Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የምግብና የፍጆታ እቃዎች ዋጋ...
የምግብና የፍጆታ እቃዎች ዋጋ... Print E-mail
Wednesday, 07 May 2008
የምግብና የፍጆታ እቃዎች ዋጋ አሁንም እየጨመረ ነው
በአንድ ወር ከ15 በመቶ በላይ ጭማሪ ታይቷል


በዳዊት ታዬ

የምግብና የፍጆታ እቃዎች ዋጋ አሁንም በፍጥነት እየጨመረ ሲሆን በተለይ የምግብ እህሎች ዋጋ በአንድ ወር ልዩነት ውስጥ ብቻ ከ15 በመቶ በላይ የዋጋ ለውጥ እንደታየባቸውና ለአንዳንድ የምግብ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ደግሞ የአቅርቦት እጥረት እያጋጠማቸው መሆኑ ታወቋል፡፡

ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ ያደረግነው የገበያ ቅኝት እንደሚያስረዳው አብዛኛዎቹ ምግብ ነክ የሆኑ የፋብሪካና የሠብል ምርቶች ዋጋቸው በየእለቱ እየጨመረ ሲሆን ዱቄትና ሩዝ የአቅርቦት እጥረት ከታየባቸው ምርቶች ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የገበያ ቅኝት ካደረግንባቸው ገበያዎች መካከል በአቃቂና በሳሪስ ገበያ አንድ ኩንታል አንደኛ ደረጃ ጤፍ 8ዐዐ ብር ደርሷል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ የሚባለው ደግሞ 7ዐዐ ድረስ በመሸጥ ላይ ነው፡፡

የዋጋው ለውጥ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በየእለቱ እየጨመረ መጥቶ በአንድ ሳምንት ልዩነት ውስጥ ብቻ ከ50 ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በነዚህ ገበያዎች ያነጋገርናቸው የጤፍ ነጋዴዎች እንደገለፁልን ከሦስት ሳምንት በፊት አንደኛ ደረጃ የሚባለው ጤፍ ከ7ዐዐ እስከ 730 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን በዚህ የጊዜ ልዩነት ውስጥ ይህን ያህል ጭማሪ ሲያሳይና አንድ ኩንታል ጤፍ በ8ዐዐ ብር ሲሸጡ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው፡፡

"እኛ ራሳችን እየከበደን ነው" ያሉትና በአቃቂ ገበያ የጤፍ ነጋዴ የሆኑት አቶ ነጋሽ ሙሉ ገበያተኛው የጤፍ ዋጋ ይህን ያህል መድረስ ሊያምን ያልቻለበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡

የሚሸጡበት መደብር ባዶ እንዳይሆን እንጂ ከጤፍ ሽያጭ እያገኙ ያሉት ትርፍ እጅግ ትንሽ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከሚመጣበት ቦታ ዋጋው እስከ 750 ብር ደርሷል፡፡ ትራንስፖርትና የሠራተኛ ሲታከልበት የሚገኘው ትርፍ ትንሽ ነው፡፡ ደንበኞቻችን ግን በዚህ ዋጋ መሸጣችን ብዙ ትርፍ የሚገኝበት እንደሆነ ያስባሉ፡፡ እንዴት እያመጣን እንዳለ የሚያውቅልን የለም" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እንደ ጤፍ ሁሉ የሌሎች የሰብል ምርቶችም ተመሳሳይ በሆነ ፍጥነት ጨምረዋል፡፡ በሁለቱ ገበያዎች አንድ ኩንታል ስንዴ 650 ብር ደርሷል፡፡ በቆሎ 400 ብር እየተሸጠ ሲሆን ዱቄት ደግሞ 8 እና 8 ብር ከሃምሳ ሣንቲም ይሸጣል፡፡ በሾላ ገበያ ዱቄት የሚሸጡ መደብሮች በአብዛኛው እየሸጡበት ያለው ዋጋ 8 ብር መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡ የዱቄት ዋጋ ተወደደ በተባለበት ባለፈው ሳምት በኪሎ 7 ብር ነበር፡፡

በቃሊቲ የሚገኝ አንድ የዱቄት ማከፋፈያ ባለቤት እንደገለፁት የዱቄት ገበያ እየተለወጠ መምጣቱንና በየእለቱ ዋጋ እየጨመረባቸው በመሆኑ እነሱም የዋጋ ለውጥ ለማድረግ ተገደዋል፡፡

ደንበኞቻቸው የዱቄት ዋጋ የተወደደ ቢሆንም እየዟቸው ነው፡፡ ካፈለው ሳምንት ጀምሮ ግን ተወደደ በተባለበት ዋጋ እንኳን ማግኘት ባለመቻላቸው ያላቸውን ክምችት (ስቶክ) እየጨረሱ መሆኑን አስረድተው የአቅርቦቱ ማነስ እንዳሳሰባቸውም ጠቁመዋል፡፡

"ዱቄት ከምናመጣባቸው አምራቾች ይሰጠን የነበረው ዱቄት በኮታ እንዲደርሰን እያደረጉ በመሆኑ እጥረቱ ተፈጥሯል፡፡ ስለዋጋውም ስናነጋግራቸው ስንዴ ስለሌለ መፍጨት አልቻልንም፤ እንደ ቀድሞው ቢሆን ለተወሰነ ቀን መጠባበቂያ የሚሆነን እንይዝ ነበር፤ አሁን ግን ይህም የለም" ብለዋል፡፡

አቃቂ ገበያ አካባቢ በዚሁ የዱቄት ማከፋፈል ላይ የተሰማሩ ባለመደብር ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ መደብሩን መዝጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ የከፈቱትም የተወሰነ ምርት በማግኘታቸው ሲሆን የዋጋው መወደድ ብቻ ሳይሆን የአቅርቦት እጥረት እንዳለ ያስረዳሉ፡፡ እርሳቸው ያገኙትን ከ2ዐ ኩንታል የማይበልጥ ዱቄት በኪሎ በ8 ብር ስለሚሸጡ ከእርሳቸው የሚረከቡ ቸርቻሪዎች አትርፈው መሸጣቸው ስለማይቀር የዋጋ ጭማሪ መኖሩ ግድ ነው፡፡

"ህብረተሰቡ የኛንም ችግር መረዳት አለበት፡፡ የዋጋ ለውጡ የመጣው ከዋናው ቦታ ስለሆነ በእኛ መማረሩ ተገቢ አይደለም" በማለትም ገልፀዋ፡፡

ከዱቄት አምራቾች ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው ለዱቄት እጥረት የስንዴ ምርት እንደ ልብ አለመገኘቱ ዋነኛው ምክንያት ሲሆን ሰሞኑን የተፈጠረው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትም አንዳንድ አምራቾች ያለቻቸውንም ስንዴ እንዳይፈጩ መሰናክል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ባለፈው ወር በአማካይ ዘጠኝ ብር ይሸጥ የነበረው ምስር ክክ ከቅዳሜ እስከ ሰኞ ባለው ጊዜ ውስጥ ዋጋው በየቀኑ አንድ አንድ ብር እየጨመረ ከትናንት በስቲያ ባለ የገበያ ዋጋ አንዱ ኪሎ ምስር ክክ 13 ብር ገብቷል፡፡ በስድስት ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ሞኮሮኒ 9 ብር ደርሷል፡፡ የአገር ውስጥ ፓስታ ምርቶች በአማካይ 8 ብር እየተሸጡ ይገኛሉ፡፡

አንድ ኪሎ ድንች ከአራት ብር ወደ ስድስት ብር ያደገ ሲሆን በአንዳንድ የአትክልት መሸጫ መደብሮች ደግሞ 5 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል፡፡

ከሌሎች ምርቶች በተለየ መልኩ አቅርቦቱ እየቀነሰ የመጣው የሩዝ ምርት የችርቻሮ መሸጫ ዋጋው አሻቅቧል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየመደብሮቹ አንድ ኪሎ ሩዝ በኪሎ ዘጠኝ ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በአንዳንድ መደብሮች ደግሞ እስከ ዘጠኝ ብር ከሃምሳ ሳንቲም እየተሸጠ መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል፡፡

ሩዝ ከወራት በፊት አንዱ ኪሎ ከ5-6 ብር ይሸጥ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከዋጋው ማሻቀብ በተጨማሪ ከማከፋፈያው እንደልብ እየተገኘ አለመሆኑም ታውቋል፡፡

የሩዝ ምርትን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጥረት እየተፈጠረ መሆኑንና አምራች አገሮችም ወደ ውጪ የሚልኩትን ሩዝ መቀነሳቸው የሚታወቅ ነው፡፡

ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን 91 በመቶ የሚሆን ሩዝ የሚያቀርቡት የእስያ አገራት የሚያመርቱትን ምርት ለራሳቸው ፍጆታ መጠቀማቸውና አንዳንዶቹ አገሮችም ሩዝን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ማቆማቸው የሩዝ ተጠቃሚ አገሮችን "በቂ የሆነ ሩዝ እንዲያገኙ ማድረጉን" የዘገበው ታይምስ መፅሔት በዚህ እጥረት በዋነኝነት የአፍሪካ አገራት ተጐጂ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

ብዙዎቹ ነጋዴዎች እና ሸማቾች አሁን በፍጥነት እየጨመረ ያለው የእህሎችና ሸቀጦች ዋጋ ገበያው ይረጋጋል በሚባልበት ወቅትም ቢሆን አይቀንስም የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ከእጥረትም ሆነ ከሌላ ችግር ጋር በተያያዘ ዋጋቸው ጨምሮ የነበሩ ሸቀጦችና እህሎች ችግሮቹ ሲቀረፉ ዋጋቸው በሳንቲም ልዩነት እንኳን ዝቅ ሲል አልታየም፡፡

ይህም ሆኖ ሕዝረተሠቡ "ለምን?" ብሎ የመጠየቅ ባህሉን አለማዳበሩና ረከሰ በተባለበት ወቅት እንኳን የተጠየቀውን ዋጋ ከፍሎ መግዛቱ የዋጋው መናር እንዳይቀንስ አድርጐታል፡፡

በህብረተሰቡ በኩል ያለው አመለካከት "ምን አማራጭ አለን" የሚል ዓይነት ቢሆንም በመንግሥትም በኩል በነፃ የኢኮኖሚ ገበያ ስም ህብረተሰቡ አለአግባብ እንዲሸምት ሲደረግ ይህ ነው የተባለ ያደረገው መፍትሄ ለውጥ አለማምጣቱን ይጠቁማሉ፡፡
 
< Prev   Next >