|
Sunday, 04 May 2008 |
|
ኢትዮጵያና ጅቡቲ አደገኛ ኬሚካሎችንና ዝቃጮችን በጋራ ለመቆጣጠር ተስማሙ
ኢትዮጵያና ጅቡቲ በዓለም አቀፍ አካባቢ ስምምነቶች ላይ የጋራ የሆነ አመለካከት እንዳላቸው፣ በዚህም የተነሳ የአደገኛ ኬሚካሎችና ዝቃጮች ድንበር ዘለል ዝውውርን በኅብረት ለመከላከልና ለመቆጣጠር መግባባት ላይ መድረሳቸውን የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ትምህርትና ግንዛቤ መምሪያ ኃላፊ አስታወቁ፡፡
ኃላፊው አቶ ገብረሥላሴ ገብረአምላክ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንዳመለከቱት አጋራቱ ከዚህ መግባባት ላይ ሊደርሱ የቻሉት በካይ ንጥረ ነገር ያላቸው አደገኛ ኬሚካሎችና ዝቃጮች የሚመጡት በወደቦችና በደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች አማካይነት መሆኑን በማጤን ነው፡፡
የቁጥጥሩንና የክትትሉን ሥራ በጋራ ለማከናወን፣ ለዚህም እውን መሆን ለሁለቱም አገሮች የጉምሩክ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ አካባቢ ስምምነቶች ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማዳበሪያ አውደጥናት ለማዘጋጀት መስማማታቸውን አቶ ገብረሥላሴ አስረድተዋል፡፡
አቶ ገብረሥላሴ እንዳመለከቱት ኬሚካሎቹ በሦስት ይፈረጃሉ፡፡ በአንደኛ ደረጃ የሚፈረጁት ልዩ ልዩ ዓይነት ጦር መሣሪያ ለመሥራትና ለማዘጋጀት የሚያስችሉ አደገኛ ኬሚካሎች ሲሆኑ፣ የጉዳታቸው መጠን ዝቅ ያሉትን በሁለተኛነት፡ ምንም ጉዳት ሊያመጡ የማይችሉት ኬሚካሎችን በሦስተኛነት ተፈርጀዋል፡፡
በሰውና በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ አደገኛ ኬሚካሎች በምንም መልኩ ወደ አገር ውስጥ እንደማይገቡ፣ ለዚህም በየኬላው ጥብቅ ፍተሻና ክትትል እንደሚካሄድ፣ ኬሚካል የሚያመርቱ አገሮችም የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ዓለም አቀፍ ስምምነትን ተቀብለው ያፀደቁ ስለሆኑ ወደ ውጭ የመላክ ዕድላቸው በጣም የጠበበ እንደሆነ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
ይህ አይነቱ ስምምነት አደገኛ ኬሚካሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዳይመረቱና በሰውም ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለመከላከል እንደሚረዳ አቶ ገ/ሥላኤ ጠቁመው አደገኛ ዝቃጮች ድንበር ዘለል ዝውውርና አወጋገድን በተመለከተ የሚከታተልና የሚቆጣጠር ዓለም አቀፍ ስምምነት ደግሞ ዝቃጩን ከማምረት፣ ከመጠቀምና ከማዛወር ጋር በተያያዘ ያሉትን ጥንቃቄዎች ትኩረት እንደሚያደረግ አስታውቀዋል፡፡
|