| አዲሱ የኘሬስና የመረጃ ነፃነት... |
|
|
| Thursday, 10 January 2008 | |
|
አዲሱ የኘሬስና የመረጃ ነፃነት ሕግ አላስፈላጊ ገደቦችና ጣልቃ ገብነቶች አሉበት አዲሱ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት ሕግ በጋዜጠኞች ላይ አላስፈላጊ ገደቦችንና ቅጣቶችን በመጣል ላይ ያተኮረና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን የመፃፍና የመናገር መብት ሥጋት ላይ የሚጥል መሆኑ ተጠቆመ፡፡ ሕጉ በኘሬስ ሥራ ላይ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶች የሞሉበት መሆኑም ተገልጿል፡፡ ይህ የተመለከተው በፓክት ኢትዮጵያ አማካኝነት በህዳር 2ዐዐዐ ለውይይት የቀረበው ረቂቅ አስመልክቶ ከግልና ከመንግሥት መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተዘጋጀ ውይይት ላይ ነው፡፡ በውይይቱ በህጉ ላይ አስተያየት የሰጡ የህግ ባለሙያዎች እንዳሉት ረቂቅ ህጉ በወቅቱ ያለውን የመንግሥት የማስፈፀም አቅምና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን የብቃት ደረጃ ከግምት ያላስገባ ነው፡፡ የህግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አቶ ሰለሞን በርናባስ በዕለቱ እንዳሉት የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት ረቂቅ ህግ በርካታ አንቀፆች ጋዜጠኞች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ የመገደብ አዝማሚያ ይታይባቸዋል፡፡ የትርጉም አሻሚነት በረቂቁ መኖሩን አቶ ሰለሞን ሲገልፁ በምሳሌነት ያስቀመጡት በረቂቁ መረጃ ለሚለው ሀሳብ ሰነድ የሚለው ትርጓሜ አስጠቱን ነው፡፡ በዚሁ ሰነድ በሚለው ዝርዝር ትርጉም ውስጥ ደግሞ ከመረጃ ጋር የማይያያዙና ከምስጢራዊነት ጋር የተያያዙ ዝርዝሮች መኖራቸውን ይኸውም በመረጃ አሰጣጥ ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ ህጉ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 እና 13 በመፃፍና በመናገር ነፃነት ላይ የተደነገጉ ህጐችን ያላገናዘበና የሚፃረር ነው ያሉት አቶ ሰለሞን ህጉ ጋዜጠኛው ተለማምጦና ላይ ታች ብሎ መረጃ ማግኘት አለበት የሚል አንድምታ ያለው መሆኑንና በጋዜጠኛው በነፃነት የመስራት ሁኔታ ላይ ችግር የሚፈጥር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ህጉ በአብዛኛው የመገደብ አዝማሚያ ያለው መሆኑን ሲገልፁ ከአንቀፅ 13-25 ያለውና የረቂቁ ዋናው አካል ሊባል የሚችለው ክፍል የሚገድቡ አንቀፆችን የያዘ ነው ካሉ በኋላ መገደብ አስፈላጊ ቢሆን እንኳን እንደ ረቂቅ ህጉ ዋና አካል ሳይሆን መጨረሻ ላይ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ነጥብ ተደርጐ ሊቀመጥ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም በረቂቅ ህጉ የተከለከሉ የመንግሥት ሰነዶች ብዛት መንግሥት የሚሠራው ሥራ በሙሉ ምስጢር እንደሆነ ያስመስላል ያሉት አቶ ሰለሞን ፣የመንግሥት ሥራ ከህዝብ ምስጢር ነውን?፣ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ቅጣትን በተመለተም በወንጀል ህጉ የተካተተ በመሆኑ ጋዜጠኛው ጥፋት ቢሰራ ሊጠየቅበት እንደሚችልና በረቂቅ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት ህጉ ይህንን በድጋሚ ማካተቱ አላስፈላጊ መሆኑንና ፣ሁለት ጊዜ ሊቀጣ ነው?፣ የሚል ጥያቄ እንደሚያስነሳ አስረድተዋል፡፡ በለንደን በማስተማርና በምርምር ሥራ ላይ መሠማራታቸው የተገለፀው ዶ/ር እንዳርጋቸው ጥሩነህ (የህግና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ) በበኩላቸው በረቂቅ ህጉ ላይ አላስፈላጊ የሆኑ ጣልቃ ገብነቶች በስፋት እንደሚታዩ ገልፀዋል፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 መሠት ከተጠቀሱ አራት ዋና ዋና ምክንያቶች ማለትም የወጣቶችን ደህንነት ለመጠበቅ፣ የዜጐችን መልካም ስምና ዝና እንዲሁም ኘሮፖጋንዳን የመቃወምና ገደብ የሚጥል ህግ ማውጣት አይቻልም ብለዋል ዶ/ር አንዳርጋቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ምዝገባን በተመለከተ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር መሠጠቱ አግባብ አለመሆኑን ይህና ሌሎች ምክንያቶች በረቂቅ ህጉ ሚዲያው ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የተፈለገ መሆኑን የሚጠቁሙ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡ ፣በዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት ኘሬሶች ቢያጠፉ ካሳ ይከፍላሉ እንጂ ቅጣት አይቀጡም፣ ካሉ በኋላ ረቂቁ ቅጣትን የያዘ መሆኑ ሊቀር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በቤተልሔም ነጋሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |