| ለ3ዐ ዓመታት |
|
|
| Wednesday, 07 May 2008 | |
ጐመን ከመሸጥ ፈቀቅ ያላለ ኑሮበምሕረት አስቻለው ልደታ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት አስፋልት ዳር ላይ ጐመንና ቆስጣ የሚሸጡ በርካታ ሴቶች አሉ፡፡ ከሌሎቹ ገንጠል ብለው የተመለከትናቸውን በእድሜ የገፉ እናት ቀርበን አነጋገርናቸው፡፡ ወ/ሮ አስናቀች በለው ይባላሉ፡፡ እድሜአቸው በግምት በስልሳዎቹ አጋማሽ ላይ ይሆናል፡፡ የአምስት ልጆች እናት ሲሆኑ ባለቤታቸው በመሞታቸው ልጆቻቸውን ለብቻቸው ማሳደጋቸውን ገልፀውልናል፡፡ “ባለቤቴ ከሞተ ቆይቷል፡፡ እዚህ ልደታ ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ጧፍና እጣን ከዚያም ጐመንና ቆስጣ መሸጥ ከጀመርኩ ከሠላሳ ዓመት በላይ ይሆነኛል፡፡ ይሄን እየሠራሁ አምስቱንም ልጆቼን ለማስተማር ታግያለሁ” በማለት ሁለት ወንድ ልጆቻቸው በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ዘምተው አንደኛው ሲመለስ ስለሌላው በሕይወት መኖርና አለመኖር እስከ አሁንም የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ነግረውናል፡፡ አንዷ ልጃቸው ከአሥረኛ ክፍል ውጤት ስላልመጣላት ትምህርቷን መቀጠል አልቻለችም፡፡ የመጨረሻዎቹ ሁለት ልጆቻቸው የሰባትና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያ ደጃፍ ጧፍና እጣን መሸጥ አላዋጣ ሲላቸው ጐመንና ቆስጣ መሸጥ መጀመራቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ አስናቀች የሚኖሩት አምስተኛ አካባቢ ሲሆን ከንጋቱ አሥራ አንድ ሠዓት ላይ ከቤታቸው በመነሳት የሚሸጧቸውን አትክልቶች ከመኪና ላይ ለመረከብ ልደታ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት አሥራ ሁለት ሠዓት ሳይሞላ መገኘት ግዴታቸው ነው፡፡ ከአትክልት አከፋፋዮቹ ላይ በገንዘብ የመግዛት አቅም ስለሌላቸው የሚረከቡት በዱቤ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአጠቃላይ የሚያገኙትን ትርፍ አነስተኛ ያደርገዋል፡፡ በቀን የሠላሳና የአርባ ብር አትክልት ቢረከቡ የሚያገኙት ትርፍ ከአራት ብር እንደማይበልጥ አመልክተዋል፡፡ ካልተሸጠላቸው ቆጥረው በማግስቱ ለአከፋፋዮቹ መልሰው ያስረክባሉ፡፡ “እኔ ቤት ጤፍም አይሸመትም፣ እንጀራም አይገዛም ቂጣውን ጋግሬ ወይም ዳቦ ገዝቼ ጐመን በመቀቀል ልጆቼን አበላቸዋለሁ፡፡ ጐመኗም ብትሆን ከምሸጠው ተበጣጥሳ የምትቀረዋ ናት፡፡ ለሚማሩት ልጆቼም ዓመት መጀመሪያ ላይ አንዳንድ ዘመድ ደብተርና እስኪሪቢቶ ይገዛላቸዋል፡፡ ዓመት በአልም ለኛ እንደሌው ቀን ነው” ወ/ሮ አስናቀች እንዳሉት በፊት የፆም ወቅት ላይ ጥሩ የአትክልት ገበያ ነበር፡፡ አሁን ግን የፆም ወቅት ሆነም አልሆነ ብዙም የተለየ ነገር የለም፡፡ ሁለትም ሆነ ሦስት ብር ትርፍ ለማግኘት ከአከፋፋዮች ላይ የተረከቡትን ሸጠው መጨረስ ስላለባቸው ገበያ የጠፋ እለት እስከ ምሽቱ አንድና ሁለት ሠዓት ሊያመሹ ይችላሉ፡፡ ስናነጋግራቸው ከረፋዱ አራት ሠዓት ተኩል ገደማ ነበር፡፡ የስኳር ሕመምተኛ መሆናቸውን በመግለፅ ይቅርታ ጠይቀውን አንዲት ባለ ሀያ አምስት ሣንቲም ዳቦ የያዘች ስስ ፌስታል በማውጣት እየቆረሱ መብላት ጀመሩ፡፡ “ከቤቴ የምወጣው በሌሊት ስለሆነ አልበላም፡፡ እዚህ እንደደረስኩም ከመኪና ላይ መረከብ ከዚያም ቦታ በማፅዳትና አትክልቶቹን ለመደርደር ወዲያ ወዲህ ስል ይረፍዳል፡፡ ምሳ ሠዓት ላይም ከዚሁ አካባቢ ዳቦ ገዝቼ ያችን በልቼ እውላለሁ፡፡ ለነገሩ ዳቦ እንዳልበላ ሀኪም ከልክሎኝ ነበር” በማለት ምንም እንኳ የስኳር ሕመምተኛ በመሆናቸው የተለያዩ ጥንያቄዎችን ቢያደርጉም አሁን ባሉበት የኑሮ ሁኔታ ይህን ልብላ ይህን ልተው ማለት እንደማይችሉ ገልፀዋል፡፡ ሠዓት ጠብቆ መመገብም ሆነ ይህ ሥራ አድካሚ ነው ልተወው ማለት ለወ/ሮ አስናቀች ፈፅሞ የማይቻል ነው፡፡ ልጆቻቸው ራሳቸውን ባለመቻላቸው ዛሬ በደካማነታቸውም ቢሆን እነሱን የመመገብ ሀላፊነት አለባቸው፡፡ “እኛ ቤት ቁርስ፣ ምሣ፣ እራት የሚባል ነገር የለም፡፡ ማታ ያገኘኋትን ይዤ እገባለሁ፡፡ እሷን ተካፍለን እናድራለን፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ተበጣጥሶ የተራረፈ ጐመን ይዤ በመግባት ነው የምመግባቸው ዘወትር ጐመን፣ ዳቦና፣ ቂጣ ነው፡፡ አንድ ብር ከሀምሳ እንጀራ መግዛት እንኳ ለእኔ ከባድ ነው” ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል ይሸጡ የነበረው ቤተክርስቲያኑ አካባቢ ነበር፡፡ ከዚያ እንዲለቁ ተደርገዋል፡፡ አሁን የሚሸጡበት ቦታ ምንም ዓይነት መጠለያ ስለሌለው ለፀሀይና ለዝናብ የተጋለጠ ነው፡፡ ከጤናቸው አንፃርም ሆነ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ሌላ ነገር ለመስራት ማሰባቸውን አስመልክተን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ተስፋ መቁረጥ በተሞላበት አንደበት “ምን እሠራለሁ፡፡ ደግሞስ በየትኛው ገንዘቤ በዚያ ላይ በሽተኛ ነኝ፡፡ እድሜዬም እየገፋ ነው” በማለት መልሰውልናል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |