Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የሚጥል በሽታን በምግብ መከላከል ይቻላል
የሚጥል በሽታን በምግብ መከላከል ይቻላል Print E-mail
Wednesday, 07 May 2008
ሕፃናት ላይ የሚከሰትን የሚጥል በሽታ የተለየና ከፍተኛ የቅባትነት ይዘት ያለው ምግብ በመመገብ መቀነስ እንደሚቻል የእንግሊዝ ተመራማሪዎች አስታወቁ፡፡

የሚጥል በሽታ ያለባቸው ህጻናት አዲስ በተጀመረው የምግብ ህክምና መሰረት የቅባትነት ይዘቱ ከፍያለ፣ የካርቦሃይድሬት ይዘቱ ዝቅ ያለና የተመጠነ ፕሮቲን ያለው ምግብ እንዲወስዱ ማድረግ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ቅባትነት የበዛበት ምግብ የሚጥል በሽታን እንዴት መከላከል እንደሚችል በግልፅ መናገር አይቻልም፡፡ ይሁንና ሰውነታችን ውስጥ ከገባ በኋላ ከስብ የሚፈጠረው ከቴን የተሰኘ ንጥረ ነገር የሚጥል በሽታን ሊከላከልና ድንገተኛ ራስ መሳትን ሊቀንስ እንደሚችል ግምታቸውን ገልፀዋል፡፡

ከሁለት እስከ 16 የእድሜ ክልል ለሚገኙ፤ ለሚጥል በሽታ የሚሰጥ መድሃኒት ያልሰራላቸው 145 ያህል ህፃናት በጥናቱ ተካተዋል፡፡ በመድሃኒቱ የጤና ለውጥ ማምጣት ያልቻሉ አነኚሁ ህጻናት ግማሾቹ ወዲያውኑ የምግብ ህክምናው እንዲጀመርላቸው የተደረገ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ለሦስት ወር ያለ ምግብ ህክምናው እንቆዩ፣ ተደርጓል፡፡

በሙከራው የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው የምግብ ህክምናውን የጀመሩ ህፃናት በድንገት ራስ መሳታቸውን በሁለት ሦስተኛ የቀነሰላቸው ሲሆን ያልተጀመረላቸው ምንም የጤና መሻሻል አላሳዩም፡፡ የምግብ ህክምናው ከተጀመረላቸው በተለይ አምስቱ ደግሞ በድንገት የሚወድቁት 90 በመቶ እንደተዋቸው የጥናቱ ሪፖርት ያሳያል፡፡

ለሚጥል በሽታ ከ1920ዎቹ ጀምሮ ከሚሰጠው የመድሃኒት ህክምና ይልቅ አዲሱ የምግብ ህክምና በተሻለ ለውጥ እንደሚያመጣ የተነገረለት ቢሆንም የጎን ጉዳትቶች እንዳሉት የቢቢሲ ዘገባ ይገልፃል፡፡ በምግብ ህክምናው መሰረት በተለየና በተመጠነ መልኩ ከፍ ያለ የቅባትነት ይዘት ያለው፣ ዝቅተኛ የካርቦሃይድሬት ይዘትና መጠነኛ ፕሮቲን ያለው ምግብ እንዲወስዱ የተደረጉ ህጻናት እንደ ድርቀት፣ ማስመለስ፣ የሃይል ማጣትና ርሃብ እንደሚሰማቸው በጥናቱ ወቅት ተረጋግጧል፡፡

የጥናቱ መሪና ለንደን ውስጥ በሚገኝ ግሬት ኦርማንድ ስትሪት ሆስፒታል ውስጥ የኒውሮሎጂ አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሄለን ክሮስ “በአንድ የህክምና ደረጃ በቀላሉ በቁጥጥር ስር የሚውል የሚጥል በሽታ ያለባቸው ህጻናት የምግብ ህክምናውን እንዲወስዱ አልመክርም፡፡ ይሁንና በሁለት አይነት የመድሃኒት ህክምና ለውጥ ላልመጣላቸው ህጻናት ህክምናው ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ሕክምና በሽታዎችን ለመከላከል አንዱ አማራጭ እንደሆነ ቢታመንበትም ይሄንን ለማድረግ የምግብ አይነቶችን በትክክል መመጠን የሚችሉ የስነ ምግብ ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ ባለሙያዋ ጨምረው ገልፀዋል፡፡


የህፃናት ሙቀት መስጫ ማሽኖች ስጋት ፈጥረዋል

ከሕፃናት ሙቀት መስጫ ማሽኖች (ኢንኪውቤተር) የሚወጣው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ማዕቀፍ (ኤሌክትሮማግኔቲክ ፊልድ) አዲስ በሚወለዱ ህፃናት የልብ ምት ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ሳይንቲስቶች ገልፀዋል፡፡

በሕፃናት ላይ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ማሽኖቹ ሥራ ላይ ሲውሉ  የህጻናቱ የልብ ምት ይቀንሳል፡፡ ይሁንና የጣሊያን አጥኝዎች እንደሚሉት እስካሁን ድረስ በማሽኖች ምክንያት የተከሰተ ከባድ የሚባል የጤና ጉዳት አልደረሰም፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩና ከመወለጃ እድሜያቸው ቀድመው የሚወለዱ ህጻናት ጤነኛ እንዲሆኑ በሙቀት መስጫ ማሽኖች ለወራት ያህል መቆየት ያስፈልጋቸዋል፡፡

የማሽኑ ዋና አላማ ለህፃኑ ሙቀት መስጠት ነው፡፡ ይሁንና ሞተሩ ስራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ህጻኑ የተኛበት ቦታ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ማዕቀፍ (ኤሌክትሮማግኔቲክ ፊልድ) ይሞላል፡፡ ይህ የኤሌክትሪክ ማዕቀፍ በልጁ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳውና እንደሌለው በሲየና ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናትም በልጁ የልብ ምት ላይ ልዩነትን እንደሚፈጥር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የልብ ምት መጠን መቀነስ የልብ ሕመም ላለባቸው አዋቂዎች ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የጤና ባለሙያዎች የልብ ምት መጠኑ መቀነሱን ተጠቅመው በሽተኛው ለወደፊቱ አደጋ እንደማያጋጥመውና እንደሚያጋጥመው ቀድመው ለመተንበይ ያግዛቸዋል፡፡ ይህ እውነት ህፃናትም ላይ እውነት ይሁን፣ አይሁን ምንም መረጃ የለም፡፡

ጥናቱን ያካሄዱ ሳይንቲስቶች ማሽኑ ህጻናት ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል በትክክል ለማወቅ ቀጣይ ጥናት የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው ማሽኑን የሚያመርቱ አካላት ግን ህፃናቱ ከማሽኑ የሚከለሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሌላ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በኩባ የመጀመሪያው ሕጋዊ የቤት ውስጥ ኮምፒውተር ገበያ ላይ ዋለ

በኩባ የመጀመሪያው ሕጋዊ የቤት ውስጥ ኮምፒውተር ገበያ ላይ ዋለ፡፡ ይሁንና በአንዳንድ ተቋማት በኢንተርኔት ላይ የተጣለው እገዳ እስካሁን እንዳልተነሳ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የፊደል ካስትሮ ወንድም ራውል ካስትሮ ከተተኩ በኋላ በሃገሪቱ ከነበሩ ጥብቅ እገዳዎች መካከል ይህ ውሳኔ ትንሽ ነፃነት የታየበት እንደሆነ ታውቋል፡ ኮምፒውተሮች በሃቫና ከተማ ካርሎስ ሶስተኛ በተባለ ሱቅ ውስጥ እንዲሸጡ የተፈቀደ ሲሆን የሃገሪቱ ሕዝቦችም አብዛኞቹ ኮምፒውተሮችን ለማየት ቦታውን ሲጎበኙ እንደነበረ ዘገባው አክሎ ገል..ል፡፡

በሃገሪቷ አማካይ የዜጎች ደሞዝ በወር ከ20 ዶላር ያነሰ ሲሆን የአንድ ዴስክቶፕ ኮምፒውተር ዋጋ 800 ዶላር እንደሆነም ታውቋል፡፡ ይሁንና የተወሰኑ ኩባውያን ተጨማሪ ገቢ አላቸው፡፡ ከመካከላቸው አብዛኞቹም ከኩባ ውጭ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ገንዘብ እየተላከላቸው የሚኖሩ ናቸው፡፡

ራውል ካስትሮ የፕሬዚዳንትነት ቦታውን ከያዙበት ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ በቀድሞው ጊዜ በሃገሪቱ ገበያ ላይ እንዳይውሉ ተከልክለው የነበሩ ሸቀጣ ሸቀጦችን እንዲገዙ ፈቅደዋል፡፡ በመሆኑም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ኩባውያን የሞባይል ስልክና ዲቪዲ ማጫዎቻ ገዝተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ኮምፒውተር የመግዛት ፈቃድ አግኝተዋል፡፡ ይሁንና በተወሰኑ የሥራ ቦታዎች፣ በትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ኢንተርኔት መጠቀም እንደተከለከለ ነው፡፡

የኩባ መንግሥት እንደሚለው ኩባ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር የባህር ውስጥ የፋይበር ኦፕቲክ ኬብል በመዘርጋት ኢንተርኔት እንዲኖር ማድረግ የማይቻል ነው፡፡ ይህም የሆነው አሜሪካ በኩባ ላይ በጣለችው የንግድ ማዕቀብ የተነሳ እንደሆነ መንግሥት ያብራራል፡፡ የኦን ላይን ኮኔክሽን በአሁኑ ወቅት የተወሰነ ባንድዊድዝ ባለው ሳተላይት የሚካሄድ ሲሆን ዋጋውም እጅግ ውድ ነው፡፡

የኩባ ወዳጅ የሆኑት የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ሁጎ ቻቬዝ በካሪቢያን ውቅያኖስ በኩል አዲስ ኬብል እየዘረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡ የኬብል ዝርጋታው እንዳለቀም ለኩባ የአለም አቀፉን ድረ ገፅ (ወርልድ ዋይድ ዌብ) ያለ ምንም እገዳ ማዳረስ ይቻላል ተብሏል፡፡

ለወደፊቱ የኒውክሊየር ዋጋ ይንራል

የኒውክሊየር ሃይልን በመጠቀም የከርሰ ምድር ነዳጅን ለመተካትና አየር ላይ የሚለቀቀውን የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠንን መቀነስ ይቻላል የሚለው ሃሳብ በአውስትራሊያ የዘርፉ ባለሙያዎች ባወጡት አዲስ ሪፖርት ችግር ገጥሞታል፡፡

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው የኒውክሊየር ሃይልን ለማመንጨት የሚያገለግለውን ዩራኒየም የተሰኘ ማዕድን ለማውጣት የሚወጣው ወጭ ከፍተኛ ነው፡፡ ከፍተኛ ጥራት ያለው የዩራኒየም ማዕድን በማውጣት ወደ ሃይል ሰጭነት ቀይሮ መጠቀም ወደ አየር የሚለቀቀውን የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ለመቀነስ የተሻለ ቢሆንም ማዕድኑን ለማውጣት የሚፈጀው ወጭ ግን ነዳጅ ከማውጣት የበለጠ ነው፡፡ በመሆኑም ለወደፊቱ የኒውክሊየር ዋጋ እየጨመረ መሄዱ ጥርጥር እንደሌለው “ኢንቫይሮመንታል ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ” የተሰኘ ጆርናል ላይ የወጣው የአውስትራሊያ ባለሙያዎች ሪፖርት ይጠቁማል፡፡

“የአየር ሁኔታ ለውጥን ለመቀነስ ሲባል እንደ አዲስ አማራጭ እየታየ ያለው የኒውክሊየር ሃይልን መጠቀም ዩራኒየምን ለማውጣት ሲባል ተጨማሪ ሃይል የሚጠይቅ ነው” ያሉት በአውስትራሊያ ምናሽ ዩኒቨርሲቲ የጥናቱ መሪ ጋቪን መድ አዲስ የዩራኒየም ክምችት ያለባቸው ቦታዎች መፈለግ የሚቻል ቢሆንም የዩራኒየም ክምችቶች በአብዛኛው በከርሰ ምድር ጥልቀት ውስጥ ስለሚሆኑ ለማውጣት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በኒውክሊየር ኢነርጂ ኤጀንሲ የሳይንስና ዲቨሎፕመንት ምክትል ዳይሬክተር ቴየር ዱጃርዲን የጥናቱን ቅድመ መደምደሚያ አይቀበሉትም፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የኒውክሊየር ሃይልን ለማመንጨት የሚወጣው ወጭ ምንም ያህል ይሁን ወደ አየር በሚለቀቀው የተቃጠለ አየር አናሳነት ከከርሰ ምድር ነዳጅ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡

ቲየር አክለውም ለወደፊቱ ቴክኖሎጂው በተሻሻለ ቁጥር አዳዲስ የዩራኒየም ክምችት እንደሚገኝና አነስተኛ ጥራት ያላቸው የዩራኒየም ንጥረ ነገሮችንም መጠቀም እንደሚቻል በሙሉ የራስ መተማመን ስሜት ገልፀዋል፡፡  
 
< Prev   Next >