| ከሕንፃና የመንገድ ግንባታ ጎን ለጎን... |
|
|
| Wednesday, 07 May 2008 | |
ከሕንፃና የመንገድ ግንባታ ጎን ለጎን የፍትሕና የመልካም መስተዳድር ግንባታ ይኑር!አዲስ አበባ እንደገና እየተሰራች ነው፡፡ አሌ የማይባል ግልፅና ገሃድ ሃቅ ነው፡፡ በርካታ ትላልቅ መንገዶችና ድልድዮች እየተገነቡ ነው፡፡ በርካታ አዳዲስ ሕንፃዎች ተሰርተዋል፣ እየተሰሩም ናቸው፡፡ በዚህም አዲስ አበባ ከአፍሪካ ትላልቅ ከተሞች እንዷ ልትሆን ትችላለች፡፡ አዲስ አበባን እንደገና ሠራኋት ብሎ ኢሕአዴግ ቢኮራ አያሳፍረውም፡፡ ከአዲስ አበባ ሌላ ሌሎች በርካታ ከተሞችም እንደገና እየተሰሩ ናቸው፡፡ ባሕርዳር፣ አዋሳ፣ ጅጅጋ፣ መቀሌ የመሳሰሉትና ሌሎችም እንደዚሁ፡፡ አውራ መንገዶች በብዛት እየተሰሩ ናቸው፣ የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እየተገነቡ ነው፣ በርካታ ከተሞች መብራትና ስልክ እያገኙ ነው፡፡ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክና ሆስፒታልም በየከተማውና በየገጠሩ እየተስፋፉ ነው፡፡ ገና ብዙ ቢቀረንም ይህን ሃቅ አስምረንበት ማለፍ አለብን፡፡ የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ግን ከሕንፃና ከመንገድ ግንባታው ጎን ለጎን መጓዝ አልቻለም፡፡ ፍትሕና መልካም አስተዳደር የማንገሥ ጉዳይ ኢሕአዴግ በተደጋጋሚ ሲለውና ቃል ሲገባለት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ትኩረት መልካም አስተዳደር ማስፈን ነው ብሎም ወስኗል፡፡ መርሃ ግብርም አውጥቷል፡፡ በተግባር ግን አልተሳካለትም፡፡ የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ሊታይ አልቻለም፡፡ የሲሚንቶ የብረታ ብረትና የነዳጅ ዋጋ መናርና እጥረትም ምክንያቶች ሆነው የሚቀርቡለት ጉዳይ አይደለም፡፡ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ግንባታ ለምን ከሌላው አካላዊ ግንባታ ጋር ጎን ለጎን ሊሄድ አልቻለም? የብረት ዋጋ ቢጨምር፣ የሲሚንቶ ዋጋ ቢንር፣ የነዳጅ ዋጋ ሰማይ ቢወጣ፣ የመንገድና የሕንፃ ግንባታ ሳይቆም በየጊዜው እየቀጠለ ባለበት የፍትሕና የአስተዳደር ማንገሥ አጀንዳ ግን ለምን አልተሳካም? ያለመሳካቱ ምክንያት ስለሚታወቅ ለመግለፅ አስቸጋሪ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ በአመራር ደረጃ ወጥነት የለም፡፡ ሁሉም የኢሕአዴግ ወይም የመንግሥት የአመራር አካል ፍትሕና መልካም አስተዳደርን ለማንገሥ እኩል ሲቆረቆር፣ ሲጨነቅና ሲረባረብ አይታይም፡፡ ወጥነት የሌለው ነገር ደግሞ ዘላቂነት አይኖረውም፡፡ ሌላው ምክንያት ቢሮክራሲው ተለይቷል፡፡ የአመራሩ አካል አይደለም ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ሕዝብንና መንግሥትን እያጋጨና እያጣላ የሚውል ቢሮክራሲ ወደ መሆን አዘንብሏል፡፡ ቢሮክራሲው እጅግ በሙስና የተዘፈቀ ነው፡፡ የቢሮክራሲው ዓላማ ሕዝቡን ማገልገል ሳይሆን ቦጭቆ፣ ሰርቆና ዘርፎ መሸሽ መሆኑን በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ይህ ችግር እንዳለ ለማሳወቅ ያለው ሂደትም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ለሕዝብ የሚቆረቆር ወገን የሚያውቅበት መንገድ እየጠፋ ነው፡፡ የበላይ አካልም ለማወቅ የሚከተለው መንገድ የተመቻቸ ነው፤ ማለት አይቻልም፡፡ አልፎ አልፎ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከሕዝብ ጋር ለመገናኘት በየቀበሌውና በየክፍለ ከተማው የሚያደርገው ስለላና መገናኘትም በተግባራዊ መፍትሄ ካልታገዘ ሕዝብ ብሶቱን መናገሩ ያቆማል፡፡ መፍትሔ ላይገኝ ምን አስለፈለፈኝ ብሎ ዝምታን ሊመርጥ ይችላል፡፡ መንግሥት ይህን ሁኔታ በአጭር ጊዜ ልዩ ትኩረትና እንቅስቃሴ አድርጎ ሊፈታውና ሊቀይረው ይገባል፡፡ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች በተደረገው የማሟያ ምርጫ ኢሕአዴግ የበላይነቱን አረጋግጧል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ፍትሕን ለማጠናከር አመቺ ሁኔታ ይፈጥርለታል ቢባል የተሳሳተ አይደለም፡፡ አዲሱ የአዲስ አበባ አስተዳደር ስልጣኑን ተረክቦ ሥራውን ሲጀምር ሁለቱንም ጎን ለጎን ለማሳካት ቆርጦ መነሳት ይኖርበታል፡፡ የመንገድና የሕንፃ ግንባታው በተሻለ ፍጥነት፣ በተሻለ ዲዛይን፣ በተሻለ ንጽሕና ከሙስና በፀዳ አሰራር ሊያካሂደው ይገባል፡፡ ከሕንፃ ግንባታ በተጨማሪ አዲስ አበባ በቂ መናፈሻና በቂ መዝናኛ ያሏት ከተማ መሆንዋንና "ኢንቫይሮመንት"ን ግምት ውስጥ ያስገባ አካሄድ እንዲኖራት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት የታየ የአዲስ አበባ እድገት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ግን በተለይ ባለፈው ዓመት ብልሽትና መንሸራተት የታየበት ስለነበር ቆም ብሎ፣ አስቦ ተረጋግቶ መቀየርና ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ እርምጃውም ፈጣንና ቆራጥ መሆን አለበት፡፡ ሕዝቡ በተግባርና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያየው የሚችል ፍትሕና መልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ እንቅስቃሴ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የፍትሕና የመልካም አስተዳደር መዛባት ቀስ በቀስ ሌላውን የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴ ይዞት መውደቁ አይቀርም፡፡ ፍትሕና መልካም አስተዳደር ሲጠናከር የመንገድ፣ የሕንፃና በአጠቃላይ የመሠረተ ልማት ግንባታን ያቀላጥፋል፤ ያጠናክራል፡፡ ስለዚህ፣ ከሕንፃውና ከመንገዱ ግንባታ ጎን ለጎን የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ይካሂድ! |
| Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |