅ ዘይትን በሚመለከት መንግሥት በአቋሙ የነዳጅን ዋጋ በመደጐም መኪኖች እንዲመገቡ አድርጓል፡፡ ይህን ባያደርግ ግብርናውንም ጨምሮ የዋጋ ግሽበቱ በሁሉም ሊንፀባረቅ ስለሚችል ጥሩ የመፍትሄ አካሄድ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣው መኪኖቹ በዚያ ሁኔታ እየተመገቡ ሰዎቻችን ግን እየተመገቡ አይደለም፡፡ የምግብን ዋጋ ለመቆጣጠር ድጐማ የለም፡፡ ነጋዴዎች እንደፈለጋቸው የሚዋኙበት የዋጋ ሜዳ ነው ያለው፡፡ እንደፈለጋቸው በመሆን ደሃውን ሕዝብ እያስጨነቁና እያስጠቁ ነው፡፡ ምግቦች እንዳይገቡና እንዳይሸጡ በመጋዘን እያስቀመጡ በተለይ መግዛት የማይችለውን ደሃ ሕዝብ እያንገላቱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይሄንን መንግሥት እንዴት ይቆጣጠረው?

ዶ/ር ሚናስ፡
- መፍትሄው ቁጥጥር አይደለም፡፡ መፍትሄው ወሳኝ የምግብ እህሎችንና ምርቶችን በገፍ በአገር እንዲመረቱ ማድረግ ነው፡፡ የተለያዩ አገሮች ለምሳሌ ሕንድ ሩዝ በገፍ እንዲመረት ትፈልጋለች፡፡ ሩዝ በገፍ መመረቱን የፀጥታ ጉዳይ አድርጋ ታያለች፡፡ ሩዝን ለማስመረት ለገበሬው የተለያየ ማበረታቻ አላት፡፡ መንግሥት በቀጥታ ምርት ውስጥ አልገባም፡፡ የእርሻ ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲሸጥ በማድረግ አንዳንዴም በመደጐም ገበሬው እጅ እንዲገቡና ገበሬው እንዲያመርትና በገበያው መርህ መሠረት ዋጋውን ዝቅ የማስደረግ ሁኔታ አለ፡፡ ሕንድ ውስጥ አይናቸውና ልባቸው ሁል ጊዜም ዋጋው ላይ ነው፡፡ በተለይ የምግብ ዋጋ ላይ፡፡

ሪፖርተር፡- የምግብ ዋጋ ላይ ትኩረት የሚያደርገው መንግሥትም ነው?

ዶ/ር ሚናስ፡-
ከአካባቢ መንግሥታት ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥቱ ድረስ የዱቄት፣ የስንዴ፣ የሩዝ፣ የወተት፣ የዳቦና የመሳሰሉትን መሠረታዊ ምግቦች ዋጋ ስንት ነው ብለው ያያሉ፡፡ ምርቱም ከበቂ በላይ በሆነ መንገድ እንዲኖር ግፊት ያደርጋሉ፡፡ ተመርቶ ለሽያጭ ሲቀርብ ሕዝቡ ይችለዋል ወይ የሚለውን ያያሉ፡፡ ምርቱ ተመርቶ ለገበያ እስኪደርስ ያለው ወጪ በመረጃ ስላላቸው ዋጋ ከፍ በሚልበት ጊዜ ይህንን የሚቆጣጠሩበት መንገድ አላቸው፡፡ ለመቆጣጠርም ምርቱ ከተመረተ በኋላ መንግሥት ገዝቶ በመጋዘን ያስቀምጣል፡፡ ሕዝብ ይችለዋል በሚለው ዋጋም የመሸጥ ሁኔታ አለ፡፡ ይህን የዋጋ ድጋፍ ይሉታል፡፡ በዚህ እይታና ሂደት ማንም ምርቱን በመጋዘን እያጐረ ወይም ከውጭ ስንት ይመጣል እያለ እየተመካከረ ዋጋውን የትም የሚያደርስበት ሁኔታ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በነፃ ገበያ መርህ መንግሥት ይህንን ማድረግ ይችላል?

ዶ/ር ሚናስ፡-
እዚህ ላይ ውሳኔ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ በተለይ መሠረታዊ ምግቦች ላይ ያለውን የዋጋ ግሽበት መንግሥት ባትኩሮት ሊያየው ይገባል፡፡ ለምሳሌ የወተት ሁኔታ በአገራችን በነጋዴዎች ቁጥጥር ስር ስለሆነ ልጆች እየጠጡ አይደለም፡፡ እኛ ስናድግ ከቫይታሚን “ኤ” ጋር መንግሥት ያጠጣ ነበር፡፡ አሁን ይህ ሁኔታ የለም፡፡ ላሞችም በብዛት የሉም፡፡ ወተትም የለም፡፡ ለዚህም ከ17 በመቶ የማያንሱ ህፃናት 5ኛ የልደት በዓላቸውን አያከብሩም፡፡ ወተት ከውጭ ይመጣል፡፡ ከ110 እስከ 200 በመቶ ድረስ እጥፍ ሆኖ ይሸጣል፡፡ አቅም ያለው ይገዛል፡፡ ሆኖም 50 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ናቸው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚያስከትለው የሰውነትን መቀጨጭ ብቻ ሳይሆን የአእምሮንም  ነው፡፡ ይህ አገሪቱን ለመምራት የሚችል የአእምሮ አስተዋፅኦን ስለሚቀንስ ልማታችንም አዳጋች ይሆናል፡፡ በመሆኑም ለወተት፣ ለቅባት፣ ለጤፍና ለመሳሰሉት መንግሥት ሳይቆጣጠር መረጃውን በመከታተል ብቻ አድሎአዊ ያልሆነ የዋጋ ጣሪያ ገደብ (Price Margin) እየፈቀደ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በነፃ ኢኮኖሚ መርህ እየተዳደሩ ይህን የሚከተሉ አገሮች አሉ?

ዶ/ር ሚናስ
፡- አሉ፡፡ ሜክሲኮን ብንወስድ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የሚጠቀሙት በቆሎ ዋጋው እንዳይንር የተለያየ መንገድ ትጠቀማለች፡፡ የዋጋ ድጋፍ አለ፡፡ ከገበሬው ትርፉን ባላሳነሰ መንገድ ገዝተው የማስቀመጥ እንዲሁም ራሳቸው ምርት ውስጥ በመግባት ሕዝቡን የመደገፍ አሰራር አላቸው፡፡ በተለይ ዋና በሚባሉት እንደ በቆሎ በመሳሰሉት ምርቶች ይገባሉ፡፡ በግሉ ዘርፍ የሚመረተው ዋጋው ሲንር መንግሥት የራሱን ይለቃል፡፡ መንግሥት ራሱም አስመጪ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ በአገራችን የዚህ ዓይነቱ አሰራር በጅምላ ንግድ አስመጪ ድርጅት የሚሠራ ቢሆንም ድርጅቱ በሚያጥለቅለቅ ሁኔታ እየሰራ አይደለም፡፡ ለጊዜው የማብረድ ሁኔታ ነው እየሰራ ያለው፡፡ ዘይት ስለተወደደ ዘይት ብቻ ከሚያመጣ ወተት፣ መድሃኒትና የመሳሰሉት መሠረታዊ ምግቦችና የሕዝብ ፍላጎቶች ላይ ለምን በገፍ አይሠራም? የውጭ ምግብ ቸርቻሪዎች ትርፋቸው ከ10 እስከ 18 በመቶ ነው፡፡ ገቢያቸውን የሚያገኙት በመጠን ነው፡፡ ሁል ጊዜም እንቅስቃሴ አለ፡፡ በሚገኘው ገቢ ንግዳቸውን ይገነባሉ፡፡ በአገራችን ምርትን አንቀው ይዘው ዋጋው ወደላይ እስኪወጣ ይጠብቃሉ፡፡ መመካከርና ህገወጥነትም አለ፡፡ የንግዱ ህብረተሰብ ግብረገብነቱን በጠበቀ መልኩ ታማኝ መሆን አለበት፡፡ የዋጋ አድማ ማድረግ የለበትም፡፡ በሌላው ዓለም የዋጋ አድማ የኩባንያ መሪዎችን እስር ቤት ያስገባል፡፡ በአሜሪካ መረጃ ከተገኘ እርምጃው ይወሰዳል፡፡ በአገራችን በስሚንቶው፣ በብረት፣ በምግብ፣ በወተት፣ በስኳር... የዋጋ አድማ አለ፡፡ ይህ መሰበር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በተለይ በምግብ እህሎች ላይ ያለውን በምን መልኩ መቆጣጠር ይቻላል?

ዶ/ር ሚናስ፡
- መንግሥት ፖሊስን ማሰማራት አለበት፡፡ ለምንድን ነው በሳንቲም ደረጃ ዋጋ የማይለያዩት፡፡ በውጭው ዓለም ፋብሪካ አካባቢ ጠጋ ሲባል ዋጋ ዝቅ ይላል፡፡ ራቅ ሲል ከፍ ይላል፡፡ ጐን ለጐን ባሉ ሱቆች የዋጋ ውድድር አለ፡፡ አንዱ የሰጠውን ዋጋ ለማፍረስ ሌላው ያስተዋውቃል፡፡ በአገራችን ለምሳሌ የቆርቆሮ ዋጋ መርካቶ 100 እየተሸጠ ሌላ ቦታ 70 ቢሆን በነጋዴው ላይ በር የሚያንኳኳ አመፀኛ ይመጣበታል፡፡ ይህ ትልቁ ችግር ነው፡፡ በመጪው ሸቀጦችን የመቆጣጠር ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ መነሻው ቻይና መድረሻው መርካቶ ቢሆን ከመነሻው እስከ መድረሻው አንድ አካል ይቆጣጠረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥታችን ከነፃ የገበያ ፖሊሲው አንፃር ይህን ማድረግ ይችላል?

ዶ/ር ሚናስ፡-
በግል የሚሠራ ነው፡፡ መንግሥት ነፃ ገበያ ስላለ ወጥቷል፡፡ በግሉ የሚሠራ አካል የሚያደርገው የጅምላና የችርቻሮ ሽያጭን መቆጣጠር ነው፡፡ ይህንን ጥሶ ለማለፍ ማንም መንገድ አይኖረውም፡፡ በአገራችን አንዳንዱ ነጋዴ የጅምላ ንግዱን ተቆጣጥሮታል፣ ምርቱን ከየት እንዳመጣ አያሳውቅም፣ አገራችን ቀጥታ ገብቶ ችርቻሮ ላይ ይውላል፡፡ ይህ ገበያን መቆጣጠር ማለት ነው፡፡ በእንደዚህ ገብተው የሚሸጡ ብዙ ምርቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጅምሩ ችግሮች መፍትሄ ቢያገኙ መንግሥት ብዙ ሳያደርግ የምርቶች ዋጋ ሊረጋጋ ይችል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ያለውን የዋጋ ግሽበት ችግር ከነምክንያቱ እንዴት መፍታት እንችላለን?

ዶ/ር ሚናስ
፡- መመካከር ያስፈልጋል፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ አካላት ሊነጋገሩ ይገባል፡፡ ሸማቾችም መደራጀት አለባቸው፡፡ የንግዱ ህብረተሰብ የዋጋ አድማ አድርጐ እንደሚያስቸግር ሁሉ ሸማቹም በመነጋገር አንገዛም እስከማለት የሚደርስ የአድማ ጡንቻ ሊኖረው ይገባል፡፡ በሌሎች ዘርፎች በፉክክር ነገሮች እልባት እያገኙ ነው፡፡ ወደ ንግዱ ስንመጣ ግን ፍፁም ነፃ አድርገነው የወንጀል መልክና ባህሪ እየያዘ አስቸጋሪ ሁኔታ በአገራችን እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህ ግብር መክፈልንም ይመለከታል፡፡ ደረሰኝ የማይሰጡ ሱቆች አሉ፡፡ ደረሰኝ ከወሰዱ ተጨማሪ እሴት ታክስ ይከፍላሉ የሚሉም አሉ፡፡ ንግድ ከሆነ በአግባቡና በታማኝነት መከናወን አለበት፡፡ በግብርና ኢንቨስትመንትም ብዙ ነጋዴዎች እየተሳተፉበት አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- በነፃ ገበያ ስም የመንግሥት የቁጥጥር ዘዴ መላላት ለችግሩ መንስኤ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ?

ዶ/ር ሚናስ፡-
ትክክል ነው፡፡ በውጪው “Better business Bureo” አለ፡፡ የመንግሥት አካል ነው፡፡ ዋጋን በፋብሪካ፣ በጅምላና በችርቻሮ ንግድ ደረጃ ያትማል፡፡ የዋጋ አድመኞች፣ ንግድን በጅምላ የመቆጣጠር (ከምርት እስከ ችርቻሮ)፣ በንግዱ ህብረተሰብ ካለ ወንጀልና የውድድር መርህም አይደለምና ይከታተላል፡፡ በሌላ በኩል ሸማቹ ብሶቱን ለኩባንያው አቀርቦ ምላሽ ካላገኘ ለቢሮው ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሸማች የተበላሸ ምግብ ከገዛ ሄዶ ይመልሳል ገንዘቡን፤ ይቀበላል፡፡ በአገራችን ይህ አይቻልም፡፡ የተበላሸ/የተቀላቀለ ቅቤ የገዛ ሰው ለመመለስ መብት የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ በደረሰኝ ካለመገበያየት የመጣ ይመስላል፡-

ዶ/ር ሚናስ፡
- የተሸጠው እቃ እንደተገዛው ሆኖ ሳይገኝ የመመለስ/የመቀበል ግዴታ እንዳለ ባለመቀበል ነው፡፡ በአገራችን ደረሰኝም ኖሮ የንግዱ ህብረተሰብ የራሱን ስነምግባር ስላላወጣ፣ በመንግሥትም በኩል ሕግ ስለሌለ ተቀባይነት የለውም፡፡ የሸማቾች ማህበር በግፊት ብቅ እንዲል ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱም ይህ ነው፡፡ መድሃኒትን ጨምሮ ያልሆነውን ሆነ ብሎ የመሸጥ ሁኔታ አለ፡፡ መንግሥትም ሆነ የንግዱ ህብረተሰብ በየፊናው ሁኔታዎችን ለማስተካከል መሥራት አለባቸው፡፡ በበለጠ ደግሞ ሸማቹ ተገቢ ካልሆኑ ነገሮች ለመዳንና መብቱን ለማስጠበቅ መደራጀት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የሕዝቡን አቅም ጭራሽ ባላገናዘበ መልኩ የዋጋ ግሽበቱ እየናረ ነው፡-

ዶ/ር ሚናስ፡-
ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ በዓለማቀፍ ደረጃ የዋጋ መናር፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ በምዕራቡ ዓለም ከሚታየው የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተያይዞ የዶላር መቀነስና በአጠቃላይ በዓለም ደረጃ የምርት ማነስ ይጠቀሳሉ፡፡ የምግብ ማነሱ የተከሰተው በላተኛው ስለጨመረ ብቻ ሳይሆን ከካርቦን ውጭ የሃይል ምንጭ ለማግኘት ሲባል የምግብ ውጤቶችን የመጠቀሙ ሁኔታ በመኖሩም ጭምር ነው፡፡ ቀድሞ ስንዴና በቆሎ በብዛት የሚመረትባቸው አገሮች ተመጋቢው አነስተኛ ስለነበረ ትርፍ ምግብ ወደ ማጐሪያ የሚሄድበት፣ ወደ ባህር የሚጣልበት ሁኔታ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት አዲስ የእህል ጥቅም ብቅ ስላለ በአሜሪካ ብቻ 150 የሚሆኑ ፋብሪካዎች በቆሎውንና ስንዴውን ይሰበስባሉ፡፡ ገበሬዎችም ጥሩ ዋጋ እያገኙ ነው፡፡ በአገራችንም ተመሳሳይ ነገሮችን ለመሥራት የእህል ውጤቶችንም ባይሆን ሌሎች አዝርዕቶችን ለመጠቀም ጅምሩ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በአገራችን የአመጋገብ ባህል በተለይ ጤፍን ስናይ ከውጪዎቹ ፍፁም የተለየ ነው፡፡ ከውጪው ዓለም በማያዛምደን መሠረታዊ ምግባችን ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ይታያል፡፡ ከነዳጅ መጨመር ጋር የተያያዘውን ለውጥ ብንቀበለውም ግሽበቱ ከነዳጅም በዘለለ ነው፡-

ዶ/ር ሚናስ፡
- ጤፍን በሚመለከት የዋጋ ንረቱ የተከሰተው በአገራችን ሕንዶች የሚጠቀሙበት አብዝቶ ማምረትና የዋጋ ድጋፍ ባለመኖሩ ነው፡፡ ጤፍ ወደ ውጭ የሚላክ ቢሆንም አነስተኛ ነው፡፡ ተከልክሎም የሚወጣበት ሁኔታ አለ፡፡ መንግሥት መጠንከር ያለበት ጠረፎችን አጠንክሮ መቆጣጠሩም ላይ ነው፡፡ በአንድ አገር ጤፍን ለመድሃኒትነት እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ስንዴ ግሉቲን ስላለው ስንዴ የማይበሉ ሰዎች ጤፍ ተተኪ ሆኖ ተዘጋጅቶ የሚቀርበበት ሁኔታ አለ፡፡ ዲያስፖራውም እያደገ ስለሆነ ጤፍ ከዚሁ ሄዶ ነው የሚመገበው እንደ አሜሪካና ሆላንድ ያሉት ጤፍን ማምረት ቢጀምሩም ምርቱ አናሳ ስለሆነ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያን ኤክስፖርት አይተካም፡፡ ወደውጭ መላኩን ገበሬውም ነጋዴውም ስላወቀ አካሄዱንና እቅዱን ልላክ በሚል እየተሰለፈ ነው፡፡ ልክ ከብቶቻችን ወደ ሱዳን እንደሚጓዙት፡፡ እዚህም ላይ መንግሥት ሚና አለው፡፡ የሕዝቡን የምግብ ፍላጐት የሚገፋ ሁኔታ ሲፈጠር የሚገፋውን ሁኔታ ለመግፋት ዘዴ መፍጠር አለበት፡፡ መንግሥት በአገሪቱ ጤፍ በብዛት ለማምረት የምትፈልጉ ባለሀብቶች ካላችሁ እናንተን ለማቋቋም የቻልኩትን አደርጋለሁ ማለት አለበት፡፡ ጤፍ አምርታችሁ ለአገር ፍጆታ ብቻ አውሉ ብሎ ፖሊሲ ማውጣት ይኖርበታል፡፡ ጤፍ ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ ሕንዶቹ አንዳደረጉት የወተት ምርት ወሳኝ በመሆኑ በብዛት እንዲመረት ማበረታታት አለበት፡፡ ሕንዶች ከራሳቸው ተርፈው ወተት ወደ ሌላ አገር መላክ ጀምረዋል፡፡ ወሳኝ በሆኑ ምርቶች ላይ የሕዝቡን ፍላጐት ያለዋጋ ግሽበት ለማሟላት መንግሥት መሥራት አለበት፡፡ ዝናብን ከመጠባበቅም ወደ መስኖ ልማት መሄድ አለብን፡፡ ይህ በተለያየ ሁኔታ ሲነገር ቢቆይም እየሞቀና እየቀዘቀዘ ጉዳዩ ዘላቂ በሆነ መንገድ የሄደበት ሁኔታ የለም፡፡   

ሪፖርተር፡- በአገራችን በቆሎ በተትረፈረፈተበት ወቅት ገበሬው ሳይጠቀም ቀረ የሚል ሃሳብ ሲሰነዘር ነበር፡፡ የምርት መብዛት መንግሥትን ማስደንገጥ አለበት?

ዶ/ር ሚናስ፡-
ድግግሞሹን እንቀጥልበት፡፡ ጉዳዩ ማምረት ብቻ አይደለም፡፡ ጥሬ ምርቱን ፕሮሰስ ማድረግ አለብን፡፡ ፕሮሰስ ከተደረገ ልንይዘውም ውጭ ልንልከውም እንችላለን፡፡ የበቆሎው ሁኔታ የሚያሳዝን ነው፡፡  ከደቡብ አፍሪካና ከአረብ አገር ..ኮርን ፍሌክስ.. ከምናመጣ አከማችተን አገራችን ልናመርት እንችል ነበር፡፡ ቴክኖሎጂው በጣም ቀላል ነው፡፡ ድንች በአገራችን ተወዷል፡፡ በብዛት አምርተን የድንች ጥብስና ዱቄት ተዘጋጅቶና ታሽጐ ሊቀመጥም ውጭ ሊላክም ይችላል፡፡ እኔ በአጠቃላይ ሳየው እዚህ ላይ መንግሥት ትኩረት ማድረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡ የኢንቨስትመንት ሂደቱንና ትራፊኩን በዚህ ማሳለፍ ይኖርበታል፡፡ እስካሁን ሆቴል መስራትና በመሳሰሉት ነው ልማቱ ያለው፡፡ ታች ነጥሮ ካልወጣ ምንም አያደርግም፡፡ የኢንቨስትመንት ቅድሚያዬ ይሄ ነው፤ ሕዝቤ የሚፈልገው ይሄን ነው፤ ምግብ የአገር ደህንነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ብሎ የኢንቨስትመንቱን የተወሰነ ፐርሰንት በምግብ እህሎች ማሳተፍ አለብኝ ማለት አለበት፡፡ በሌላ በኩል ባንኮች ብዙ እየሰሩ አይደለም፡፡ በውጭ አገር ኢንቨስትመንት የሚያስኬዱት ባንኮች ናቸው፡፡ በአገራችን ባንኮች በክፍያና በኮሚሽን ስለሚያተርፉ ልማት ላይ እያተኮሩ አይደለም፡፡ ትርፋቸውን ገንዘብ በመላክ ከመሳሰሉት ስለሚያገኙ የገጠር ልማት ላይ የሉም፡፡ የገጠር ልማት ላይ አዋጭ የሆነ ፕሮጀክት አዘጋጅተው ቢሰሩ ለምግብ ችግራችን በረዥም ጊዜ መፍትሄ ይገኛል፡፡ ከ10ና 15 ዓመት በኋላ የሕዝቡም ቁጥር ስለሚጨምር ይህም ተሠርቶ ጠብ ላይል ይችላል፡፡ ይህ ካልሆነ ወደ ሌላ አማራጮች መሄድ አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት አማራጮች?

ዶ/ር ሚናስ፡-
ለምሳሌ ግብፆች የሚጠቀሙበትን የድጐማ መንገድ መከተል፡፡ መንግሥት ነዳጅ እንደሚደጉመው ቤቶችን፣ ትራንስፖርትን፣ ምግብን መደጎም ያስፈልገዋል፡፡ ነዳጅ ላይ እንድንመረኮዝ ያደረገን የሕዝብ ትራንስፖርትን እየደገፍን ባለመሆኑ ነው፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርትን ለመደገፍ የግል መኪና ይዞ የሚሄደውን ለነዳጅ የሚከፍለውን በመጨመር፣ ፈቃዱን ሲያሳድስ ክፍያ ከፍ በማድረግ ገቢውን ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በማዋልና የሕዝብ ትራንስፖርት ላይ ኢንቨስት በማድረግ ነዳጅ ላይ ያለውን መመርኮዝ መቀነስ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ግብፅ በዋጋ ግሽበት የተነሳ ወደ ውጭ የምትልከውን ሩዝ አቁማለች፡፡ በአገራችንም ጤፍ ላይ ገደብ ተጥሏል፡፡ ብቻውን መፍትሄ ይሆናል?

ዶ/ር ሚናስ፡-
ዋና መፍትሄው በተትረፈረፈ መልኩ ማምረት ነው፡፡ ገበሬው በገፍ አምርቼ ዋጋ ይወድቃል እንዳይል መንግሥት የዋጋ ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ ገበሬ አይከስርም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በሚያተርፍበት ሁኔታ ስንዴውንም ሆነ ሌላውን ስለሚገዛው ነው፡፡ አገራችንም ሆነ ሌላ ቦታ ድርቅ ሲሆን ስንዴ በገፍ የሚልኩት ለዚህ ነው፡፡ ግሽበት በታየም ጊዜ መንግሥት በአነስተኛ ዋጋ ይሸጠዋል፡፡ ይህ ዋጋን ለማረጋጋት የሚጠቀሙበት ነው፡፡ የእርሻ ሰብል ተቋማትና እንቅስቃሴ ወደዚህ ዓይነቱ አሰራር መዞር አለባቸው፡፡ መንግሥት በገበሬውና በገዢው መካከል ያሉ ደላላዎችን በተቻለ መጠን ቢያስወግድ ጥሩ ነው፡፡ እህል በማመላለስ የሚሰሩ ትራንስፖርተሮች ላይም ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡ በሕንድ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል እህል በሚሸጋገርበት ጊዜ በመንግሥት ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ የት እንደሚሄድና የትኛው ሱቅ እንደሚገባ፡፡ በገባበት ቦታ መድረሱን፣ የሚሸጥበትን ዋጋ ያረጋግጣል፡፡ ይቆጣጠራል፡፡ በአገራችን ይህ አሰራር ባለመኖሩ አመላላሾች ገዢዎችና ራሳቸው ሻጮች ይሆናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በምግብ እህሎችና በሌሎች ምርቶች ላይ የዋጋ ውድድር አይታይም፡-

ዶ/ር ሚናስ፡-
መንግሥት የዋጋ ውድድር እንዲኖር እንደ አንድ መስፈርት ማስቀመጥ አለበት፡፡ ነጋዴው ዋጋ እንዲለጥፍ መደረግ አለበት፡፡ ሆኖም ዳቦ ቤት እንደለጠፉት አንድ ዓይነት ዋጋ መሆን የለበትም፡፡ የአንዱ ከሌላው ለምን ዝቅ አይልም? የዋጋ ውድድር ሲባል ከስሮ እስከመሸጥ ድረስ ነፃነት አለ፡፡ ይህ ደግሞ አዳዲስ ገዢዎችንም ለመሳብ በውጪውም ዓለም የሚሠራበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥት በኩል ነፃ የገበያ መር ፖሊሲ ቢቀመጥም ነጋዴው ነፃ ገበያ ምን ማለት እንደሆነ አልገባውም፡-

ዶ/ር ሚናስ፡-
ልክ ነው፡፡ ነፃነት ከኃላፊነት ጋር ነው የሚሄደው፡፡ የንግዱ ህብረተሰብ ኃላፊነት አለበት፡፡ ገበያ እንዲኖረው ከፈለገ የሸማቾችን ህልውና መጠበቅ አለበት፡፡ በውጭ አገር ሸማቹን ለማገዝ ብዙ ኩባንያዎች የተራድኦ ክንፍ አላቸው፡፡ የእነሱ አመለካከት ሸማቹን ካገዙ ሸማቹ የእነሱ ደንበኛ ሆኖ እንደሚቀጥል ነው፡፡ Social Capital አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የንግዱ ህብረተሰብ ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ የመንግሥት ሚና ምን መሆን አለበት?

ዶ/ር ሚናስ፡-
መቆስቆስና ማስተማር አለበት፡፡ የእውቀት ችግር አለብን፡፡ የንግድ ሥነ ምግባር ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች አገሮች የንግዱ ህብረተሰብ የህብረተሰቡ አካል ነው፡፡ የተጐዱትንና ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ከመንግሥት ጋር ሆኖ እንዴት እንፍታው ብሎ ይወያያል፡፡ መኪና ወይም ሽቶ ቢወደድ ደስ የሚላቸው ሰዎች ይኖራሉ፡፡ የምግብ ውጤቶች ቢወደዱ ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለውም መፍትሄ ካልተገኘ ሰዎች የሚረብሹበት ሁኔታ ይመጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕዝቡ የመግዛት አቅሙ ከሚገባው በላይ እየወደቀ ነው ያለው፡፡ በሌላ በኩል የአገሪቱ ኢኮኖሚ አድጓል፡-

ዶ/ር ሚናስ፡-
ይህ እንቆቅልሽ ቢመስልም እድገት ሲመጣ የዋጋ ግሽበት አብሮ የሚመጣ መሆኑን ልንቀበለው የሚገባ ክኒን ነው፡፡ እድገት ሲመጣ የምርት ውጤቶችን ወደ ውጭ የመላክ ሁኔታ ይመጣል፡፡ ሲላክ ገዢዎች የሚሰጡት ገንዘብ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌ ጤፍ በአሜሪካ በ10 ኪሎ 20 ዶላር አካባቢ ነበር፡፡ ምርቱ ቢኖርም አገር ውስጥ ያለውን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህ በሌላ መልኩ ያለው ይግዛ ነው፡፡ ሆኖም የሌለው ምን ይሁን የሚለው ዋናው ጥያቄ ነው፡ አብዛኛው የህብረተሰባችን አካል በቀን ከ1 ዶላር በታች ገቢ ያለው በመሆኑ አገሪቷ የደሃው ናት ማለት እንችላለን፡፡ ስለዚህ የደሃውን ድምፅ ማዳመጥ ይገባል፡፡ ሕዝቡ በተለያየ መልኩ ችግሩን እየተናገረ ነው፡፡ እድገት በጥንቃቄ ካልተያዘ ባላቸውና በሌላቸው መካከል ያለውን ልዩነት ያሰፋዋል፡፡ እየታየ ያለው በእድገቱ ሃብታሙ እያደገ ደሃው ወደ ጐሬው እየገባ መሆኑ ነው፡፡ ይህ እድገት አይደለም፡፡ እድገት አብሮ የሚሄድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የሸማቾች ሚና አይታይም፡-

ዶ/ር ሚናስ፡-
የሸማቾች ሚና ጠቃሚ መፍትሄ ይሆናል፡፡ ሁልጊዜም ተጐጂው ሸማቹ በመሆኑ በዋጋ ንረት ጊዜ ለመፍትሄው ተዋናይ መሆን አለበት፡፡ ሆኖም በዘርፍ ችግር አለ፡፡ የሸማች ማህበራት በመንግሥት ካልተበረታቱ እንደነጋዴው ሊንቀሳቀሱ አይችሉም፡፡
 
< Prev   Next >