|
አዲስ አበባን ከተላላፊ በሽታዎች ለመታደግ |
|
|
|
Sunday, 04 May 2008 |
 ዶክተር አቻሜሌህ አለባቸው በታደሰ ገብረማርያም በአዲስ አበባ ከተማ እስካሁን ድረስ በወረርሽኝ መልክ የተከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች የሉም፡፡ ነገር ግን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት፣ በባክቴሪያ የሚመጣ የደም ተቅማጥና ሚኒጃይትስ በወረርሽኝ መልክ ሊከሰቱ እንደሚችሉ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተላላፊ በሽታዎች መምሪያ ኃላፊ ገልፀዋል፡፡
ኃላፊው ዶክተር አቻሜሌህ አለባቸው እንዳብራሩት በተላላፊ በሽታዎች ላይም በቅኝትና በአሰሳ እንዲሁም በሰርቬይላይንስ አማካይነት ክትትል እየተደረገባቸው ነው፡፡ ክትትሉን በጥራት ለማካሄድ እንዲቻልም የአሰራር ሲስተም ተዘርግቷል፡፡
በሲስተሙ መሰረት በቢሮ የክትትልና ቁጥጥር ቡድን ተዋቅሮ በየክፍለ ከተሞቹ፣ በእያንዳንዱ የመንግሥትና በአብዛኛው የግል ሕክምና ተቋማት የሰርቬይላይንስ ማዕከል ተመስርቷል፡፡
ቡድኑ የራሱ የሆነ መመሪያ እንዳለው፣ በመመሪያውም መሰረት እንደበሽታው አይነት ወዲያውኑ፣ በየሳምንቱና በየወሩ ሪፖርት እንደሚያደርግ፣ እስካሁን ለቢሮው በደረሰው ሪፖርት መሰረት በአሁኑ ሰዓት ከተቅማጥ ጋር የተያያዘ ወረርሽኝ እንደሌለ፣ ወይም የወረርሽኝ በሽታ ተከስቷል የሚል ሪፖርት እንዳልደረሰ አስረድተዋል፡፡
አንዳንድ ወረርሽኞች ወቅታዊ (ሲዝናል) ናቸው፡፡ ስለሆነም ወቅቶቹ ሲደርሱ ይጠበቃሉ፡፡ ለምሳሌ በዓመት ውስጥ ወባ የሚከሰትባቸው ወቅቶች አሉ፡፡ ወቅቱን ጠብቆ የሚከሰተው ሌላው በሽታ ሜኔጃይትስ ነው፡፡ በአፍሪካ ሜኔጃይትስ ቤልት (ቀበቶ) የሚባል መስመር አለ፡፡ በዚህ ቀበቶ ውስጥ ያሉት አገሮችም ቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ሴኒጋል፣ ሴንትራል ሪፐብሊክ አፍሪካ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡
በዚህም ቀበቶ መስመር የሚገኙ እነዚህ አገሮች ሜኔጃይትስ የሚከሰትባቸው በደረቅ ወቅት (ድራይ ሊዝን) ነው፡፡ ይህም ማለት ከታህሳስ እስከ የካቲት፣ ካዛም ግንቦትና ሰኔ ነው፡፡ ስለሆነም በእነዚህ ወቅቶች የሜኔጃይትስ ወረርሽኝ መከሰት ይጠበቃል፡፡ ወረርሽኙ በአብዛኛው የሚከሰተው ከስምንት እስከ 15 ዓመት ባለው ኢንተርቫል (ጊዜ ውስጥ) መሆኑን ከልምድ ታይቷል፡፡
"በዚህም መሰረት ሜኔጃይትስ አዲስ አበባ ውስጥ ተከስቶ የነበረው እ.ኤ.አ በ2000 ይመስለኛል" ያሉት ዶ/ር አቻሜለህ አሁን ስምንት ዓመት እየሆነው ስለሆነ፣ ሀገሪቱም በሜኔጃይትስ ቤልት ውስጥ ስለምትገኝና ወቅቱም ደረቅና ሞቃታማ ስለሆነ በሽታው ሊከሰት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን እስካሁን ድረስ ወረርሽኙ አለመከሰቱን አስታውቀዋል፡፡
ይህ አይነቱን ወረርሽኝ የሚያስከትለውም ናይዜሪያ ሚኒጃቲዲስ የተባለው ባክቴሪያ ነው፡፡ ባክቴሪያው በአፍንጫና በጉሮሮ አካባቢ ባለው የመተንፈሻ አካል (ኒኮዘ) ላይ ይቀመጣል፡፡ በሽታና ሌላም ምልክት ሳያስከትል ከብዙ ሰዎች ጋር አብሮ ይኖራል፡፡ በደረቅና ሞቃታማ ወቅቶች ግን ባክቴሪያው የተቀመጠበት መተንፈሻ አካል የመቆጣት (ኢረቴት) እና የመሰነጣጠቅ ባህሪ ያመጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ባክቴሪያው ወደ ውስጥ የመሰረግና በሽታ የማምጣት ዕድል ያገኛል፡፡
ይህም በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው በትንፋሽ አማከይነት ይተላለፋል፡፡ ነገር ግን በቀላሉ መከላከልና ሊድንም ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው የመከላከያ ክትባት በመስጠት ነው፡፡ ለዚህም ሲባል የክትባት መድሃኒቶች ተዘጋጅተዋል፡፡ ክትባቱም የሚሰጠው በነፃ ነው፡፡
ከሁለት እስከ 30 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች ከ90 በመቶ በላይ የሜኔጃይትስ ተጠቂ ይሆናሉ፡፡ በአብዛኛው ተፋፍጎ የመኖር ሁኔታም ለበሽታው ይዳርጋል፡፡ ስለዚህ አካቢን በተቻለ መጠን ነፋሻና ንጹህ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ አይነቱም ሁኔታም አፍንጫና ጉሮሮ አካባቢ ያለው ኒኮዛ ኢርቴትድ እንዳይሆንና ኢንፌክሽን እንዳይፈጥር ይረዳል፡፡
የበሽታው ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታትና የአንገት መግረፍ (አንገት አለመታጠፍና ለመንቀሳቀስ መቸገር) ሲሆኑ የበሽታው ምልክቶች ሲታዩ ቶሎ ብሎ በአቅራቢያው ወደሚገኘው የሕክምና ተቋም ሄዶ መታየት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ከዶ/ር አቻሜለህ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የግልና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅን በሚመለከት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማዳበሪያ ትምህርት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ኃላፊው አመልክተው ትምህርቱ መሰጠት ያለበት ወረርሽኝ በተከሰተ ቁጥር ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት መቀጠል እንደሚኖርበት፣ ለዚህም እውን መሆን የደንብ ማስከበር መዋቅር ሊያሰራ የሚያስችል አቅም እንዲኖረው ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
በጤናው ቢሮ በኩልም የኢንቫይሮመንታልና ሳኔቴሺን ዲፓርትመንትን ማዋቀር እንደሚያስፈልግ እስካሁን ድረስ ያለው ግን በዲፓርትመንት ደረጃ ሳይሆን በኤክስፐርት ደረጃ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ |