| የኢሳያስን መንግሥት ለማስወገድ |
|
|
| Wednesday, 07 May 2008 | |
በየማነ ናግሽሁለት አዳዲስ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ የ13 ተቃዋሚ ድርጅቶች እናት ድርጅት የሆነው የኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ኪዳን (ኪዳን) ለአንድ ዓመት ያህል ለሁለት ተሰንጥቆ ከቆየ በኋላ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ብዙዎቹ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መሆናቸውን በመግለፅ "ሎሚስ ሓዲአላ" ሲሉ ተስተውለዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የስልጠና ተቋም አዳራሽ፣ የኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ኪዳን ለሳምንት የሚቆየውን የሁለተኛ ጉባኤውን የመክፈቻ ስነ ሥርዓት አካሂደዋል፡፡ የመክፈቻ ንግግሩ በትግርኛ፣ ዓረብኛ፣ እንግሊዝኛና አማርኛ ቀርቧል፡፡ በመክፈቻ ንግግሩ ጥሪ የተደረገላቸው የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችና አብዛኞቹ በመላ ዓለም ያሉ የኤርትራ ሲቪክ ማህበራት እንዲሁም የሰንዓ ፎረም ሴክሬታሪ አባላት ተገኝተዋል፡፡ በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ በተደረገው ስብሰባ ድርጅቱ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት አመቻች ኮሚቴ ተቋቁሞ ቻርተርና ሕገ ደንቡን እንዲያረቅ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በአቶ መንግሥተአብ አስመሮም በኩል ተዘጋጅቶ መቅረቡን አሳውቀዋል፡፡ አመቻች ኮሚቴው በጉባኤው ለውይይት የሚቀርብ ቻርተርን ለማፅደቅ ከሁሉም አባል ድርጅቶች ወኪሎች ባሉበት መርቀቁና ከዚህ በፊት በድርጅቶቹ መካከል ሲፈጠሩ የነበሩ የፖለቲካ የአመለካከት ልዩነቶችና ለሌሎች ጉዳዮች ለማስታረቅ የተሻለና ሁሉንም አሳታፊ በሆነ መልኩ መደረጉን የጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሼክ ሳልሕ ቱርኪ ገልፀዋል፡፡ የስደት መንግሥት የማቋቋም አጀንዳ አለው ተብሎ የሚታመነው ይህ ጉባኤ ባለፈው ዓመት ጉባኤ የተፈጠሩ ስህተቶች በመማርና በፓርቲዎቹ የፖለቲካ ልዩነት ቢኖርም፣ አሁን የተፈጠረው አሳታፊ የፖለቲካ መድረክ የመጀመሪያውና የኤርትራ የተቃውሞ ኃይል አንድ እርምጃ ወደፊት ያራመደ ሊያስብል እንደሚችል ከመድረኩ አዘጋጆች ተገል"ል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያው ጉባኤያቸውን ካካሄዱ በኋላ በመካከላቸው በተፈጠረው ልዩነት በጋራ ከመንቀሳቀስ ተገድበው መቆየታቸውን የተናገሩት አቶ ሳልሕ፣ ጉባኤው እየተካሄደ ያለው አጠቃላይ የአገራቸውን ሁኔታ እጅግ አደገኛና አስጊ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኤርትራን ወደ ሽብርና እስር ቤት የቀየሯት የፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ሥርዓት ሳይወገድ በአገሪቷና በቀጣናው ምንም ዓይነት መረጋጋትና ሰላም ሊፈጠር እንደማይችል ሁሉም አምነውበታል፡፡ በመካሄድ ላይ ያለው ጉባኤ በኢሳይያስ ፀብ ጫሪነት በሁለቱም ሕዝቦች መካከል የተደረገው ጦርነትም ሊያክም የሚችል ትልቅ አጋጣሚ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በተጨባጭ በኤርትራ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ በሁሉም ኤርትራውያን ልብ የተባለ ይመስላል፡፡ "እዚህ የተሰበሰብነው አገር ለመታደግ ነው" ይላል የጉባኤው የመክፈቻ ንግግር፡፡ ከዚህ በፊት ለየት ባለ መልኩ የአገሪቱ ተወላጆችና ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ተገኝተው ለዓላማው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከመካከለኛው ምስራቅ የኤርትራ የአገር አባቶች፣ የሃይማት መሪዎችን የሲቪክ ማህበራት አመራሮች በታዛቢነት ተገኝተው ጉባኤው በግልፅነትና በልበ ሙሉነት እንዲካሄድና ኢላማውን እንዲመታ አሳስበው ሐቀኛ ትዝብታቸውንና አስተያየታቸውን ለኤርትራ ሕዝብ ለማስተላለፍ ቃል ገብተዋል፡፡ በአሜሪካና በካናዳ ከ13 ሲቪክ ማህበራት በአንድ ላይ ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው "የኤርትራ ዓለም አቀፍ አንድነት" ሲቪክ ማህበር ተወካይ አቶ ሰመረ ተስፋ ሚካኤል ለጉባኤው ድጋፋቸውን ሲገልፁ "ይህ በቀላሉ የሚታይ እርምጃ አይደለም፡፡ አዲስ አዎንታዊ ምዕራፍ ይከፍታል" በማለት የጉባኤውን አሳታፊነት አድንቀዋል፡፡ "በኤርትራ ተቃዋሚዎች ታሪክ የተለመደው የመጠራጠርና የእርስ በርስ አለመተማመን ባህል የተሻረበትና የዴሞክራሲ ጭላንጭል የተጀመረበት አጋጣሚ" ብለዋል፡፡ ተወካዩ አንዱን ለመደገፍ ሌላውን ለመንቀፍ አለመምጣታቸውን በመግለፅ፣ በአገራቸው ጭቆናና ግፍ እየተባባሰ በሚመጣበት ወቅት የተቃዋሚ ሃይሎች ጥንካሬ እየደከመ መምጣቱ እንዳሳዘናቸው ሆኖም ራሳቸውም እንደ ዜጋ ተጠያቂ መሆናቸውን አልደበቁም፡፡ ማዶ ለማዶ ተቀምጦ የመወቃቀስ መጋረጃ የተቀደደበትና ቅንና ግልፅ የሆነ መድረክ የሚካሄድበት ሁኔታ በመፈጠሩም ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ አቶ ሰመረ፣ ኪዳንን አስመልክቶ ሁለት መሰረታዊ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡ ኪዳን ሰፊውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍና የሚጠቅም፣ ግልፅ የሆነ አገራዊ ራዕይ ቀርጾ በኤርትራ ያለው አስቸኳይ ችግር ለመቅረፍ እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል፡፡ እሳቸውም በድርጅታቸው ስም ለእናት ድርጅቱ ሙሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ በአውሮፓ አገራት ከሚገኙ 10 የዜና አውታሮችን ሲቪክ ማህበራት እናት ማህበር ወክለው የተገኙ አቶ ተስፋ ዘውደ በበኩላቸው፣ በአገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ ተጋብዘው ሲሳተፉ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ገልጸው፣ ይነስ ይተልቅ ጅማሮው ትልቅ እርምጃ መሆኑን ለጉባኤው አዘጋጆች አድንቀዋል፡፡ "ለመግለፅ የሚቸግረን፣ ስናስበውም የሚሰቀጥጠን የኤርትራ ሕዝብ ሁኔታ ተጠያቂ የሆኑትን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለመጣል በተቃዋሚዎች በኩል የነበረው አካሄድ በቂ አይደለም" በማለት ወቀሳ የሰነዘሩ አቶ ተስፏ፣ "ሎሚስ ሓዲአላ" (ዛሬ ፍፃሜው ይሆናል) ብለዋል፡፡ "የኤርትራን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት ሁለተኛ እድል ያለን አይመስለኝም" በማለት የአጋጣሚውን ወሳኝነት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ መድረኩ የመጨረሻና የኤርትራ ሕዝብ ዕድል የሚወስንበት ነው፡፡ ምናልባትም ብዙዎቹ በጉጉት የሚጠብቁት የስደት መንግሥት (exile government) የሚመሰረትበት አጋጣሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አቶ ተስፋ ወክለዋቸው የተገኙት ድርጅት እምነት ያሉት ሁለት ዓበይት ነጥቦች ጠቅሰዋል፡፡ ኪዳን ሙሉ በሙሉ ኤርትራዊ ድርጅት ነው፡፡ ጉዳዩ በሙሉ የኤርትራ ጉዳይ በመሆኑ ያገባናል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ጉባኤው የኤርትራ ጉዳይ ሆኖ ኤርትራ ውስጥ መካሄድ እያለበት ውጭ አገር መደረጉ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የተቃውሞ ፖለቲካ አስፈላጊነት ተረድተው በተቀበሉበት ወቅት ኤርትራ ለብቻዋው ወደ ሌላ አቅጣጫ እየተጓዘች ትገኛለች፡፡ ሌሎች ወደፊት ሲጓዙ ኤርትራ ወደ ኋላ እየተመለሰች ነች፡፡ አቶ ተስፋ ዘውደ እንደ ተወካዩ ንግግር በጉባኤው የሚኖራቸው ትዝብት ለህዝባቸውና ለአባሎቻቸው "ሚዛናዊና ቅን፣ ሆኖም የማያወላውል ነፃ ግምገማ ለመስጠት" ተዘጋጅተዋል፡፡ ለግምገማቸው መሰረት ይሆናሉ ያሉዋቸውን ከ15 በላይ ዝርዝር መስፈርቶች አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ኪዳን ዴሞክራሲያዊ ባህል ለመፍጠር የሚኖረው ቁርጠኝነት፣ ሕዝብ የስልጣንን ምንጭ መሆኑ ማረጋገጥ፣ የኤርትራ ሕዝብ አገራዊ ጥቅሞች የሚያስከብር መሆኑ፣ በድርጅቱ ውስጥ የስልጣን ጥማት አለመኖሩና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ በጉባኤው ከ200 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን አንዳንድ ተወካዮች ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት ይህንን መድረክ የመጨረሻውና የተሳካ ይሆናል የሚል ሙሉ ተስፋ አላቸው፡፡ አቶ መንግሥተአብ አስመሮም የጉባኤው አመቻች ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ ሂደቱ እስካሁን በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ አረጋግጠውልናል፡፡ በስብሰባው ግብዣ የተደረገላቸው ወገኖች ሁሉ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸው ትልቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የጉባኤው የመክፈቻ ስብሰባ "ተስፋ ሰጪና ጉባኤው የተሳካ ያደርጋል" የሚል ግምት አላቸው፡፡ የቻርተሩ አርቃቂ ቡድን በተቻለ መጠን የሁሉንም ፓርቲዎች ፖለቲካዊ ፍላጎትና አመለካከት ግምት አስገብቶ ልዩነቶችን እያስታረቀ ከአመቻች ኮሚቴ ጋር እየተመካከረ መስራቱን ግልፅ አድርገዋል፡፡ "ባለፈው ጊዜ በኪዳን ውስጥ ያጋጠመ መከፋፈል በሕዝባችን ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ተምረንበታል፡፡ በመሆኑም ለጉባኤው መሳካት ምንም ዓይነት ጥርጥር የለኝም" ብለዋል አቶ መንግሥተአብ፡፡ ከ13 በላይ ሲቪክ ማህበራት አስተባብሮ የሚንቀሳቀሰው "የኤርትራ ዓለም ላኻዊ ሓድነት" (የኤርትራ አለማቀፍ አንድነት) እናት ማህበርን ወክሎ የመጣ አቶ ሰመረ ተስፋ ሚካኤል በበኩሉ ይህ ጉባኤ ባለፈው ጊዜያት ከተደረጉ ጉባኤዎች የሚለይበት ሲያስረዳ፣ "በኤርትራ የተቃውሞ መድረክ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም ሲቪክ ማህበራት እንዲሳተፉ መደረጉ በአገራችን የዴሞክራሲ ባህል ትልቅ የመሰረት ድንጋይ ጥሎ ያልፋል" ብለዋል፡፡ "የኪዳን" አባል የሆኑትና በሽምቅ ውጊያ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የቀይ ባህር ዓፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ያሲን መሐመድ አብደላ ከጉባኤው የሚጠብቁት ውጤት ሲገልፁ "የስርዓቱን ዕድሜ ለማሳጠር የምናካሂደው ትግል የሚያፋጥን ፕሮግራምና ቻርተር አፅድቀን እናወጣለን" በማለት አረጋግጠዋል፡፡ "ሕዝቡ የሚበላው አጥቶ በረሃብ እየማቀቀ፣ ሰላምና ነፃነት ርቆታል፣ የሥርዓቱ መዘዝ ከኤርትራ ወጥቶ ወደ ጎረቤት አገራት እየተሸጋገረ ነው" ያሉት አቶ ያሲን፣ "ኤርትራዊ የሚሸማቀቅበት ሁኔታ ተፈጥሯል" ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ያሲን አባባል፣ እየተባባሰ የመጣው የሥርዓቱ አስከፊነት ፓርቲዎቹ ልዩነታቸውን እንዲያስታርቁ አስገድዷቸዋል፡፡ የቀይ ባህር አፋር በኤርትራ አፋሮች ለራስ በራስ ዕድል የመወሰን እስከ መገንጠል መብት የሚታገል ሲሆን እስካሁን በኤርትራ ወታደሮች በወሰደው የማጥቃት እርምጃ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሶበታል፡፡ አርቲስት (አቀናባሪ) እዮብ ዮሐንስ ይባላል፡፡ ለ17 ዓመት ያህል ነዋሪነቱ በዚህ በአዲስ አበባ ነው፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ንቅናቄ ፓርቲ አባል በመሆኑ የጉባኤው ተሳታፊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የጉባኤውን መንፈስ ጠይቀነው በጣም ደስተኛ እንደሆነና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መጀመሩን አረጋግጦልናል፡፡ "ፓሪቲዎቹ ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው የኤርትራን ሕዝብ እሮሮና ስቃይ ያስቀደሙ ይመስላል" ብሏል፡፡ ዓላማን ለማሳካት በተናጠል መጓዝ ሳይሆን ከሌሎች ተቀናጅቶና ተባብሮ መስራት መሆኑ የአርቲስቱ እምነት ነው፡፡ ለኤርትራ ሕዝብ የዴሞክራሲ ምንጭ ይሆናሉ ብለህ ታምናለህ ወይ ተብሎ ሲመልስ "በተቃዋሚዎቹ አመራር ደረጃ ያሉት የቀድሞ ታጋዮችና ሥርዓቱ ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ ተመልሰው ያ ዓይነቱ ሥርዓት ያመጣሉ ብዬ አልገምትም" ብሏል አርቲስት እዬብ፡፡ የሥርዓቱ አስከፊነት አስመልክቶ "የሕግደፍ (ሻዕቢያ) አካሄድ በጣም ከባድ ነው፡፡ ከኤርትራ ውጭ ያለው ሰውም ለማሰር የሚሞክር ነው፡፡ እርስ በርሱ እንዳይገናኝና እንዳይነጋገር ይቆጣጠራል፡፡ በመሆኑም ኤርትራዊው እንዴት ወደ አገሩ ይሂድ?" ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል ውጭ አገር በመዘዋወር የበርካታ ታዋቂ ዘፈኖች ማቀነባበሩን ገልፆ፣ "ባለመረዳት ሊሆን ይችላል እንጂ የኤርትራ አርቲስቶች ድርሻችን እየተወጣን አይደለም" በማለት የኤርትራን የወቅቱ አርቲስቶች ወቅሷል፡፡ "ከም በዓል የማነ ዝአመስሉ ዓቢይቲ አርቲስቶች". እንደ የማነ ባርያ የመሳሰሉ ታላላቅ አርቲስቶች ቢኖሩ ኑሮ ትልቅ አስተዋፅኦ ባደረጉ ነበር" ብሏል፡፡ አሁን አሁን በተለይ በውጭ የሚገኙ አንዳንድ አርቲስቶች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ እዮብ አርቲስቱ የለውጥ ሃዋርያ ሊሆን ይገባል የሚል እምነት አለው፡፡ በአዲስ አበባ ሲኖር ምንም ዓይነት ችግርና ልዩነት እንዳልገጠመው የሚናገረው አርቲስት እዮብ፣ ስለወደፊቱ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዕድል ሲናገር "ድንበር ምን ጥቅም አለው፣ አሁንም በልብ አንድ ላይ ነው ያለነው፣ ዓለም ራሷ አንድ እየሆነች ነው" ብሏል፡፡ የአሜሪካ ሲቪክ ማህበራት ተወካይ አቶ ሰመረ በበኩላቸው የሲቪክ ማህበራት ትግል አስመልክቶ "በተቃዋሚ ወገን ሆነ በሲቪክ ማህበር የተደራጀ የትግል ስልቶች ለአንድ ዓላማ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ለዴሞክራሲና ለለውጥ እንሰራለን እንጂ ለስልጣን አንንቀሳቀስም" ብለዋል፡፡ "ትልቁ ችግራችን" አሉ አቶ ሰመረ፣ "ትልቁ ችግራችን በአገራችን የምንጠላው መንግሥት አለ፣ ይሁን እንጂ የምናምነው የተቃውሞ ኃይልም አላገኘንም" ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ሰመረ አባባል በውጭ ዓለም የሚኖሩ የኤርትራ ዜጎች ከ7 ዓመት በፊትና አሁን ለሥርዓቱ ድጋፍ የሚሰጥ ቁጥር ሲነፃፀር በአሁኑ ወቅት ተዳክመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሕዝብ ወደ ተቃውሞ መድረክ ጎርፏል ማለት አይቻልም፡፡ ታማኝ የተቃዋሚ ሃይል አላገኘም፡፡ ብዙዎቹ ይህንን ሁኔታ በቅርቡ ይቀየራል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ታግሎ ሊያታግል የሚችል ኃይል ፍለጋ ላይ ያለው ሕዝብ - የኤርትራ ዲያስፖራ፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ኪዳን ጉባኤ አሜሪካን ጨምሮ የሌሎች ኃያላን አገራት ድጋፍ የተቸረ በመሆኑ የስደት መንግሥት አቋቁሞ ኢሳይያስን ሊጥል የሚችል ወታደራዊ ኃይል መፍጠር ይችላል፡፡ የኤርትራ ሕዝብም በሥርዓቱ ከፍተኛ ግፍና ጭቆና እየተፈፀመበት በመሆኑ ከአዲሱ የስደት መንግሥት ሊያብር ይችላል የሚል ግምት ፈጥሯል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |