Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የመንገድ ፈንድ ለመሰብሰብ ካቀደው...
የመንገድ ፈንድ ለመሰብሰብ ካቀደው... Print E-mail
Wednesday, 07 May 2008
የመንገድ ፈንድ ለመሰብሰብ ካቀደው ግማሽ ያህሉን አልሰበሰበም
የውጭ ኮንትራክተሮች ቁጥር 80 በመቶ ጨምሯል

በዳዊት ታዬ

የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በ2000 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ለመሰብሰብ ካቀደው ገንዘብ ውስጥ ግማሽ ያህሉን እንኳ መሰብሰብ አለመቻሉና ለመስጠት ካቀደው ገንዘብ ውስጥ ያሳካው 42 በመቶውን ብቻ መሆኑን የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ሪፖርት አመለከተ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በመንገድ ሥራ የተሠማሩ የውጭ ኮንትራክተሮች ቁጥር 80 በመቶ ጨምሯል፡፡

የሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው በ2000 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የመንገድ ፈንድ ጽ/ቤት ተብሎ በእቅድ ተይዞ የነበረው 752 ሚሊዮን 409 ሺህ ብር ሲሆን መሰብሰብ የቻለው ግን 352 ሚሊዮን 126 ሺህ ብር ብቻ ነው፡፡

ይህም የእቅዱን 47 በመቶ ብቻ ያሳካ መሆኑን የሚገልፀው ይኸው ሪፖርት አፈፃፀሙ ከእቅዱ በታች የሆነበት ምክንያት የነዳጅ ድርጅቶች ከሐምሌ እስከ ጥቅምት ያለውን ፈንድ ብቻ በማስገባታቸውና ገቢ እንዲሰበስቡ ውክልና የተሰጣቸው አካላት የሰበሰቡትን ገንዘብ በጊዜ ገቢ ባለማድረጋቸው እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩልም ጽ/ቤቱ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለመንገድ ጥገናና ደህንነት 959.67 ሚሊዮን ብር ክፍያ ለመፈፀም አቅዶ ወጪ ያደረገው ግን 401.18 ሚሊዮን ብር በመሆኑ በዚህም ረገድ አፈፃፀሙን የእቅዱን 42 በመቶ ብቻ እንዲሆን አድርጐታል፡፡

ጽ/ቤቱ ለመንገድ ጥገና የሚሆን ፈንድ በማሰባሰብ ለየክልሎች የሚያከፋፍል ሲሆን ፈንዱንም የሚሰበስበው በዋነኛነት ከነዳጅ ሽያጭ ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰው ደግሞ ጽ/ቤቱ በተጨማሪ የገቢ ምንጮችንና የገቢ ማስፋፊያ መንገዶች ላይ ጥናቶችን ለማካሄድ ታስቦ ጥናቱን ለማስጠናት ከመንገድ ፈንድ፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ ከትራንስፖርት ባለስልጣን የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ረቂቅ ጥናቱ መዘጋጀቱ አስረድቷል፡፡

ጽ/ቤቱ በ2000 በጀት ዓመት የመንገድ ፈንድ ገቢ ከጥገና ፍላጐት እና ከትራፊክ ደህንነት ፕሮግራሞች ጋር አጣጥሞ የማሳደግ ስትራቴጂካዊ እቅዱን ለማሳካት ለመሰብሰብ አቅዶት የነበረው ጠቅላላ ገንዘብ 1.002 ቢሊዮን ብር እንደነበርም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩልም በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሥር በሚከናወኑ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች ተሳታፊ የሚሆኑ የውጭ ኮንትራክተሮች ቁጥር 80 በመቶ መጨመሩን ይኸው ሪፖርት ጠቁሟል፡፡

ባለስልጣኑ ግንባታዎችን የሚያካሂደው በሶስት ምድቦችን ተከፋፍሎ፤ በውጭ አገር ተቋራጮች፣ በአገር ውስጥ ተቋራጮችና በራስ ሃይል የሚሠሩ ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ በበጀት ዓመቱ በዋና ዋና የመንገድ ሥራዎች 36 የውጭ ኮንትራክተሮች 808 ኪ.ሜትር መንገድ ለመሥራት ታቅዷል፡፡ ይህም የውጭ ኮንትራክተሮች ተሳትፎ ቁጥር ከ1999 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ16 ወይም በ80 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

በበጀት ዓመቱ በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የሚሠራ ተብሎ በእቅድ የተያዘው መንገድ ርዝማኔ 614 ኪሎ ሜትር ሲሆን የኮንትራክተሮቹ ቁጥር ደግሞ 27 መሆናቸውን ያትታል፡፡ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በተያዘው የበጀት ዓመት በመንገድ ሥራው ላይ የሚሳተፉ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ብዛት በ13 ወይም በ93 በመቶ ጨምሯል፡፡

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ በዋና ዋና የመንገድ ሥራዎች በኮንትራት ለመሥራት ከታቀዱት 63 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ በውጭ ኮንትራክተሮች ይሠራሉ የተባሉት 36 ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ሥራው ለኮንትራክተሮቹ የተሰጠ ሲሆን በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ይሠራሉ ከተባሉት 27 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ 23ቱ ሥራው የተሰጠ ሲሆን ቀሪዎቹ እስከ በጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ድረስ አራት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
 
< Prev   Next >