| የዜግነት ስሜት |
|
|
| Wednesday, 07 May 2008 | |
|
በሰለሞን ጎሹ
ከበርካታ ጥናቶችም ሆነ ከተግባራዊ ልምዳችን አንፃር የኢትዮጵያ ተወላጆች ወደ ውጭ በተለይም ወደ ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ ለማቅናት ሕልም ያላቸውና አጋጣሚን የሚጠቀሙ በርካቶች ናቸው፡፡ ለአንዳንዶች የኑሮ ማሻሻያና የተሻለ ሥራ ፍለጋ ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ግን የዜግነት ስሜታቸው በጣም ቀዝቃዛ በመሆኑና ከሌሎች ጠንካራ የዜግነት ስሜት ካላቸው ቡድኖች ጋር መመሳሰል ስላልቻሉ ሀገር የሚለቁ እንደሆኑ የአንዳንድ ጥናቶች መረጃ ያመለክታል፡፡ በአሜሪካ ኩዊንስ ኮሌጅ የሶስዮሎጂ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አለምሰገድ ሀብቱ ባለፈው ጥቅምት ኢንተር አፍሪካ ባዘጋጀው ኮንፈረንስ “Citizenship, ethnicity and group rights in the Greater Horn of Africa with a case study of Ethiopia “በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው ነበር፡፡ "አንድ አገር በግዛቱ ለሚኖሩት አባላቱ ዜግነት ሲሰጥ የጀብደኝነትና የብሔርተኝነት ስሜት በጋራ እንዲይዙ ለማድረግ ይሞክራል፡፡ በለዘብተኝነት የሚገዛና አምባገነን መንግሥት ዜጎችን ለመቆጣጠርና በባለቤትነት ለመያዝ ሲሞክር ዜጎች ግን ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን በፍቃዳቸው ስር ያውላሉ" የሚሉት ፕሮፌሰር አለምሰገድ ዜግነትን ህጋዊና በተግባር የሚታይ ሲሉ ለሁለት ይከፍሉታል፡፡ ህጋዊ ዜግነት በአንድ የተደራጀ ፖለቲካዊ ኅብረተሰብ ውስጥ አባላቱ ያላቸው በህግ የተሰጠ ድርሻ ሲሆን ድርሻውም ለሁሉም አባላት እኩል ነው፡፡ ይህም በአገሪቱ የበላይ ሕግ በሆነው በሕገመንግሥቱ ጭምር ከለላ ተሰጥቶት በዝርዝር የተቀመጠ ነው፡፡ ድሆች፣ ሴቶች፣ የተጨቆኑ የሃይማኖት ቡድኖች፣ የዘርና የጎሳ ቡድኖች ይህን ህጋዊ ዜግነት ለማግኘት ረጅምና አሰልቺ እንዲሁም እልህ አስጨራሽ የሆነ ፖለቲካዊ ትግል አካሂደዋል፡፡ በህግ አይን ዜጎች እኩል እንደሆኑ ግምት ቢሰጣቸውም እውነታው ግን በሀብት፣ የኑሮ ደረጃና ኃይል በመሳሰሉት ነገሮች አንዳንዶች ከሌሎች እኩል አይደሉም፡፡ በዚህም ህጋዊ ዜግነት ከሀሳብ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ከታሪክ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ክልል፣ መደብና ጾታ ከመሳሰሉት ነገሮች በመነሳት ጥቂቶች በተግባር የሚታይ ዜግነት አላቸው፡፡ በተግባር የሚታይ ዜግነት መደብን፣ ፆታን፣ ዘርን ብሔርን፣ ሃይማኖትንና የትውልድ ቦታን ግምት ውስጥ ሳያስገባ እኩል እድል ይሰጣል፡፡ "በተግባር የሚታይ ዜግነትን ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ የትም አልተቻለም፡፡ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ የህይወት፣ የንብረት፣ የምግብ፣ የጤና ጥበቃ፣ የመጠለያ፣ የአልባሳት፣ የትምህርት፣ የማኅበራዊ ደህንነት ሁኔታ ያልተረጋገጠ በመሆኑ በክልሉ በተግባር የሚታይ ዜግነትን ለማረጋገጥ ብዙ ይቀረናል" ይላሉ ፕሮፌሰር አለምሰገድ፡፡ ዜጎች በአገራቸው በተግባር የሚታይ ተጠቃሚነታቸው ካልተረጋገጠ በስርዓቱ የማመንና የመገዛት ብሎም በግዛቱ የመቆየት ስሜታቸው እየቀነሰ ከከፋም እየጠፋ ይመጣል፡፡ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በየትኛውም ዋጋ ዜጎች የአገር ስሜቱ እንዲጠፋባቸው አይፈቅድም፡፡ በተለይም ፣ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ፣ ነኝ ብሎ የሚያስብን ግለሰብም ሆነ ቡድን በሥርዓቱ ውስጥ የራሱን ሚና እንዲጫወት ማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ጉዳዩ የበለጠ ውስብስብ የሚሆነው ደግሞ ኢትዮጵያ ከግለሰብ መብት ይልቅ ቅድሚያ የምትሰጠው ለቡድን መብቶች መሆኑ ነው፡፡ ቡድኖቹ ራሳቸው የተደራጁት በብሔር በመሆኑ የፉክክር ስሜት አላቸው፡፡ ፉክክሩ የሚደረገው ደግሞ በግለሰብ የብሔሩ አባላት ደረጃ ሳይሆን በልሂቃኑ መሪነት ነው፡፡ በቁጥር ጥቂት የሆኑት ልሂቃን ደግሞ በብሔሩ ስም የራሳቸውን ጥቅም ማሳደዳቸው የታሪካችን አንድ አካል ነው፡፡ ፕሮፌሰር አለምሰገድ "በብሔርም ሆነ በሌላ ሁኔታ የተደራጁ ቡድኖች ትግል በተግባር የሚታይ ዜግነት ለመፍጠር የሚደረገው ትግል አካል ነው፡፡ ስለዚህ ዜግነት፣ ብሔርተኝነትና የቡድን መብት የተያያዙ ናቸው" ይላሉ፡፡ እውቅና ማግኘትና ሕጋዊ ከለላ ማግኘት አያያዥ ምክንያት መሆኑን ቢጠቅሱም ከዚህ አንድነትም በላይ ሰፊና የማይታረቁ ልዩነቶች መኖራቸውን አላብራሩም፡፡ ዜጋው በአገሪቱ እምነት ሲያድርበት ለብሔሩ የተለየ ስሜት የማይኖረው ሲሆን በአግባቡ አልተያዝኩም ብሎ ሲያስብ ግን ከብሔሩ አባላት ጋር የተለየ መቀራረብና ኅብረት ይፈጥራል፡፡ ይህ ደግሞ አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ቅያሜ እንዲያሳድር ያደርገዋል፡፡ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩትን የአንዳንድ ብሔሮች ጭቆናና በደል ለማካካስ የሚደረጉ አዎንታዊ እርምጃዎች በዜጎች መካከል የመበላለጥ ስሜት ማሳደራቸው ደግሞ አይቀርም፡፡ አንዳንድ ምሁራን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት በአንድ ወገን የዜጎችን መሠረታዊ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ እቀበላለሁ ብሎ በሌላ ወገን የቡድን መብቶችን ያለምንም መሸራረፍ እስከ መገንጠል እቀበላለሁ ማለቱ ሥርዓቱን በቅራኔ እንደሞላው ይተቻሉ፡፡ በተለይም ሁለቱ መብቶች በሚጋጩበት ጊዜ ለመፍታት የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ የግጭት አወጋገድ ስርዓት አገሪቱ አለመዘርጋቷን ይጠቅሳሉ፡፡ ሌሎች ምሁራን ግን ኢትዮጵያ ሁለቱ መብቶች ከተጋጩ ለብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች የቡድን መብት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ከህገ-መንግሥቱ ንባብ መረዳት እንችላለን ይላሉ፡፡ ፕሮፌሰር አለምሰገድ ሀብቱ ኢትዮጵያ ዜጎቿን ብቻ ሳይሆን ፣ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች፣ በማለት የብሔር ቡድኖችን እንደምታበላልጥ ይጠቅሳሉ፡፡ "እነዚህን ተወዳዳሪ የይገባኛል ጥያቄዎች በአግባቡ የሚፈታ ተቋም መገንባትና ፖሊሲ መቅረጽ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መፈጠር ወሳኝ ናቸው" በማለትም ያክላሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለገበሬው፣ ለላብአደሩ፣ ለጭቁን ብሔሮች ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሴቶች የቆመ ድርጅት መሆኑን ደጋግሞ ገልጿል፡፡ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የማይካተቱ ግለቦችም ሆኑ ቡድኖች በኢሕአዴግ በበጎ አይን የማይታዩ ሲሆን ፣ለሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚሰራ የፖለቲካ ሥርዓት አልተመሰረተም፣ እንዲሉም አድርጓል፡፡ "ግለሰቦች የአንድ ቡድን አባል በመሆናቸው ይደርስባቸው ከነበረው አድልኦ በመነሳት የቡድን መብት መከበርን ለህጋዊ ከለላነት ይፈልጉት ነበር፡፡ የአፍሪካ አሜሪካውያንና ሴቶች ለቡድን መብት መዳበር አስተዋጽኦዋቸው የበዛ ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር አለምሰገድ ሀብቱ የቡድን መብት ጽንሰ ሀሳብ የቅርብ ጊዜ መሆኑን ሲያብራሩ፡፡ "ለብሔርና ለቡድን መብቶች የሚሰጠው እውቅና በመንግስት ህጋዊ፣ ድርጅታዊና ቢሮክራሲያዊ መዋቅሮች፤ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ሂደቶች እንዲሁም ከመንግሥትና ከባለስልጣናቱ ድርጊቶች በግልጽ የሚታይ ነው" የሚሉት ፕሮፌሰር አለምሰገድ ሀብቱ የብሔርና የቡድን መብትን ተግባራዊ ለማድረግ እርስ በርስ በተፈቃቀደ ሁኔታ እውቅና መሰጣጠት፣ ውይይት ማድረግ፣ መስተነጋገድ፣ የአቻ ለአቻ ምልልስ ማድረግ እንዲሁም ክፍት፣ ተለዋዋጭ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ያሰምሩበታል፡፡ የብሔር ፌደራሊዝም ለምትከለተው አገራችን ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩል መሆናቸውን ህገ-መንግሥቱ ያረጋግጥ እንጂ ብሔሮቹ ተመሳሳይ ስሜት ያላቸው ስለመሆኑ ጥርጣሬ አለ፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ የዜግነት ስሜትም የተዥጎረጎረ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ መንግሥት ሚሌኒየሙን ተከትሎ በተለይ የዜግነት ስሜቱ እየቀዘቀዘ ነው ያለውን ዲያስፖራ በአገር ግንባታው እንዲሳተፍ ለማድረግ ያደረገው አበረታች ተግባር እንዳለ ሆኖ በርካታዎቹ አሁንም እንደ አንድ ዜጋ ሊኖራቸው የሚገባው ስሜት የላቸውም፡፡ የአንድነትንና የኢትዮጵያን ስሜት ለመቀስቀስ የሚጥሩ በርካታ ኢትዮጵያን በውጭ አገር ያሉ ቢሆንም ብዙዎቹ በኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት እንደተያዙ እምነት የላቸውም፡፡ በብዙሃኑ የሚመረጠው መንግሥት የአናሳውን ሰብዓዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበር ይኖርበታል፡፡ ህግ አውጭው፣ ህግ አስፈፃሚውና ሕግ ተርጓሚው አካል እርስ በርስ የተለያዩና አንዱ አንዱን እንዲቆጣጠረው ተደርጎ ነው የተቀረፀው፡፡ አባላቱን የሚመርጠውም የአገሪቷ ዜጋ ነው፡፡ ስለዚህም ዜጎች መንግሥትን በበላይነት ያዙታል፡፡ ይቆጣጠሩታል፡፡ ያርሙታል፡፡ ይህ ከላይ የተገለፀው የዴሞከራሲያዊ መንግሥት መለያ ነው፡፡ በሌላ መልኩ በለዘብተኝነት የሚገዙና አምባገነናዊ ሥርዓት ያላቸው መንግሥታት ዜጎችን ይቆጣጠራሉ፡፡ በቀላል አነጋገር "እኛ ለዜጎቻችን ሁሉንም እናውቃለን"" የሚሉ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው መንግሥታት የማኅበረሰቡን አመለካከት በመቅረጽ የነበራቸው ሚና የጎላ ነው፡፡ ለዜጎችም በአገር ደረጃ ከሚሰጡት መብት በተጨማሪ በአለም አቀፍ ሁኔታ ከለላ ይሰጣሉ፡፡ አንድ ዜጋ በዓለም አቀፍ ሕግ እውቅና ኖሮት መብቱን የሚያስከብረው በአገሪቱ ዜግነቱ በቀጥታ አልያም ራሷ አገሪቷ ወክላው ነው፡፡ ዜጎች ለመረጡት መንግስት መፈፀም ያለባቸው በርካታ ግዴታዎች አለባቸው፡፡ ዋነኛው ግብር ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ የዜጎችን የግል መብት ማክበርና ህገዊ ከለላ መስጠት አለበት፡፡ በዚህ መልኩ ዜጎች ከመንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት ጤናማ፣ በጋራ ኃላፊነት እና ግዴታ ላይ የተመሰረተ ከሆነ የዜግነት ስሜት ይጎለብታል፡፡ ነፃ እና ዘና ያለ አእምሮ ያለው ደስተኛ ዜጋ ደግሞ በአጭር ጊዜ የማይታመን ለውጥ ያመጣል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ የፖለቲካው አካሄድ የዜግነት ስሜት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲፈጥር ሆኖ ስለሚካሄድ ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡ ከበርካታ አመታት ታሪካችን በመነሳት መንግሥት ከዜጎች ጋር የተቀራረበ ግንኙነት አልነበረውም፡፡ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርሕ ሳይሆን የአዛዣና ታዛዥ ቀጥተኛ ግንኙነት ነው የነበራቸው፡፡ ይህን ለመቀየር መንግሥት በሕግ ደረጃ አንድ እርምጃ የተራመደ ሲሆን ዜጎች ሁለተኛውን ተግባራዊ እርምጃ እንዲያመጣ ሲያስጨንቁ አይስተዋሉም፡፡ የዜጎች የራስ መተማመን ስሜት ከፍተኛ ባለመሆኑም የመንግሥት የመለወጥ አዝማሚያ ዘገምተኛ ነው፡፡ በዓለም ላይ ከፍተኛ የራስ መተማመን ስሜት ካላቸው ዜጎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ጀርመኖች ናቸው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደቀቀውን የጀርመን ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ገንብቶ ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛው ጠንካራ ኢኮኖሚ ያደረጉት የራስ መተማመንና ከፍተኛ የዜግነት ስሜታቸውን በመጠቀም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በግለሰቦችም ሆነ በቡድን ደረጃ ጥሩ የማይባሉ ግንኙነቶችን የፈጠረችበት ጊዜ ነበር፡፡ ዜጎች ትላንት ስለተፈጠረው ቅራኔ ዛሬ ላይ ያለመተማመንና የተጠራጣሪነት መንፈስ ካላቸው የዜግነት ስሜታቸው በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ሳይሆን የአለፈውን በመፍራት ላይ ብቻ ይመሰረታል፡፡ ይህ ደግሞ በዜግነት መብቱ በእኩልነት እየተስተናገደ ቢሆንም አድልኦ እየተፈፀመበት እንደሆነ እንዲያስብ ሊያደርገው ይችላል፡፡ በፖለቲካ የተደላደለችና በኢኮኖሚ የዳበረች የጋራ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ይህ ከባድ ሳንካ ይሆናል፡፡ ከላይ እንደ ምሳሌ ያነሳሁት የጀርመንን ጉዳይ ዳግም ብመለስበት ያን የዜግነት ስሜት በማነሳሳት ለውጡን ያፋጠኑት የጀርመን ልሂቃን ናቸው፡፡ ሌላውን ነገር ዘንግተው በሥራ ባህላቸው ጀርመንን ከውድቀት እንዲታደጓት ምሁራኑ በግልጽ ቋንቋ ለዜጎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ምሁራን ያበረከቷቸው ሥራዎች የዜግነትን ስሜት ከማነሳሳት ይልቅ የሚያደበዝዙት ይበዛሉ፡፡ በተለይም ከጎሳ ና ከብሔር ፖለቲካው አንፃር ወይም ለፖለተካው ጥቅማቸው አልያም ለቡድናቸው ካላቸው ልዩ የተቆርቋሪነት ስሜት በመነሳት ርዕሰ ጉዳያቸው አንዱን ቡድን ወይም ግለሰብ በመተቸትና በመንቀፍ ሌላውን ደግሞ በመደገፍ ያተኩራል፡፡ በአንፃራዊነት ሊበራል የሚባሉት ምሁራን ለመናገር ያላቸው ፍላጎት የተገደበ ሲሆን ፈቃደኛ ሲሆኑም ለሚዲያው ብርቅ ስለሚሆኑ ሁሉም ተቀባብሏቸው እስከመሰልቸት ይደርሳሉ፡፡ የፖለቲካ አቋም ያላቸውና በግልጽ ሃሳባቸውን ለገበያ የሚያቀርቡት ምሁራንም የተለመደ ሃሳባቸውን በጋዜጣ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በመጽሔት ቀዳሚ ዜና እየሆኑ አመታት የዘለቁ ሲሆን ለአመለካከታቸው አዲስ አቅጣጫና እይታ ወይም ሃሳብ ያለው አዲስ ምሁር ለማየት እንጓጓለን እንጂ ብዙም አልተሳካም፡፡ የሚናገሩትም ቢሆኑ ከጥቂቆቹ በስተቀር ችግሮቻችንን ነቅዘው በማውጣት የተሻለ የወደፊት አቅጣጫ የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ በቋንቋ፣ ባህል፣ የስነ-ልቦና አንድነት፣ በታሪክና በተመሳሳይ ግዛት የተቀራረቡትንና የተዛመዱትን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ወደ ጋራ ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ ይሸጋገር ዘንድ የዜግነት ሰስሜት መዳበሩ አስፈላጊ በመሆኑ ላይ ብዙዎች ቢስማሙም በተግባር ያለው አካሄድ ግን ወደዚያ የሚያመራ አይደለም፡፡ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ የመገንጠል መብት የተሰጣቸው ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች በዜግነት ስሜታቸው ላይ የእርግጠኝነት ነገር ካልተሰማቸው የፌደራል መንግሥቱ አካል መሆናቸውን ወደ ፍፃሜው ለመውሰድ የመገንጠል ጥያቄ ማቅረባቸው አይቀርም፡፡ መገንጠሉን ከልምድ እንደታየው ሲከለክሉ ደግሞ ይበልጥ የዜግነት ስሜታቸው ይሞታል፡፡ የመንግሥቱ ሉአላዊ ባለቤቶች የሆኑት ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች አባላት በስልጣን ክፍፍሉ፣ በሀብት ክፍፍሉ፣ በተቋሞች አደረጃጀትና በመሳሰለው ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሲሆን በተጽዕኖ መፍጠር፣ በህዝብ ቁጥርና በመሠረተ ልማት የተሻለ ደረጃ ያላቸው የበላይ ለመሆን ፍላጎትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደርጉ ይሆናል፡፡ ዙሮ ዙሮ በቡድኑ መብት ተጠቃሚ የሚሆኑት ግለሰቦች በመሆናቸው አሉታዊውም ሆነ አዎንታዊው ውጤት በዜግነት ስሜታቸው ላይ ይፈጠራል፡፡ የዜግነት ስሜት በጥሩ ደረጃ ላይ መገኘቱ ንቃተ ሕሊናው የዳበረ መብቱን የሚያስከብርና ግዴታውን የሚፈጽም ማኅበረሰብ በመፍጠር ዴሞክራሲያዊና በኢኮኖሚ የበለፀገ ሀገር ለመመስረት ለሚያልም እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ባለ ድርሻ የሆኑ ሁሉ ሊረባረቡበት ይገባል፡፡ ያኔ በመግቢያችን ላይ የገለጽናቸው ለመውጣት የሚያቆበቁቡ ኢትዮጵያዊያን ለመግባት ሰልፍ ይይዛሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |