Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
Jul 05th
Home arrow Sections arrow ለብሔራዊ ባንክ በሽታ...
ለብሔራዊ ባንክ በሽታ... Print E-mail
Sunday, 04 May 2008
ለብሔራዊ ባንክ በሽታ መፍትሄው
ፓራሲታሞል ወይስ ቀዶ - ጥገና?

በአባዋሪ ጅብሪል

አንድ በሽተኛ ወደ ሆስፒታል ሲሄድ ዶክተሩ ከመረመረው በኋላ እንደ በሽታው አይነትና ክብደት መድሀኒት ያዝለታል፡፡ በዚሁ መሰረት እስካሁን የተገለጹትንና ያልተገለጹትን የብሔራዊ የባንክ መጠነ ሰፊ ችግሮች ስናጤናቸውና በአሁኑ ሰአት የገባበትን አዘቅት ስንመለከት በእርግጥ ለባንኩ በሽታ የሚያስፈልገው ለማስታገሻ የሚሆን ፓራሲታሞል ወይስ አጠቃላይ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሥር-ነቀል ለውጥ"ቀዶ ጥገና"? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ አድርጎናል፡፡

 

የባንኩ መሪዎች ያለባቸው በብቃት የመምራት የማስተዳደር ችግርና በተቋሙና በአገር ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው ጥፋት በዚህ አምድ በኩል መውጣት ከጀመረ በኋላ በባንኩ ውስጥ የተለያዩ ነገሮች እየተከሰቱ ነው፡፡ አንደኛ የባንኩ መሪዎች ራሳቸውን ሊያድኑ የሚችሉበትን ነገሮች ለማመቻቸት ላይ ታች ሲሉ፣ ሲሰበሰቡና ሪፖርት ሲያዘጋጁ ይታያሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኙትና የባንኩ መሪዎች ከቦታቸው ቢነሱና በሌላ ሰው ቢተኩ ችግር ውስጥ እንገባለን፤ ብለው የሰጉ በፖለቲካ አመለካከትና በአገራዊ አጀንዳ ሳይሆን ከመሪዎቹ ጋር ባላቸው የግል ጥቅም የተሳሰሩና በዋናው መስመር ላይ ተቀምጠው ልዩ ተጠቃሚ የሆኑ ከተራ ሰራተኛ እስከ ዳይሬክተር ደረጃ ያሉ ጥቂት ሰራተኞችና የስራ ሀላፊዎች ለሪፖርተር ጋዜጣ መረጃ የሚሰጡ እነማን ናቸው በሚል ምርመራ ተወጥረው ይውላሉ፡፡

ይሄ በእንዲህ እያለ በቅርቡ  የባንኩ ገዥ ሰራተኞችንና የስራ ሀላፊዎችን ሁሉ ሰብስበው ለመስደብና ለማስፈራራት መሞከራቸው በባንኩ ውስጥ ተጨማሪ መነጋገሪያ የሆነ ብቻ ሳይሆን መሪዎቹ አሁንም ገና በሰሩት ስራ ተፀጽተው ለመታረም ዝግጁ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ሆኗል፡፡

የባንኩ ገዥ ከሰራተኞች ጋር አጠቃላይ ስብሰባ ካደረጉ ከ4 አመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በእነዚህ አመታት ውስጥ ደግሞ በርካታ ችግሮችና ከፍተኛ ቅሬታዎች ተፈጥረዋል፡፡ የባንኩ ገዥም ከዚህ የተነሳ ሰራተኛ ሰብስበው ለማነጋገር ፍላጎቱ ስለሌላቸው በየመምሪያው "ከፋፍለህ ሰብስብ" ስልት ቀርጸው ሲያስፈጽሙ ነበር፡፡ ሆኖም እርሳቸውም ሆኑ ሌሎች ጥቂት የስራ ሀላፊዎች ከሰራተኛው ቢሸሹም ካለባቸው የብቃት ችግር ሊደበቁ አልቻሉምና ባንኩ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሶ ጉዳዩ ሁሉ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ በኋላ ማጠፊያው ማጠር ጀመረ፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ አጀንዳው ምን እንደሆነ ሳይገለጽ መጋቢት 15፣ 2000 ዓ.ም. ድንገተኛ አጠቃላይ የሰራኞች ስብሰባ ከሰአት በኋላ እንዳለ የሚገልጽ ማስታወቂያ ጠዋት ተለጠፈ፡፡ ሰራተኛው ከ4 አመት በኋላ በድንገት ስብሰባ የተጠራነው ምን ሊሉን ይሆን? ብሎ ወደ አዳራሹ አቀና፡፡ ስብሰባውም በባንኩ ገዢ ሰብሳቢነት እየተመራ የባንኩ የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሳይሆን በ2000 ዓ.ም. ባንኩ ያጋጠሙት 3 ከፍተኛ ችግሮች ምን እንደሆኑና መንግስት የደመወዝ ማስተካከያ እንዳደረገ የሚገልጽ ነበር፡፡ ከሦስቱ ከፍተኛ ችግሮች ውስጥ ሁለቱ ባንኩ ያጋጠመው ከፍተኛ የሆነ የሰራተኞች መልቀቅና የወርቅ መጭበርበር ጉዳዮች ነበሩ፡፡

ከዚህ በፊት የሰራተኞችን መልቀቅ ለመቀነስና ሰራተኞችን ለማቆየት እንዲቻል ቀና አመለካከት ባላቸውና አርቆ አሳቢ በሆኑ ጥቂት የማኔጅመንት አባላት፣ ሰራተኞችና በሰራተኛ ማህበሩ በኩል በተደጋጋሚ አሁን እነርሱ መፍትሄ ነው ብለው ያቀረቡትንና ሌሎች የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦች ሲቀርብላቸውና ሲለመኑ የባንኩ ገዥና የሰው ሀይልና የአስተዳደር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር "የሰራተኞች መልቀቅ የተለመደና የባንኩ ችግር አይደለም፡፡ ወደፊትም የባንኩ ችግር አይሆንም፡፡ ሰራተኛ ቢለቅ ሰራተኛ ይተካል ገበያው ላይ ብዙ የተማረ ሰው አለ. . ". እያሉ ነገሩን ሲያጣጥሉ ከርመው ነበር፡፡

ዛሬ መምሪያዎች ስራ ለመስራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ባንኩ በሰራተኞች መልቀቅ የተነሳ አስከፊ ችግር ውስጥ ገብቷል ብለው "የእርጂኝ አብሮ አደጌ" ጥሪ ቢያስተላልፉም በሰራተኛው ዘንድ በፊት ሲነገራቸው የት ነበሩ? ከማለት ባለፈ የጠበቁትን ያህል ትኩረትና መልስ ሊያስገኝላቸው አልቻለም፡፡ በስብሰባው ላይ የባንኩ ገዥ እንዳሉት በ6 ወራት ውስጥ ብቻ ወደ 600 ከሚጠጉት የባንኩ ሰራተኞች ውስጥ ከ50 በላይ ለቀዋል፡፡ በዚህ ስሌት በሳምንት ውስጥ ቢያንስ 2 ሰራተኞች ይለቃሉ ማለት ነው፡፡ ይሄም ሁኔታ የባንኩ መሪዎችና የሚመለከታቸው የስራ ሀላፊዎች አካባቢያቸውንና የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ተመልክተው የሰራተኛ እቅድና አስተዳደር/ሃበቂሮቃ Resource Planning and Development Policy and Strategy/ ስልት የማዘጋጀትና የማስፈጸም ብቃት ምን ያህል አነስተኛ እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል፡፡ ሆኖም እዚህ ጋር ሳንገልጽ የማናልፈው ጉዳይ ባንኩን ለቀው እየሄዱ ያሉት የስራ ሀላፊዎችና ሰራተኞች ሁሉ ባንኩን የሚለቁት የተሻለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ስላገኙ ብቻ ሳይሆን አንዳንዶቹ በደረሰባቸው አስተዳደራዊ በደልና ባንኩ ውስጥ ባለው የተበላሸ የሰራተኞች አስተዳደር ጭምር መሆኑ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

ባንኩን ያጋጠመው ሌላው ከፍተኛ ችግር ተብሎ በገዢው የተገለጸው ባንኩ የተጭበረበረበት የወርቅ ግዢ ጉዳይ ነው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ ክስተቱ ". . . የባንኩን ሰራተኞች አንገት ያስደፋ፣ አገሪቱን 158 ሚሊዮን ብር ያሳጣ፣ ሰራተኞች የብሔራዊ ባንክ ሰራተኛ ነኝ ብለው ለመናገር እስከማይችሉ ድረስ ያሳፈረና ያሸማቀቀ፣ በባንኩ ሰራተኞች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሞራልና የሥነ-ልቦና ችግር የፈጠረ፣ ሰራተኞችና የስራ ሀላፊዎች በነጻነት ለመዝናናት ያልቻሉበት. . ". ሁኔታዎችን ፈጥሯል ብለዋል፡፡ አክለውም ". . . ስርቆቱ በረቀቀ ሁኔታ ሳይሆን ተራ በሚባል መንገድ መፈጸሙ የበለጠ አሳፋሪና መልስ ያሳጣን ሊሆን ችሏል. . . " ብለዋል፡፡ እናም ክስተቱ የዚህን ያህል ከተሰማቸውና ይሄ ሁሉ ጉድ የተፈጸመው ደግሞ እሳቸው የባንኩ ገዥ ሆነው ሳለ ተገቢውን ክትትል ባለማድረጋቸው ከሆነ ወንበሩ ላይ የሙጥኝ ማለትን ምን አመጣው? ምክንያቱም ከታች ያሉት ሰራተኞችና የስራ ሀላፊዎች በግልጽ ተቀምጧል በተባለው መመሪያና በስብሰባ ላይ ተደረሰበት በተባለው ስምምነትና በተፈረመው ቃለ-ጉባኤ መሰረት የወርቁን ግዢ እያከናወኑ ስለመሆኑ በቅርብ የመከታተልና የእርምት እርምጃዎችን መውሰድ የባንኪንግና የውጪ ምንዛሬ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሀላፊነት ብቻ ሳይሆን የገዢዎቹም ጭምር ስለነበር ከተጠያቂነት ነጻ ሊሆኑ የሚችሉበት አንዳንችም ምክንያት የለም፡፡ ስለሆነም ባንኩን በአግባቡ መምራት ባለመቻላቸው የተነሳ ለተከሰተው ችግር ሁሉ ሀላፊነቱን ወስደው ቦታቸውን መልቀቅ ሲገባቸው እኛን ሰብስቦ ህዳር ላይ የሰማነውን መርዶ መጋቢት ላይ እንደ አዲስ ላርዳችሁና ለቅሶ ተቀመጡ ማለት ስሜት የሚሰጥ አይመስለንም፡፡

ባንኩ በእንደዚህ አይነት የከፋ ችግር ውስጥ እያለ፣ የባንኩ ገዥ ጭምር እያመኑና ባንኩን ለዚህ ደረጃ ያደረሱት የባንኩ ገዢዎችና በዙሪያቸው ያሉት ጥቂት የስራ ሀላፊዎች ይሰጡ በነበረው አመራር መሆኑ እየታወቀ ከስር ያሉትን ጥቂት ሰዎች አስሮና በሙስና ወንጀል ከሶ ከላይ ያሉትን እንደልባቸው እንዲንቀሳቀሱና እንዲናገሩ ነጻ አድርጎ መተው ፍትሀዊ ውሳኔና አካሄድ አይመስለንም፡፡ ለባንኩም ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከበቂ ጊዜ በላይ መውሰዱ ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የባንኩ መሪዎች 10 እና ከዚያም በላይ የሆኑ አመታት ተሰጥቷቸው ባንኩን ሲመሩ ነበር፡፡ በእነዚህ አመታት ውስጥ ደግሞ የሰሯቸው ስህተቶች ተራ የሚባሉ ሳይሆኑ አገሪቱ በበርካታ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር እንድትከስር ያደረጉ ጥፋቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው መንግስት "ህመም ሲሰማዎ ሁለት ፍሬ ይውሰዱ" እየተባለ በሚታዘዝ ፓራሲታሞል በሽታውን ለማስታገስና ለማስታመም ከሚሞክር ይልቅ በአስቸኳይ ቀዶ ጥገና የበሽታውን ምንጭ በማስወገድ ያለበትን ሙሉ ኃላፊነት መወጣት አለበት የምንለው፡፡

ከሁሉም በላይ በእለቱ ስብሰባ ላይ የባንኩ ገዥ የተናገሩት ንግግርና ዛቻ ሰራተኛውን የበለጠ ያስቆጣ ጉዳይ ነበር፡፡ ይኸውም ሰራተኞች ከባንኩ ችግር ጋር በተያያዘ ዜናም ሆነ ሌላ ዘገባ ይዘው የሚወጡ ጋዜጦችን ለማንበብ እንደማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ ጋዜጣ ይገዛሉ፣ ያነባሉ፣ ይለዋወጣሉ፣ በጉዳዩ ላይ ይወያያሉ፡፡ እናም በአንድ በኩል በጋዜጦች (በተለይም በሪፖርተር) ላይ ጥርሳቸውን የነከሱትና በሌላ በኩል የሰሩትን ስህተት ለህዝብና ለመንግስት ይፋ የሚያደርጉና ለጋዜጦች መረጃ የሚሰጡ ሰራተኞች አሉ በሚል ንዴትና እልህ ውስጥ የገቡት የባንኩ መሪዎች በተለይም የባንኩ ገዥ" . . . ጋዜጣ ኮፒ እያደረጉ የሚያነቡ ሰራተኞች ማለት እናቱ ወይም አባቱ ወይም ሚስቱ ስትሰደብ እንደሚስቅ አይነት ሰው ሳዲስቶች ናቸው. . . የባንኩንም ድክመትና የውስጥ ችግር ለጋዜጣ መስጠት የሥነ-ምግባር ችግር ነው . . . እያንዳንዱ ሰራተኛ የሚያደርገውን እናውቃለን. . . እየተጠና ያለው ጥናት (BPR ማለታቸው ነው) ተጠናቆ ወደ ተግባር ሲገባ የሚንገዋለለው ይንገዋለላል. . . " ብለው በውስጣቸው ለወራት የቆየውን ቁጣና ከህዳር 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ያጋጠማቸውን ውጥረት ሰራተኛው ላይ ዘረገፉት፡፡

እያንዳንዱ ሰራተኛ የሚሰራውን ነገር ሁሉ በደንብ የሚያውቁ ከነበረ በወርቅ ፋንታ ባሌስትራ ሲገዛ አሳምረው ያውቁ ነበር ማለት ነው፡፡ በቢፒአር አስታኮ ዛቻ መሰንዘሩን "ሳታማሀኝ ብላ . . . " እንዳለው ዘፋኝ ወይም "ሊበሉ የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ነች ይሏት" እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ የማንበብና የመጻፍ መብት በህገ መንግስቱ ጭምር የተከበረ የሁሉም ዜጎች መብት ጭምር ነው፡፡ ከህግ አንጻርም ቢሆን አንድ ሰው የሚጽፈው ጽሁፍና በአደባባይ የሚናገረው ንግግር በበቂ ማስረጃ ተደግፎና የህዝብንና የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅና ለመከላከል እስከሆነ ድረስ ጽሁፉ ወይም ንግግሩ የግለሰብን ስም የሚያጠፋ ቢሆን እንኳን ከተጠያቂነት ነጻ ነው፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው ሰራተኛ እያደረ ያለውም ይሄንኑ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ድርጊት ሲከናወንና የተሰራው ስህተት ሲገለጽ ከጥፋቱ ጋር በተያያዘ የጥፋቱ መሪ ተዋንያኖች መጠቀሳቸው ገና ለገና ግለሰቦች ቅር ይሰኛሉ ተብሎ ተቋሙ ሲወድም ዝም ብለን ማየት አንችልም፡፡ እንዲያውም ከአሁን አሁን ነገሮች ይሻሻላሉ በሚል ተስፋ ስንጠብቅ ጊዜ አባክነናል፡፡

በማንኛውም ጋዜጣ ላይ ባንኩን አስመልክተው የሚዘገቡት ዜናዎች ወይም የሚጻፉት ጽሁፎች ትክክል አይደሉም፤ ብለው የሚያስቡና በቂ ማስረጃና ድፍረት ካላቸው እኛን ሰብስቦ ከማስፈራራትና "ሳዲስት" እያሉ ከመሳደብ በግልጽ አደባባይ ወጥቶ ማስተባበል ይገባቸዋል፡፡ ለነገሩ ይሄንን ለማድረግ ደግሞ አሳማኝና አኩሪ ስራ ሰርቶ መገኘት ያሻል፡፡
እኛም ሆንን ጋዜጦች እየጻፉ ያሉት የባንኩ መሪዎችና በዙሪያቸው ያሉት ጥቂት የማኔጅመንት አባላት የሰሩትና እየሰሩ ያሉት ጥፋት በባንኩና በአገር ላይ ያስከተለውንና በማስከተል ላይ ያለውን ውድመት ነው፡፡ ስለሆነም የራስን ማንነት ብሔራዊ ባንክ በሚለው ተቋማዊ ስያሜ ውስጥ ደብቆ ከተጠያቂነት ለማምለጥና እየተቻችሁና እያጋለጣችሁ ያላችሁት እኛን ሳይሆን ባንኩን ነውና "ነብር አየኝ በሉ" ብሎ ለማስፈራራት መሞከር የራስን የስብዕና ችግር የበለጠ እንዲታይ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ የባንኩን ጥፋት መንግስትና ህዝብ እንዲያውቀው ማድረግ በእነርሱ መለኪያ "የሥነ-ምግባር ችግር ነው" ብለውናል፡፡ በእርግጥ የሥነ-ምግባር ችግር ያለበት ሰራተኛውን ሰብስቦ በመንግስት የታዘዘውን መልእክት ብቻ ማስተላለፍ ሲገባው ጋዜጣ ለምን አነበባችሁ፣ ኮፒ እያደረጋችሁ ለምን ትለዋወጣላችሁ፣ የሰራነውን ስህተት ለምን አጋለጣችሁ በሚል ንዴት "ሳዲስት" ብሎ የሚሳደበው ሰው? ወይስ የሚጠበቅባቸውን ስራ እየሰሩ በአገሪቱ ህግ መሰረት ፍቃድ አውጥተው በገበያ ላይ የዋሉትን ጋዜጦች የሚያነቡትንና ሙስናን የሚዋጉትን ሰራተኞች?   

ለጊዜው ይሄንን በዚህ እናቁምና በ500 ሺህ ዶላር ተጠና ስለተባለው የመዋቅር ጥናትና ከጥናቱ ጋር በተያያዘ የባንኩ የስራ ሀላፊዎች ከባንኩ ጋር ውል ተፈራርመው ከ3 ሺህ እስከ 28 ሺህ ብር ወደተቀበሉበት አስገራሚ የክፍያ ጉዳይ እንለፍ፡፡

ባንኩ አጠቃላይ የመዋቅር ጥናት ያስፈልገዋል፤ ተብሎ በመንግስት 500 ሺህ የአሜሪካን ዶላር"ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ) ይፈቀድና ስራው በ1993 ዓ.ም. ይጀመራል፡፡ በጊዜው በነበረው አጠቃላይ ስብሰባ ላይም የባንኩ መሪዎች ጥናቱ በ8 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው ነበር፡፡ ሆኖም የተለያዩ ምክንያቶች ሲደረደሩና ጥናቱ ሲንዛዛ ቆይቶ ከ4 አመታት በኋላ በ1997 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ የሰራተኞች ምደባ ተደርጎ ስራው ተጠናቀቀ፡፡ መዋቅሩ የተጠናው KPMG በተባለ የውጪ አገር ኮንሰልታንት ቢሆንም የባንኩ መሪዎች ጥናቱን ከስር ከስሩ በአብዛኛው እነርሱ ወደሚፈልጉት ሁኔታ እየለወጡ አሁን የያዘውን መልክ ሊይዝ ችሏል፡፡ በተለይም በስራ ቦታዎች አከፋፈት፣ በስራ መደቦች ደረጃ አሰጣጥና በሰራተኞች ምደባ ጊዜ ጥቂት የባንኩ መሪዎች እነደፈለጉት እንዲሆን ያደረጉበት ሁኔታ እስካሁን ድረስ ቅሬታ እንደፈጠረ ይገኛል፡፡ ለዚህ ጥቂት ማስረጃዎችን ብቻ እንይ፡፡ በጥናቱ ጊዜ በመምሪያ ደረጃ እንዲሆን የታቀደውን አሁን የባንክ ሞደርናይዜሽንና የውጪ ግንኙነት ተብሎ የሚጠራውን ዳይሬክቶሬት በቦታው ላይ የሚቀመጡትን ግለሰብ በማሰብ በዳይሬክቶሬት የስራ መደብ ደረጃ 22 ሆኖ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ ሆኖም ዳይሬክቶሬቱ ላለፉት 3 አመታት ሲሰራ የነበረው ስራ በጣም ቢበዛ አንድ በደረጃ 16 ላይ የሚገኝ ዋና ክፍል ሊሰራ የሚችለውን ስራ መሆኑ ነገሩን የበለጠ ገሀድ አውጥቶታል፡፡ በሱፐርቪዥን ዳይሬክቶሬት ውስጥ ካሉት 3 መምሪያዎች ውስጥ ሁለቱ መምሪያዎች ደረጃ 20 ሲሰጣቸው ለባንኪንግ ሱፐር ቪዥን መምሪያ ስራ አስኪያጅነት የሚቀመጡትን ግለሰብ በማሰብ ከሁለቱ መምሪያዎች ነጥሎ ደረጃው 21 እንዲሆን መደረጉ፣ በባንኪንግና የውጪ ዳይሬክቶሬት ውስጥ ከሚገኙት 4 መምሪያዎች ውስጥ ሦስቱ ደረጃ 19 ሲደረጉ የሪዘርቭ ማኔጅመንት መምሪያ ግን ስራ አስኪያጅ ሊሆኑ የሚችሉትን ሰው በማሰብ ደረጃው 20 ተደርጓል፣ በኦዲት መምሪያ ውስጥ በፐርፎርማንስ ማኔጅመንት ኦዲት ዋና ክፍል ሀላፊነት ላይ ሊመድቡ ያሰቧቸውን ግለሰብ በማሰብ ደረጃው 18 ሲደረግ ለዚህኛውም ጉዳይ ሽፋን ለመስጠት እግረ መንገዳቸውን የሲስተም ኦዲት ዋና ክፍልንም ደረጃ 18 አድርገውታል፡፡ በመሰረቱ ግን እነዚህ ሁለት ዋና ክፍሎች በሌሎች መምሪያዎች ውስጥ በደረጃ 17 ወይም 16 ላይ ከተቀመጡት ዋና ክፍሎች የበለጠ ሀላፊነትና ስራ የላቸውም፡፡ ላለፉት 3 አመታትም ሲሰሩ አልታየም፡፡

እንደዚሁም በሞኒተሪ ፖሊሲ ዳይሬክቶሬት ውስጥ ሁለት የቅርብ ሰዎች በመኖራቸው ምክንያትና አንዱን ራቅ ባለ ደረጃ ላይ ለመመደብ ስለከበዳቸው ዳይሬክተርና ምክትል ዳይሬክተር በሚል ደረጃ 22 እና 21 ሰጥተዋል፡፡ በዚህ የተነሳ በሁለቱ መሀል በስራና በውሳኔ መተላለፍ /ቄባስቈ lapping/ ሲፈጠር ይታያል፡፡ እንደዚሁ በሰው ሀይል መምሪያ ውስጥ ብዙ ስራና ሪስክ ለሌለው ክፍል ደረጃ 13 ሰጥተው"አሁን በቅርቡ ስራው ከደረጃው ያነሰ ነው በሚል በቦታው ላይ ተመድበው የነበሩት ሰራተኛ ወደ ከረንሲ መምሪያ ተዛውረው ስራው ደረጃ 7 በሆነ ክለርክ እየተሰራ ይገኛል፡፡) በተቃራኒው ግን በዚያው መምሪያ ውስጥ ብዙ ስራና ሀላፊነት ያለውን ክፍል ደረጃ 11 አድርገውታል፡፡

ተጠና የተባለው መዋቅር ያለበት ሌላው ችግር የመጀመሪያ ዲግሪ ይዞ በሱፐርቪዥን፣ በሞኒታሪ ፖሊሲ ዳይሬክቶሬቶችና በሌሎች ጥቂት መምሪያዎች ውስጥ በደረጃ 9 ላይ የሚቀጠሩ ሰራተኞች ከሁለት አመት በኋላ በእድገት ደረጃ 11 ሲሆኑ፤ በውጪ ምንዛሬና ስታትስቲክስ መምሪያ ውስጥ የሚመደቡ ግን ከሁለት አመት በኋላ የሚቀመጡት በደረጃ 10 ላይ ነው፡፡ ከዚህ በተለየ ደግሞ በባንክ ሞደርናይዜሽንና የውጪ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ውስጥ በአቅም ማሻሻያ ዋና ክፍል ውስጥ ከደረጃ 9 ቀጥሎ ያለው ደረጃ 13 በመሆኑ በደረጃ 9 ላይ የሚቀጠሩ ሰራተኞች ምንም እድገት ሳይሰጣቸው  ለ4አመታት እንዲቆዩ ይገደዳሉ፡፡ ይሄ ሁሉ መዘበራረቅ የመጣው የሚሰራውን ስራ ሳይሆን ሰዎችንና መምሪያዎችን በማበላለጥ በተሰራ ተራ ስሌት ምክንያት ነው፡፡ እነዚህንና ከላይ የጠቀስናቸውን ተመሳሳይ የትምህርት መስፈርትና የስራ ልምድ ለሚጠይቁ የሥራ መደቦች እንዴት የተለያየ ደረጃ ሊሰጣቸው ቻለ? በሚል ለተነሳው ጥያቄ ስራውን የሰሩት ክፍሎች በጊዜው በሁሉም መምሪያዎች ውስጥ በቦታው ላይ የነበሩት የስራ ሀላፊዎች በሰጡት መረጃ መሰረት ዳታው ወደ ኮምፒውተር ሲገባ ፕሮግራሙ ራሱ አስልቶት ያስቀመጠው ደረጃ ነው ሲሉ፤ በተቃራኒው የተባሉት ሀላፊዎች ደግሞ ስራውን የሰሩት ሰዎች በራሳቸው መንገድ ያስቀመጡት እንጂ እኛ የምናውቀው ነገር የለም በሚል ሲወነጃጀሉ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ 500 ሺህ ዶላር ወጥቶ ጥናት ቢጠናም ጥቂት ሀላፊዎች የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ በሰሩት ስህተት ውጤቱ የወጣውን ወጪ ያህል ቀርቶ ግማሹን እንኳን ሳይሆን በከንቱ ቀርቷል፡፡ ባንኩም ከአዲሱ መዋቅር በኋላ በተጨባጭ ያመጣው ለውጥ የለም፡፡    
የተሰራው የሰራተኞች ምደባ ተጠናቆ ደብዳቤ ከተበተነ በኋላ ሁኔታውን አይተው በድርጊቱ በጣም ያዘኑትና የተቆጡት የባንኩ ሰራተኞች በምደባ ኮሚቴ ውስጥ ማህበሩ የወከላቸውን ሁለቱን የማህበር መሪዎች ጨምሮ የተቀሩትን የአመራር አባላት በሙሉ የተሰጣችሁን ሀላፊነት በአግባቡ አልተወጣችሁም፣ ከሰራተኛው ይልቅ የራሳችሁን ጥቅም በማስቀደም ከማኔጅመንቱ ጋር በመተባበር በደል ፈጽማችሁብናል፣ ይሄ ሁሉ ኢ-ፍትሀዊ ድርጊት ሲፈጸም አልተቃወማችሁም በማለት የስራ ጊዜያቸው ከማለቁ በፊት ከሀላፊነታቸው በማንሳት በምትካቸው አዲስ የአመራር አባላትን መርጠዋል፡፡

ጥናቱ በሚካሄድበት ጊዜ ወደ 5 የሚጠጉ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ነበር፡፡ እናም የተወሰኑ የባንኩ የማኔጅመንት አባላት በእነዚህ ኮሚቴዎች ውስጥ በመመደብ ጥናቱ ሲካሄድ ካውንተር ፓርት ሆነው ስለሚሰሩና ለሌሎችም የማኔጅመት አባላት ልዩ ክፍያ እንደሚያስፈልግ በመስማማት የተለያዩ የክፍያ መጠኖችን በማውጣት ጸድቆ ይቀመጥና ጥናቱ ከተጠናቀቀና የሰራተኞች ምደባ ከተደረገ በኋላ በ1998 ዓ.ም. ላይ ጉዳዩን እንደገና ከማስታወሻ ጋር ለባንኩ መሪዎች በማቅረብ ቡራኬ ካገኘ በኋላ ክፍያው ሊፈጸም ችሏል፡፡ በዚህም በአምስት ኮሚቴዎች ውስጥ በኮሚቴ ሰብሳቢነትና አባልነት በመሳተፍ ወደ 30 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ተከፋይ በመሆን የሰው ሀይልና የአስተዳደር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አንደኛ ሲሆኑ ወደ 20 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ በመቀበል የባንክ ሞደርናይዜሽንና የውጪ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሁለተኛ በመሆን ይከተላሉ፡፡ ሌሎችም እንደየቅደም ተከተላቸው እስከ 3 ሺህ ብር ድረስ የድርሻቸውን ተቀብለዋል፡፡ አስገራሚውም ነገር ይሄ ነው፡፡ የማኔጅመንት አባላት ስራ ማቀድ፣ ማደራጀት፣ መምራትና መቆጣጠር ነው፡፡ ለዚህ ስራቸው ደግሞ ደመወዝና ዘመናዊ መኪና ከነዳጅ ጋር ተሰጥቷቸዋል፡፡ እንደዚሁም ከታክስ ነጻ የሆነ የቦታ አበል ይከፈላቸዋል፡፡ እናም እንደ ማኔጅመንት የሚጠበቅባቸውን ስራ ለመስራት ተጨማሪ የክፍያ ውል መዋዋል ነበረባቸው?

ጉዳዩ ምን ያህል ትክክል እንዳልሆነ እያወቁ በስውር ለማድረግ እንደፈለጉ የሚያሳይ ድርጊት መፈጸሙን ክፍያው ከተከናወነና ሰራተኛው ሁሉ ካወቀው በኋላ ሊወጣ ችሏል፡፡ ይኸውም ክፍያውን ማንም ሰራተኛ ሳይሰማና ሳያውቅ ለመፈጸም ስራውን በመደበኛ የስራ ቀን ሳይሆን ቅዳሜና እሁድ የተወሰኑ ሰዎች ተመርጠው ገብተው እንዲሰሩ ከተደረገ በኋላ ሰኞ ጠዋት አስፈርመው ከአስተዳደር መምሪያ ክፍል እንዲወጣ ያደርጋሉ፡፡ ዝርዝሩንም ከአንድ ሰራተኛ ጋር አድርገው ተጨማሪ የሂሳብ ስራዎች ወደሚሰራባቸው መምሪያዎች ልከው ካስጨረሱ በኋላ ወደ አካውንታቸው ገቢ እንዲሆን ንግድ ባንክ ይልኩታል፡፡ ስራውም ከተሰራበት ክፍል ኮምፒተር ላይ ያሉት ዳታዎች ሁሉ እንዲጠፉ ካስደረጉ በኋላ ዶክሜንቶቹን በሙሉ ሌሎች ሰራተኞች እንዳያዩአቸው በሚል በአንድ ሀላፊ ቢሮ ውስጥ እንዲቀመጡ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ስራው ከላይ በዚህ ሁኔታ እንዲሰራ ትእዛዝ ያስተላለፉት የሰው ሀይልና የአስተዳደር አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክቶሬትም ሆኑ ጉዳዩን ለመደበቅ የሞከሩት ሰዎች የሚከፈላቸው ሀላፊዎች ስም ዝርዝርና የክፍያውን መጠን የሚገልጸው ሊስት ከስራው ጋር በተያያዘ የግድ ሌሎች ሁለት መምሪያዎች ውስጥ መሄድ እንዳለበት ያላወቁት ወይም የረሱት ጉዳይ ነበር፡፡ ሰራተኛውም ሁኔታውን ከሰማ በኋላ ክፍያውም ልዩና ለሌሎች ሰራተኞች አርአያ የሚሆን ስራ ተሰርቶ ለዚያ የሚሰጥ ማበራታቻ ሳይሆን በውል የተፈጸመ ስለነበር ክፍያው በመጀመሪያ ደረጃ እንዴት ሊፈቀድ ቻለ? ህጋዊ ከሆነስ መደባበቅና መሸፋፈን ለምን አስፈለገ? የሚሉ ጥያቄዎችን ቢያነሳም መልስ የሚሰጥ አካል አልነበረም፡፡

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው 500 ሺህ ዶላር ወጪ ተደርጎ ተሰራ በተባለው ጥናት አንዱን መሾሚያ ሌላውን መበቀያ አድርገው ለሰሩት ስራ ነው የሚመለከታቸው አካላት ነገሩን ህጋዊ ለማስመሰል ከባንኩ ጋር ውል ተዋውለው ከመንግስት ካዝና ብር ወጪ አድርገው የተከፋፈሉት፡፡ ድሮስ "አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ" ተብሎ የለ፡፡  እነርሱ እንደዚህ ባለ ሁኔታ እርስ በራሳቸው ውል እየተዋዋሉ የመንግስትን ገንዘብ የሚከፋፈሉ ከሆነ ሌላው ከውጪ መጥቶ በወርቅ ፋንታ ባሌስትራ ሸጦ የአገሪቱን ገንዘብ ቢዘርፍ ምን ያስደንቃል? እንግዲህ ይሄ አመራር ነው ከባንኩ መሪዎች ጋር ሆኖ የአገሪቱን ማእከላዊ ባንክ እያስተዳደረ ያለው፡፡ ታዲያ ለዚህ የባንኩ ገዳይ በሽታ መታዘዝ ያለበት ማስታገሻ የሚሆን ፓራሲታሞል ወይስ ዘላቂ ፈውስ ሊያመጣና በራሳቸው በባንኩ ገዥ አነጋገር መሰረት "ጋንግሪኑን" ቆርጦ ሊያስወግድ የሚችል ቀዶ-ጥገና?  

 
< Prev   Next >