| የኢትዮጵያ ቡና አድናቆት አገኘ |
|
|
| Wednesday, 07 May 2008 | |
|
በጋዜጣው ሪፖርተር
የኢትዮጵያ ቡና በ1ዐ ሺህ በሚቆጠሩ የቡና አፍቃሪዎች፣ በቡና ኢንዱስትሪ በተሰማሩ ባለሙያዎች አድናቆት ማግኘቱና ከ7ዐ በላይ ከሆኑ ኩባንያዎች ጋር ለመስማማትም አመቺ እድል መፈጠሩ ተጠቆመ፡፡ ሲኤስ ዋየር የተባለው የዜና ምንጭ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ይህንን እድል ያገኘችው ከአራት ቀናት በፊት አሜሪካ ሚኒፓሊስ ውስጥ በተዘጋጀው ዓመታዊ የቡና ጉባዔ ላይ ነው፡፡ እንደዘገባው ከሆነ በዚህ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ከመላው ዓለም የመጡ በ1ዐ ሺህ የሚቆጠሩ የቡና አፍቃሪዎች የቡና ባለሙያዎች የቡና ኢንዱስትሪ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን የኢትዮጵያን ቡና ተደናቂ እንዲሆን ያደረገውም ወደ ጉባዔው አዳራሽ ሲገባ እንግዶች አቀባበል የተደረገላቸው በኢትዮጵያ ባህላዊ ቡና አፈላል ስርዓት መሠረት በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር እንደመሆንዋ መጠን ከሌሎች አገሮች ቡና አምራች አገሮች በተለየ መልኩ እድል እንድታገኝ በተደረገበት በዚህ ጉባዔ ኢትዮጵያ የዘንድሮው ጉባዔና ኘሮግራም ልዩ አገር እንድትሆንና "Portrait Country" የሚል ስያሜ እንዲሰጣት ተደርጓል፡፡ በዚህ ኘሮግራራም ላይ ከኢትዮጵያ ባህላዊ የቡና አፈላል ሥርዓት ጐን ለጐን ለእንግዶቹ የተደረገውን መስተንግዶ ኢትዮጵያውያን እንዲያከናውኑም ተደርጓል፡፡ በዚህ ልዩ ኘሮግራም ላይ የኢትዮጵያ የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ያቆብ ያላ መገኘታቸውን የገለፀው ይኸው ዘገባ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ያገኘችው ልዩ እድል ትልቅ ኩራት የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከ15 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ህይወቱ የተመሰረተው በቡና ላይ መሆኑን የጠቆመው ዘገባ ጉባዔው የኢትዮጵያን ቡና ከማስተዋወቁም በላይ ተሳታፊ ከሆኑና ከ29 አገሮች የተውጣጡ ከ7ዐ በላይ ከሚሆኑ ትላልቅ የቡና ኢንዱስትሪ ተወካዮች ጋር በጋራ ለመስራትና አዳዲስ ገበያዎችን ለማግኘት አመቺ እድል እንደተፈጠረላትም ጠቁሟል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |