Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 25th
Home arrow Sections arrow የካናዳ ኤምባሲ ለካንሰር በሽተኛዋ...
የካናዳ ኤምባሲ ለካንሰር በሽተኛዋ... Print E-mail
Thursday, 10 January 2008

የካናዳ ኤምባሲ ለካንሰር በሽተኛዋ ህፃን ቪዛ ከለከለ

- ሼህ መሀመድ አላሙዲ ወጪዋን በመሸፈን ወደ ባንኮክ ላኳት

የጐንደር ሆስፒታልና የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ቦርድ ውጭ ሀገር ሄዳ እንድትታከም የፀደቀላት ስርጉት ግዛቸው የተባለች የ14 ዓመት ህፃን በካናዳ ኤምባሲ ቪዛ ተከለከለች፡፡ ሼህ መሀመድ አላሙዲን ከ80 ሺህ ዶላር በላይ በማውጣት ታዳጊ ወጣቷን ለህክምና ወደ ባንኮክ እንድትሄድ አድርገዋል፡፡

በካንሰር በሽታ ምክንያት ከወገብ በታች ፓራላይዝድ የሆነችው ታዳጊ ወጣት ስርጉት ህክምናዋን ስትከታተል ከነበረችበት ከጐንደር ሆስፒታልና ከጥቁር አንበሳ የህክምና ቦርድ ውጭ አገር ሄዳ ህክምና እንድትከታተል የሚገልፅ ማስረጃ ቢሰጣትም ውጭ ሀገር ከሄደች እዚያው ልትቀር ትችላለች በሚል ምክንያት የካናዳ ኤምባሲ ቪዛ እንደከለከላት ካገኘነው መረጃ ለማወቅ ችለናል፡፡

በካንሰር በሽታ ስትሰቃይ የቆየችው ልጃቸው ወደ ካናዳ ሄዳ እንዳትታከም በመደረጉ ለከፍተኛ ሀዘን እና ብስጭት ተጋልጠው እንደነበር ለሪፖርተር ጋዜጣ የገለፁት የስርጉት አባት አቶ ግዛቸው፣ ተስፋ በቆረጡበት ጊዜ ሼህ መሀመድ አላሙዲን ደርሰው የልጅቷን ሙሉ ወጪ በመሸፈን ለህክምና ወደ ባንኮክ እንድትሄድ በማድረጋቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለሀብቱ ለህፃኗ የፈፀሙት ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስመሰግናቸው መሆኑንም አቶ ግዛቸው አክለው ገልፀዋል፡፡

መጀመሪያ ላይ ልጃቸው ወደ ካናዳ ሄዳ እንድትታከም በተጠየቀ ጊዜ የካናዳ ኤምባሲ በቂ ገንዘብ የላችሁም በሚል ምክንያት የቪዛ ፈቃድ ከልክሎ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ግዛቸው ካናዳ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው የተጠየቀውን ገንዘብ ባንክ ቤት ካስያዙ በኋላ የቪዛ ፈቃድ ይሰጣታል ብለው ሲጠብቁ ልጅቷ እዚያው (ካናዳ) ልትቀር ትችላለች በሚል ምክንያት በካንሰር በሽታ የምትሰቃየውና ከወገብ በታች ፓራላይዝድ የሆነችው ልጃቸው ቪዛ እንደተከለከለች በምሬት ገልፀዋል፡፡ የካናዳ ኤምባሲ በህፃኗ ላይ የፈፀመው ሰብዓዊነት የጐደለው ተግባር የሚያሳዝን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የጥቁር አንበሳ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዳንኤል አንድ በሽተኛ በአገር ውስጥ ባለው የህክምና ቴክኖሎጂና አቅም መታከም እንደማይችል ከተረጋገጠ የህክምና ቦርዱ የመሸኛ ደብዳቤ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመፃፍ ግለሰቡ ውጭ አገር ሄዶ እንዲታከም እንደሚደረግ ገልፀው ከህክምና ማስረጃ ውጭ ያለውን ጉዳይ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚከታተለው ተናግረዋል፡፡ ታዳጊ ወጣት ስርጉት ስላጋጠማት ችግር ያውቁ እንደሆን ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱም በየጊዜው የተለያዩ ሰዎችን ጉዳይ የምመለከት በመሆኑ ልጅቷ አጋጠማት ስለተባለው ችግር አላስታውስም፣ ነገር ግን አንድ ታማሚ ውጭ አገር ሄዶ እንዳይታከም ቪዛ ተከለከለ የሚባል ነገር ስሰማ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜየ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ችግር አጋጥሞን አያውቅም ብለዋል፡፡

ለታዳጊ ወጣት ስርጉት ግዛቸው ቪዛ የከለከለውን በናይሮቢ የካናዳ ኤምባሲን ኢትዮጵያ በሚገኘው ቢሮው አማካኝነት ጉዳዩን በማስመልከት ለማነጋገር  ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ታዳጊ ወጣት ስርጉት ከአባቷ ጋር በመሆን ቅዳሜ እለት ወደ ባንኮክ የተጓዘች ሲሆን ጠቅላላ የህክምና ወጪዋም ከ80 ሺህ ዶላር በላይ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

በኃይሌ ሙሉ

 
< Prev   Next >