|
Sunday, 04 May 2008 |
 አቶ አወል ኑር ሁሴን በታደሰ ገብረማርያም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች እ.ኤ.አ እስከ 2015 ድረስ ትምህርት ለሁሉም ለማዳረስ ለሚያካሂዱት እንቅስቃሴ ስኬታማነት በየዓመቱ በአማካይ 11 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ገንዘቡም ይገኛል ተብሎ የታሰበው ከዕርዳታ ሰጪ አገሮችና ከሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲሆን ለጋሽ አገሮችና ድርጅቶቹ ግን በሚፈለገው መልኩ እንዳልረዱ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የባህልና የትምህርት ድርጅት (ዩኒስኮ) ሚያዚያ 10 ቀን 2000 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ይፋ ማድረጉን የመሠረታዊ ትምህርት ማኅበር በኢትዮጵያ የፖሊሲ ሪሰርችና አድቨኩሲ ኦፊሰር አስታወቁ፡፡
ኦፊሰሩ አቶ አወል ኑር ሁሴን መግለጫውን ጠቅሰው ለሪፖርተር ጋዜጣ እንዳመለከቱት፣ የዓለም መንግሥታት እ.ኤ.አ በ1990 በታይላንድ ጃንቲክ ከተማ ስብሰባ አድርገው እ.ኤ.አ እስከ 2000 ድረስ ትምህርት ለሁሉም ዜጋ በሚያመቸው መልኩ ለማዳረስ ተስማምተው ነበር፡፡ ውጤቱ ሲገመገም ግን ከ115 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትና ከ875 ሚሊዮን በላይ አዋቂዎች ማንበብና መጻፍ እንደማይችሉ ተረጋገጠ፡፡
በዚህም የተነሳ እ.ኤ.አ በ2000 ኢትዮጵያን ጨምሮ 180 አገሮች ሴኔጋል ዳካር ላይ ተሰብስበው እ.ኤ.አ እስከ 2015 ድረስ ትምህርት ለሁሉም የሚለውን መርህ ለማሳካት፣ አንድም አገር ገንዘብ አጠረኝ ብሎ እስከ 2015 ድረስ ትምህርት ለሁሉን መርህ ሳያሳካ መቅረት እንደሌለበት፣ ቅድመ መደበኛ የሕፃናት እንክብካቤና ትምህርትን በተለይ እጅግ ተጋላጭ ለሆኑ ሕፃናት እንዲሁም ጥራት ያለው ነፃና አስገዳጅ (ኮምፖልሳሪ) ትምህርት ለሁሉም በተለይ ለልጃገረዶች፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሕፃናትና ለአናሳ ብሔረሰብ አባላት ለማድረስ ተስማምተዋል፡፡
የወጣቶችና ጎልማሶች የትምህርት ፍላጎት ተገቢና ተግባር ተኮር ክህሎቶችን በሚያቀርብ መልኩ ምላሽ ማግኘቱን ለማረጋገጥ፣ ቀጣይነት ባለው መልኩ የጎልማሶችን የትምህርት ዕድል እ.ኤ.አ እስከ 2015 በ50 በመቶ ለማሳደግ፣ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ የሚታየውን የፆታ አለመመጣጠን ለማጥፋት፣ በትምህርት መስክ የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን፣ በስብሰባውም ላይ የተገኙት ዕርዳታ ሰጪ አገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለፕሮግራሙ መሳካት የገንዘብ አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አቶ አወል ገልፀዋል፡፡
ቃላቸውን ጠብቀው አስር በመቶ ያህሉን ዕርዳታ ለመሠረተ ትምህርት ያዋሉት ኔዘርላንድስና ኒዊዚላንድ ብቻ መሆናቸውን አቶ አወል አመልክተው፣ የቀሩት በገቡት ቃል መሠረት በሚፈለገው መልኩ አለመርዳታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ስለሆነም በጥቅሉ ሲታይ እ.ኤ.አ በ2004 አምስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር፣ በ2005 ሦስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር፣ በ2006 አምስት ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ መገኘቱን፣ ከዚህም ውስጥ በ2006 የተሰጠው የዕርዳታ መጠን በ2004 ከተለገሰው ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዕርዳታ ሰጪ አገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሰጡት ዕርዳታ በተፈለገው መልኩ ባይሆንም ኢትዮጵያ ግን ትምህርት ለሁሉን እ.ኤ.አ እስከ 2015 ድረስ ሙሉ ለሙሉ እንደምታሳካ የሚያረጋግጡ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፡፡ ባለፉት አስርና አስራ አምስት ዓመታት በትምህርቱ ዘርፍ ብዙ መሻሻሎችና ለውጦች ታይተዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው መረጃ እንደሚያሳየው በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርቱ ሽፋን 91.3 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ እስከ 2000 ያለው ሲታከልበት ሽፋኑ ከፍ ይላል፡፡
በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አካባቢዎች ከ10 ዓመት በፊት ስድስት በመቶ የነበረው የትምህርት ሽፋን አሁን ከ30 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ በአማካይ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት እየገቡ ነው፡፡ የትምህርቱ እንቅስቃሴ በዚህ ፍጥነት ከቀጠለ፣ በትምህርት ሥራ ላይ የተሠማሩት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች አካላት ከተረባረቡ በ2015 ትምህርት ለሁሉም ይዳረሳል (ኢትዮጵያ ግቧን ትመታለች) ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ትምህርት ለሁሉምን እ.ኤ.አ እስከ 2015 ድረስ ለማሳካት ከተፈለገ አሁን ዕድሜያቸው 7 ዓመት የሆኑ ሕፃናት በዘንድሮና በሚቀጥለው ዓመት ትምህርት ቤት መግባት ይኖርቸዋል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓመት ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት እ.ኤ.አ በ2015 ስምንተኛ ክፍል ገብተው መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡
አቶ አወል እንዳመለከቱት "ጥራት ያለው ትምርት ለሁሉም፣ ከእንግዲህ መገለል ይብቃ" የሚል መሪ መፈክር ያነገበው የዓለም አቀፍ የትምህርት ዘመቻ ሁለት ቁልፍ ጉዳዮችን ይዟል፡፡ አንደኛው የትምርት ጥራት ሲሆን ሌላው ደግሞ በተጓዳኝ የተተኮረበት ከትምህርት የተገለሉ ወይም ትምህርት የተነፈጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ትምህርት ቤት የማምጣትን አስፈላጊነት በአጽንኦት የሚያስታውስ ነው፡፡
ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት ከትምህርት የሚገለሉባቸው ወይም የትምህርት ዕድል የሚነፈጉባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም ምክንያቶች መካከል አንደኛው አካል ጉዳተኝነት፣ የአስከፊ ድህነት ጫና፣ የሥርዓተ ፆታ መድልዎና የታዘበ አስተሳሰብ፣ ከመሀል አገር መራቅ፣ ለጉልበት ብዝበዛ መዳረግ፣ ወላጆችን ማጣትና ለተጋላጭነት መዳረግ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ምንም እንኳን በሥርዓት የተጠናቀረ መረጃ ባይኖርም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጠናቀሩ መረጃዎችን መሠረት ባደረገ ግምት ቁጥራቸው ከ1.7 ሚሊዮን እስከ 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ የልዩ ፍላጎት ትምህርት አቅርቦት የሚሹ ሕፃናት እንደሚገኙ ይታመናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር አሀዛዊ መረጃ እንደሚጠቁመው እ.ኤ.አ እስከ 2006 ድረስ በአገሪቱ ውስጥ ያሉት የልዩ ትምህርት ተቋማት በቁጥር 17 ያህል ብቻ ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 11 ያህሉ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡
ይኸው ሰነድ መደበኛ ትምህርት በሚሰጡ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተከፈቱ 285 የልዩ ፍላጎት ትምህርት መስጪያ ክፍሎች እንዳሉ ያመለክታል፡፡ ይህም ሆኖ በትምህርት መረጃ፣ በበጀትና በብቁ መምህራን አቅርቦት፣ እንዲሁም በክትትል ረገድ ከመደበኛ የትምህርት መስጫ ተቋማቱ አንፃር ለእነዚህ ለልዩ ፍላጎት ትምህርት መስጪያዎች የሚሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ መሆኑን አቶ አወል ገልፀዋል፡፡
"የትምህርት ጥራት የሚለካውም ጥራት ያለው ትምህርት ለማቅረብ አስፈላጊ መሆናቸው በስፋት የሚታመንባቸው ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ ሲሟላ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጡ የትምህርት ጥራት መለኪያዎች አማካይነት ነው" ያሉት ኦፊሰሩ የትምህርትን ጥራት እውን ለማድረግ አስፈላጊ ከሆኑ አላባውያንና ግብዓቶች መካከል የመምህራን ብቃት፣ የተማሪና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች (መጻሕፍት ወዘተ) ጥምረት እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡
ከዚህም ሌላ የተማሪና የአስተማሪ፣ የተማሪና የክፍል ጥምርታዎች፣ የመማር ማስተማር ሂደት፣ ለትምህርት ዘርፍ በአጠቃላይና ለትምህርት ግብዓቶች የሚመደብ በጀት ወዘተ. ለትምህርት ጥራት አስተዋጽኦ እንዳለው አቶ አወል አመልክተው ጥራት ያለው ትምህርት መገለጫዎች ደግሞ የተማሪዎች የትምህርት ውጤትና በተማሪ ሕይወት ላይ የሚታዩት ለውጦች እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡ |