| የ"ጥሩ እና በቂ" የፕሬስ ሕግ... |
|
|
| Wednesday, 07 May 2008 | |
|
የ"ጥሩ እና በቂ" የፕሬስ ሕግ ረቂቅ ግብና ዓላማ ምንድነው?
(አስፋው ነጻነት) ሕግ አውጪው አንድን ሕግ የሚያወጣው፤ የሚያፀድቀው አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ዓላማዎች ይዞና ጨብጦ ነው፡፡ ሊደርስባቸው በሚፈልጋቸው ዓላማዎችና ግቦች ላይ ከወዲሁ አነጣጥሮ፣ አልሞ፣ ለአተረጓጐማቸው ወጥነት ለተፈጻሚነታቸው እርግጥኛነት ተጠቦና ተጨንቆ መሆን አለበት፡፡ በዚህም ምክንያት የማናቸውም የሕግ ሀሳብ የማመንጨት፣ ሕግ የማርቀቅ ሂደት ከዚያ መነሳት እነዚህ ግቦችና ዓላማዎች ምንድናቸው የሚለውን ጥያቄ በግልጽ አውጥቶ በማስተጋባት፣ ለራሳቸው አፍ ሰጥቶ በማናገር (አርቲኩሌት በማድረግ) መጀመር አለበት፡፡ ይህ ደግሞ የፖሊሲ አራማጁን ሀሳብ፣ ምኞትና እቅድ፣ ዓላማና ግብ በየትኛውም ደረጃ ቁልጭ አድርጐ በማሳወቅና በማስተጋባት የተወሰነ ፋይዳ ያለው ብቻ አይደለም፡፡ የታቀደውን የሕግ ሀሳብና የሕግ ረቂቅ የመጀመሪያ ደረጃ ወይም ከሁሉም በፊት ያሉ ቀዳሚ ተደራሲዎችን (ማለትም ሕግ አውጭውን እንደ አካል የምክር ቤት እንደራሴዎችን እንደግለሰብ) በእጅጉ ያግዛል የሕጉ ተደራሲዎች ግን የሕግ አውጪው አካል አባል የሆኑት እንደራሴዎች ብቻ አይደሉም፡፡ የሕጉ “የመጨረሻ” የሚባሉ ዋነኛ ተደራሲዎች የሚባሉም ዓይነተኛ ባለ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም ለምሳሌ የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ሲሆን ሠራተኞችና አሰሪዎች የፕሬስ ሕግ ሲሆን ጋዜጠኞችና ሕዝቡ ናቸው፡፡ አንድ የሕግ ሀሳብ፣ ወይም የሕግ ረቂቅ በስተጀርባ ያለው ዓላማና ግብ፣ እንዲሁም ከዚህ በተጨማሪ፣ ፖሊሲና መርሆዎች ቁልጭ ብሎ መውጣት፣ ልቅም ብሎ መታየት ያለበትና ይህም በመሆኑ ፋይዳው ለዚህ ተብሎ ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህን ዓላማዎች ግቦች ፖሊሲዎችና መሠረታዊ መርሆዎች አጉልቶ ማውጣት ቁልጭ አድርጐ ማሳየት የታደለና የቻለ የፀደቀ ሕግ የሕጉን አተረጓጐምና አፈጻጸም የማረጋገጥ ስልጣንና ግዴታ የተጣለባቸውን የዳኝነትና የአስተዳደር የሥልጣን አካላትም በእጅጉ ያግዛል፤ የዓለም የፕሬስ ቀን በተከበረበት በዘንድሮው የሜይን ዋዜማ አካባቢ ከአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና በእነዚህ ፓርቲዎች አማካኝነት የፓርላማ መቀመጫ ከያዙ እንደራሴዎች በኩል የተሰማ አንድ ዜና የፕሬስ ሕጉ ረቂቅ ለፓርላማ እንዲቀርብ መስማማታቸውን አርድቶናል፡፡ ረቂቅ አዋጁ “ጥሩ እና ጠቃሚ” መሆኑንም ጭምር ማረጋገጣቸውን ሰምተናል፡፡ ወደ ፓርላማ እንዲቀርብ የኢህአዴግን፣ የኢዴፓ መድህንን የቅንጅትን፣ (እንዲሁም የፓርላማ ቡድን) የፓርላማ ተጠሪዎች ስምምነት ያገኘውና ጥሩና ጠቃሚ ነው የተባለው የፕሬስ ህጉ ረቂቅ በ1985 ዓ.ም የወጣውን የፕሬስ አዋጅ ቁጥር 34/85 እንደሻረና እንደተካ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ተረቅቆ በየጊዜው እንደገና “እየተሻሻለ” የመጣውና አሁንም 2000 ላይ ፀድቆ እንዲወጣ የሚፈለገው የሕግ ረቂቅ (የተባለው) ነው፡፡ ፓርላማ ውስጥ መቀመጫ ያላቸው (ከኢህአዴግ ውጭ ያሉት) ፓርቲዎች በረቂቅ ሕጉ ላይ ከአንድም ሁለት ጊዜ በስፋት እንደተወያዩበት ብዙ ማሻሻያዎች እንደተደረገበት አሁን ባለው ደረጃ ጥሩና ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት አገላለጽና ከቅርጽ አኳያ ብቻ ጥቃቅን አለመግባባቶች ከመታየቱ በስተቀር አዋጅ ሆኖ ከመውጣት የሚያግደው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል ተብሏል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ እነዚህ ሰዎች የማቀርበው አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ለመሆኑ “ጥሩና ጠቃሚ” ሆኖ ያገኙት የፕሬሱ ረቂቅ ሕግ ዓላማና ግብ ምንድነው? የሕጉን ረቂቅ ብዙ ማሻሻያዎች እንደተደረገበት በአሁኑ ደረጃ ጥሩና ጠቃሚ መሆኑን እንደመሰከሩለት ዜናውን ያስነበበን ጋዜጣ ከዚህ በላይ የሰጠው ሰፊና ዘርዘር ያለ መግለጫ የለም፡፡ ይህ ማለት ግን ዜናው ስማቸውንና አቅማቸውን እንዲሁም መግለጫቸውን መሠረት አድርጐ የዘገበላቸው ሰዎችና ፓርቲዎች (በተለይም የተቃዋሚዎቹ) ሀሳብ ይህ ብቻ ላለመሆኑ በእርግጠኛነት ለመናገር የሚያስችል መረጃ የለኝም፡፡ በአንጻሩ ግን እነዚህ ፓርቲዎች ይህን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ (ዓርብ ሚያዚያ 17 ቀን 2000) የወጣውን ዜና እና መግለጫቸውን ተከትሎ ያወጡት መግለጫ ያን አልሰማሁም የለምም፡፡ ስለፕሬስ ነጻነት የወጣው አዋጅን (አዋጅ ቁጥር 34/85) የመሰለ ሕግ በ2000 ዓ.ም “የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት ረቂቅ አዋጅ” በተባለው እንዲሻርና እንዲተካ የቀረበውን የሕግ ሀሳብ “ጥሩና ጠቃሚ” ነው አሉ ሲባል ምክንያቱ ምንድነው? የትኛውን የ1985 ሕግ “መጥፎ” በየትኛው የ2000 ረቂቅ ሕግ “ጥሩ” ለመሻር ነው? በየትኛውስ የ1985 ሕግ “ጉዳት” ፋንታ የትኛውን የ2000 ረቂቅ “ጥቅም” ለመተካት ነው? ይህን እኛም በወቅቱና ከዝርዝር የማወቅ መብት እነሱም በግልጽና በቀጥታ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ስለፕሬስ ነጻነት የምንከራከረው፣ የነጻነቱ ወሰንም እየሰፋ ሊሄድ ይገባዋል የምንለው የፕሬስ ነጻነት ሕግም ሆነ የፕሬስ ነጻነት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ያላቸው ሕጐች (እንደማናቸውም ሌላ ሕግ) “ጥሩነትና ጠቃሚነት” ከጀርባቸው ባስከተሉት በውስጣቸው ባረገዙት ዓላማና ግብ አንጻር ሊነገረን ይገባል፡፡ ነባሩ እና በየጊዜውና ቀስ በቀስ እየተገዘገዘ፣ እየተቆራረጠ ቁርጥራጩ ለየብቻው እየተገነዘ የሄደው የ1985ቱ የፕሬስ ሕግ.. ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው፣ ነጻ የሆነና የተጠናከረ ፕሬስ ሲኖር ሲጐለብትና ሲስፋፋ መሆኑን ነጻ ፕሬስ ዜጐች ረዜጐች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ሰው ተብሎ መሻሻል አለበት ባይ ነኝሪ ሃሳባቸውን በነጻ የሚገልጹበት መድረክ ከመሆኑም በላይ የግለሰቦችና የሕዝቦች መብት እንዲከበርና ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር በማድረግ እንዲሁም ዜጐች በተለያዩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በመንግሥት አመራርና አሠራር ላይ ሀሳብ እንዲያቀርቡ በማስቻል ጉልህ የሆነ ሚና የሚጫወቱ መሆኑን ፕሬስ ይህንን ተግባሩን ሊያከናውን የሚችለው የቅድሚያ ምርመራ (ሴንሰርሽፕ) እና ሌላም ተመሳሳይ ገደብ ሳይደረግበት በነጻና በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ሲፈጠርለት መሆኑን ያውጃል፡፡ በዚህ መግቢያው አማካኝነት ያስተጋባው የመርህ እና ከሞላ ጐደል የዓላማና ግብ መንደርደሪያ የቀረውና መሻሻል የሚገባው ነገር አለ ወይ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሱ አዎ በእርግጥም አለ የሚለው ነው፡፡ ከእነዚህ መሻሻል ካለባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የፕሬስ ነጻነት መብት የዜጐች ብቻ አለመሆኑን ተከታትሎ ሊኖር የሚገባው ማሻሻያ አንዱ ነው፡፡ የመንግሥት አመራርና አሰራር ላይ ሀሳብ በማቅረብ ላይ መወሰን የለበትም የምንለው የፕሬስ ሚና በዚሁ ላይ “ዘብ የመቆም”ን (የወች ዶግ) የመመርመርንና የማጋለጥንም እንዲያካትት እንሻለን፡፡ ፕሬስ የተባለውን ሁሉ ተግባር ሊያከናወን የሚችለው “የቅድሚያ ምርመራ እና ሌላም ተመሳሳይ ገደብ ሳይደረግበት” በነጻ ሲንቀሳቀስ ብቻ ነው የሚለውም በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተብራርቶ መገለጽና መዘርዘር ያለበትስ ለመሆኑ ያለፉት 15 ዓመታት እጅግ በጣም ብዙ እንዳስተማሩን እናውቃለን፡፡ በህትመት ፕሬስና በኤሌክትሮኒክስ ፕሬስ መካከል በፈቃድ እና በምዝገባ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ሳያውቁ መቅረት፣ እምቢ አላውቅም ማለት አልበቃ ብሎ የ”የሞያና የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት” ተጨማሪ የሕግ እና የአስተዳደር ሁከት የፈራው “የቅድመ ምርመራና ማናቸውም ሌላ ተመሳሳይ ገደብ በዚህ አዋጅ ተከልክሏል” በሚለው በአዋጁ አንቀጽ 3(2) አማካኝነት (ኋላም በህገመንግሥቱ አንቀጽ 29) በመንግሥት ላይ የተጣለው ገደብ ባለማወቅም በማን አለብኝነትም ስለሚጣስ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ብቻ ሳይሆኑ የማሻሻያ ሕጐችም መንግሥትን እዚህ “ፊንጃ ወረዳ” ውስጥ እንዲገባ ሲያደርጉት ይታያሉ፡፡ የፈቃድ ሕጐች በሌላው ዓለምም በኢትዮጵያም የሳንሱርና የ “ሌላ ተመሳሳይ ገደብ” አካል ሆነው ያገለገሉበት ወቅት ጥንት ዱሮ የቀረ ወይም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ቢሆንም አሁንም በየቦታው መልክ እየቀየሩ መምጣታቸው አልቀረም፡፡ የብቃት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን በተለይም የህትመት ፕሬስ የፈቃድ አስፈላጊነትና ግዴታ ህግም የዚህ ምሳሌና ማስረጃ ነው፡፡ በፈቃድና በምዝገባ መካከል ያለው ልዩነት የተምታታ ይልቁንም ጭራሽ የማይታወቅ መሆኑም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ስለዚህም ለምሳሌ ያህል “የቅድሚያ ምርመራ በማናቸውም መልኩ የተከለከሉ መሆኑን” በሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ እና “የቅድሚያ ምርመራና ማናቸውም ሌላ ተመሳሳይ ገደብ በዚህ አዋጅ ተከልክሏል” የሚለው የ85ቱ የፕሬስ ሕግ የፖሊሲ ዓላማና ግብ ዳር ድንበር ምንድነው እያልን እንጠይቃለን፡፡ እነዚህን በመሳሰሉ ድንጋጌዎች አማካኝነት በመንግሥት ላይ የተጣሉ ገደቦችን በመጣስ የማንኛውም ዴሞክራሲ መሠረታዊ መርሆዎች ከሆኑት መካከል አንዱ “የተገደበ መንግሥት” ወይም ሊሚትድ ገቨርንመንት መሆኑን በመርገጥ፣ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 29(60) እና 13(2) እንደሌለ በመቁጠር “የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ሌሎች የላቁ መብቶችን ለማስጠበቅ ሲባል በግልጽ በሚደነገጉ ሕጐች ብቻ ሀሳብን በነጻ በመግለጽና በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ላይ ገደቦች እንዲጣሉ የሚያዘውን ህገመንግሥታዊ መርህ በአንድነት በማረጋገጥ” የሚል መግቢያ ያለው ረቂቅ ሕግ ዓላማና ግብ “ጥሩነትና ጠቃሚነት” ለማነው? ለዴሞክራሲያችን ወይስ “ለግዴታ ግንባታችን”? በስፋት እንደተወያዩበት ብዙ ማሻሻያዎች እንደተደረገበት አሁን በሚገኝበት ደረጃ ጥሩና ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ስለመሰከሩለት ስለ ረቂቁ ሕግ፣ እንደራሴዎቻችንን የምጠይቃቸው ሌላው አመላካች ጥያቄ ረቂቅ ሕጉ ከዚህ ቀደም ስለ የምክር ቤቱ የአሰራር ደንብ ስለ ምርጫ ቦርድ ህግ (እንዲሁም ስለሚዲያ ህግ) እንደተባለውና ቃል እንደተገባው የውጭ ኤክስፐርቶችና ባለሙያዎች አጥንተው ባቀረቡት ጥናትና ሪፖርት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነወይ? የሚለውን ነው፡፡ የፓርላማው የአሰራር ደንብ እና የምርጫ ህጉ ብዙም የተለየ እድል ባያጋጥማቸውም እንደ ፕሬስ ህጉ የውጭ ባለሙያዎችን ጥናትና ሪፖርት “መደበቅ” ወይም እንዳልነበረ መቁጠር ድረስ ርቀው አልሄዱም፡፡ ከዚያ ጥናት ምን ተገኘ? ሌላም ጥያቄ አለ፡፡ በተለይም ብዙ ማሻሻያዎች ተደረገበት የተባለው ሕግ ረቁቅ ዋነኛና ዓይነተኛ ድንጋጌዎች በተለያዩ ሕጐች አማካኝነት ከፀደቁ በኋላ ከዚህ ረቂቅ ህግ ውስጥ የወጡ ናቸው፡፡ በአንድ አገር የፕሬስ ረቂቅ ላይ የሚወያይ፣ ረቂቅ ጥሩና ጠቃሚ ነው የሚል እንደራሴ ወንጀል ህጉን ያም ቢቀር ወንጀል ህጉ ውስጥ የገቡትን የረቂቁ ህግ አካል የነበሩትን ድንጋጌዎች በዝምታ አልፎ በስፋት ስለተወያየበት፣ ብዙ ማሻሻያዎች ስለተደረጉበት ህግ ሊያወጡ አይችልም፡፡ ምናልባት እንደራሴዎቻችን እና የረቂቅ ህጉ አስረጅዎች እንዲሁም አንዳንድ የፕሬስ ነጻነት “ባለጉዳዮች”ና “ጠበቆች” አሁን የምንነጋገረው ስለ ፕሬስ ህግ እንጂ ስለሌላ የወንጀል ህግ አይደለም የሚል መከራከሪያ ወይም ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ ስለቱርክ የፕሬስ ነጻነት የሚያወራ ማንም ሰው ስለዚህ አገር የወንጀልም መቅጫ ህግ ቁጥር 301 ስለታይላንድ የፕሬስ ነጸነት የሚናገር ሁሉ ስለዚህ አገር የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 112 ሳያነሳ እንደማይቀር፣ ሳያነሳ ቢቀር ግን ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አፉን ሞልቶ ለመናገር የግድ ቱርካዊ ታይላንዳዊ መሆን ወይም እዚያ መኖር አያስፈልግም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |