Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow ወጣቱ ዲን
ወጣቱ ዲን Print E-mail
Wednesday, 07 May 2008
Imageበምሕረት አስቻለው

ምስጋናው ሙሉጌታ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት ዲን ነው፡፡ የሕግ ትምህርቱን በ1999 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ አጠናቋል፡፡ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መሥራት ከጀመረ ስምንት ወር ሆኖታል፡፡ የዛሬ ስምንት ወር በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሲቀጠር አብዛኞቹ መምህራን ልክ እንደሱ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው መምህራን ለመሆን የተመደቡ ነበሩ፡፡ ስለነበሩና ዩኒቨርሲቲውም አዲስ ስለነበር በቢዝነስ ፋኩልቲ ሥር ለተቋቋመው ሕግ ዲፓርትመንት አስተባባሪ ሆኖ መመረጡን ነግሮናል፡፡
“ዩኒቨርሲቲው የሕግ ት/ቤት አልነበረውም፡፡ በዲፓርትመንት ደረጃ ሲቋቋም መምህራኑን እንዳስተባብር ተመረጥኩ፡፡ የተመረጥኩት ከሌሎቹ መምህራን የተለየ ብቃት ኖሮኝ ሳይሆን ትምህርቴን ባጠናቀቅኩበት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተለያዩ ክበባት እሳተፍ ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሕግ ፋኩልቲ አካዳሚክ ኮሚሽን ለአንድ ዓመት የተማሪዎች ተወካይም ነበርኩ፡፡  ይህ በሕግ ት/ቤት ውስጥ ስላለው አሰራር በተወሰነ መልኩ ግንዛቤ እንዲኖረኝ አድርጓል፡፡ አስተባባሪ ሆኜ የተመረጥኩት ብዙዎቻችን እርስ በርስ ስለማንተዋወቅ፣ ሥራውን አውቀዋለሁ የሚል ከመካከላችን ባለመኖሩና እኔም በጎ ፍቃደኛ ሆኜ በመገኘቴ ነው” ብሏል፡፡

ወጣት ምስጋናው እንዳለው በተማሪዎች ሕብረት፣ በፀረ ኤች.አይ.ቪና፣ በፆታ ክበባት እንዲሁም በሌሎች እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ መሆኑ በፋኩልቲው ውስጥ ስላለው አስተዳደራዊ አሰራር እንዲያውቅ ረድቶታል፡፡ በተማሪዎች ሕብረት በሌሎች ክለባትም ሆነ በሕግ ፋኩልቲ የአካዳሚክ ኮሚሽን ውስጥ የተማሪዎች ተወካይ መሆን የአንድ ፋኩልቲ ዲን ለመሆን በቂ ልምድ ነው ማለት አይቻልም፡፡

የአገራችን የትምህርት ፖሊሲ በመጀመሪያ ዲግሪ ቀጥታ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር መሆንን እንደማይፈቅድ የሚናገረው ወጣት ምስጋናው አገሪቷ በርካታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስለሚያስፈልጓት፣ ከዚህ አንፃር የጀማሪ መምህራን በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች መመደብ የግድ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ልምድ ባላቸው ወይም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በያዙ መምህራን ሊሰጡ የሚገባቸው የትምህርት ዓይነቶች መኖራቸውን በመጥቀስ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ላይ አካዳሚክ ኮሚሽኑ እንደሚወስን አመልክቷል፡፡

ያለምንም የማስተማር ልምድ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማስተማር የራሱ የሆኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያሉት ከመሆኑ ባሻገር እንደ ወላይታ ሶዶ ባለ አዲስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፋኩልቲ ዲን መሆን አስቸጋሪ አይሆንም? ስንል ጠየቅነው፡፡ “እንደ አዲስ አበባ ወይም ጅማ ዩኒቨርሲቲ ባሉት መምህር ወይም የፋኩልቲ ዲን መሆን ቀደም ሲል በተዘረጋና በተጠናከረ አሠራር ውስጥ ገብቶ መስራት በመሆኑ በተወሰነ መልኩ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ፋኩልቲዎች ነፃ አይደሉም፡፡ በዚህ ምክንያት በፋኩልቲዎች የበጀት ችግርም ይኖራል፡፡ ከልምድ አለመኖር ሥራዎች ከልክ በላይ ቢሮክራቲክ ይሆናሉ፡፡ መመሪያዎች በሌሉበት መንቀሳቀስ የግድ ይሆናል፡፡ በአዳደስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንድ መምህር ከማስተማር ባሻገር የተለያዩ አስተዳደራዊ ሥራዎችን የማከናወን ሀላፊነት አለበት” በማለት መልሶልናል፡፡

ምስጋናው እንዳለው፣ እሱም ሆነ ሌሎች ወጣት መምህራን ከማስተማር ውጭ የተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ያስፈፅማሉ፣ ማስታወቂያ ከመለጠፍ ጀምሮ እንደ ተላላኪ ከቢሮ ቢሮ በመዘዋወር ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ “በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ፋኩልቲ ራሴን እንደ ዲን፣ መምህርና ተላላኪ አግኝቸዋለሁ” ብሏል፡፡

በሕግ ፋኩልቲ ውስጥ ያሉት መምህራን ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ወጣቶች በመሆናቸው ከተማሪዎች ጋር ባላቸው የተማሪ አስተማሪ ግንኙነት ላይ የእድሜ መቀራረብ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድር አለባበሳቸውን ከተማሪ የተለየ ለማድረግና ከተማሪዎች ጋር የሚያደርጉትን ንግግርም ገደብ እንዲኖረው አድርገው እንደነበር አልደበቀም፡፡ በዚህ ጥሩ የመማር ማስተማር ሒደት እንደፈጠሩ የሚናገረው ወጣት ምስጋናው መምህራኑን መቆጣጠር ግን ክብዶት እንደነበር አስታውሷል፡፡ ይህንንም ችግር መምህራኑን በማሰባሰብ የጋራ የሆነ መመሪያ እንዲወጣ በማድረግ ለመፍታት ችሏል፡፡

ጀማሪ መምህራን በሚበዙበት ፋኩልቲ ልምድ ያላቸው መምህራን ባለመኖራቸው ምርምሮች ላይደረጉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ልምድ በራሱ ትልቅ ነገር ቢሆንም የወጣትነት ሀይልም ዋጋ ሊሰጠው ይገባል ብሎ ያምናል፡፡ እሱና ሌሎች መምህራን ጓደኞቹ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ዲፓርትመንትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ፋኩልቲ ከማሸጋገር ጀምሮ በፋኩልቲው የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን እስከማሟላት ያከናወኗቸው ሥራዎች ምናልባትም ረዥም የማስተማር ልምድ ባላቸው ዶክተሮች የተሰሩ ቢሆን ትልቅ ትኩረት ይሰጣቸው እንደነበር ጠቁሟል፡፡

“የማስተማር ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ዲን መሆንን ግን አስቤ አላውቅም፡፡ አንድ ነገር ከጀመርኩ ማድረግ የምችለውን ሁሉ ማድረግ አለብኝ ብዬ ስለማምን ዲን ከሆንኩ በኋላ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በነበርኩበት ወቅት ካገኘሁት ልምድና እዚህም ቀደም ካሉ መምህራን በመመልከት ለመስራት ችያለሁ”
 
< Prev   Next >