| ማረሻን ማረሻ ማለት |
|
|
| Wednesday, 07 May 2008 | |
|
የትራንስፖርት ፈላጊው ቁጥር በጣም በዛብኝ፡፡ በታክሲ፣ በከተማ አውቶቡስ፣ በቤት መኪና፣ በእግር ወዘተ. የሚጓዘው መንገደኛን በመቶኛ ምን ያህል መሆኑን ማስቀመጥ ተሳነኝ፡፡ በርከት ያለው ቁጥር በታክሲና በአውቶቡስ የሚጓጓዘው መንገደኛ ነው፡፡
ገና ከጧቱ 1፡30 ሰዓት ላይ ሰው ፈስሷል፡፡ ትርምሱ፣ ግፊያው ያስፈራል፡፡ ከሌላ ታክሲ ወርጄ ሁለተኛውን ታክሲ ለማግኘት ዕድሉ ጠባብ መሆኑን ተሰማኝ፡፡ የፈለገው ይጥበብ እንጂ ከመሄድ ግን አልቀርም፡፡ ለመጋፋት፣ በግፊያውም አሸንፎ ለመውጣት በቅድሚያ ሰውነትን ማሟሟቅ ያስፈልጋል፡፡ በጉልበት መጠቀም የግድ ይሆናል፡፡ አለበለዚያ ቆሞ መዋል ነው፡፡ "እንዴት በዚህ ዕድሜዬ እጋፋለሁ? እንዴት እነዚህን የዕድሜ አንጋፋዎችን እገፈትራለሁ?" የሚል ጥያቄ መጠየቅ ከበዛ ከትራንስፖርቱ መገለል ይሆናል፡፡ ያለው ምርጫ ተጋፍቶ አሸንፎ ማምለጥ ነው፡፡ ነፍሰ ጡሮችን፣ ደካሞችን፣ አዛውንቶችን የሚያስቀድም ብዙም አይገኝም፡፡ በጣም የበዙትን ተሣፋሪዎች በመተው ወደ መታጠፊያው ጋ ሄድኩ፡፡ የሰው ብዛት ስለሚቀንስ የተሻለ ዕድል ለማግኘት ብዬ፡፡ እዚያ ደግሞ ከግፊያው በላይ ያማረረን ታክሲዎቹ "አይጭንም" እያሉ ተሳፋሪውን ጥለው መፈርጠጣቸው ነው፡፡ ሞልተው ይመጣሉ ገልብጠው ይሮጣሉ፡፡ ጥቂቶቹ መስመሩን ያሳጥሩና ያጋድላሉ፡፡ የሚጭኑበት ቦታ ለመናገርም ብዙ ደጅ ተጠንቶ ነው፡፡ ብዙ ሰዓት ከገደልኩ በኋላ የሞት ሞቴን በሌሎችም ዕርዳታ ተሳፈርኩ፡፡ ይህ የተሳፈርኩበት ታክሲ ሁለተኛዬ ነው፡፡ ሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ይቀረኛል፡፡ ሦስተኛውም ላይ ጦርነት ይጠብቀኛል፡፡ በተለይ ከግፊያ ለማምለጥ ማልዶ መውጣት ብልህነት ነው፡፡ ሁሌ በጧት ለመውጣት ግን አይሳካም፡፡ ተሣፋሪዎች ቦታ ቦታ ከያዝን በኋላ "መሣለሚያ አይጭንም፡፡ መሣለሚያ የገባችሁ ካላችሁ 1.35 ነው" የሚል ማሳሰቢያ አዘል ማስጠንቀቂያ ከወያላው ተላለፈ፡፡ ከዚህም በላይ መመሪያ ቢያወርድ ለጊዜው የሚቃወመው ላይኖር ይችላል፡፡ ወይም አንድ ሰሞን ተንጫጭተን እንተዋቸውና በሚቀጥለው ቀን ተግባራዊ ያደርጉታል፡፡ ታክሲዎች ታሪፍ ሲጨምሩ እንደ ቀልድ ነው፡፡ አንዱ ደፋር ወያላ ይጀምረዋል፣ ሌሎች ይከተሉታል፡፡ ከአውቶቡስ ተራ አምባሳደር ወይም ጋንዲ ሆስፒታል ሁለት ብር የሚያስከፍሉ ታክሲዎች አጋጥመውኛል፡፡ ምርጫ የሌለው ለስልሳ አምስት ሣንቲም ብዬ ከሥራ አልቀርም በሚል የተጠየቀውን ከፍሎ ይጓዛል፡፡ ከዚህ በፊት ደጋግመን ያነሳነው የሥነ ምግባር ጥያቄ በቅርብ ጊዜ ምላሽ ያገኛል ማለት ያዳግታል፡፡ ከጎኔ የተቀመጡት ዘናጭ ተሣፋሪ ሽቷቸውን ሲጋብዙኝ ቆይተው ለውይይት የሚሆን ርዕስ ፈነጠቁልኝ፡፡ "እኛ ኢትዮጵያውያን ስለ ዕድገት ስናቅድ ጎን ለጎን የባሕርይ ለውጥ እንዲመጣ ፕሮፖዛል መንደፍ አለብን፡፡ በባሕሪያችን ላይ ተሠርቶ ለውጥ ካልመጣ የለማውም ይፈርሳል፣ የተገነባውም ይናዳል" አሉኝ፡፡ አባባላቸው ግልጽ እንዳልሆነልኝ ስለተረዱ የበለጠ ማብራራት ጀመሩ፡፡ መጀመሪያ ሕዝቡንና አገራችንን መውደድ መቻል አለብን፡፡ ሕዝቡንና አገራችንን ከልብ ከወደድን መፍትሄ ለማምጣት አይከብድም፡፡ የሚሣፈረው፣ የሚጉላላው፣ የሚንገላታው ወገናቸው መሆኑን ተረድተው በአግባቡ ሊያገለግሉት ኃላፊነት እንዳለባቸው ቢረዱ የትራንስፖርት ችግር በመጠኑም ቢሆን ይሻሻላል፡፡ መተሳሰብ ቢኖር መፍትሄው ቀላል ይሆናል፡፡ በዚህ በዚህ ላይ በቅድሚያ መሠራት እንዳለበት አስረግጠው ነገሩኝ፡፡ አገልግሎት ሰጪዎችን ብቻ ሳይሆን ተገልጋዩም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ ነገም ከነገወዲያም አገልግሎት ፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦ ከእሱ የሚጠበቀውን መፈፀም ይኖርበታል፡፡ የሚያጠፉ ተሣፋሪዎችን መምከር፣ መገሰጽ ወዘተ. መቻል አለበት፡፡ የባሕሪይ ለውጥ ባሉት ላይ አተኮርኩ፡፡ እውነታቸውን ነው እኛ ኢትዮጵያውያን የባሕርይ ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ ብዙዎቻችን ድርጊት ላይ ከመሳተፍ ይልቅ ነቀፋው ላይ እንበረታለን፡፡ የሚሠራን ሰው ከማገዝ፣ የተሳሳተን ከማረም ይልቅ እንኮረኩማለን፡፡ መተሳሰብ ይጎድለናል፡፡ በአፍ "አገራችንና ሕዝባችንን እንወዳለን" እንላለን፡፡ በተግባር ግን አገራችንና ሕዝባችንን ለመጎተት ድንጋይ እንፈነቅላለን፡፡ ሕዝብ የሚባለው እኮ በትራንስፖርቱ አካባቢ የሚጉላላውና በየቦታው ያለው ተደምሮ ነው፡፡ በየትም ቦታ የምናገኘው ሰው የሕዝቡ አካልና አባል ነው፡፡ ከልብ አገርና ሕዝብን የምንወድ ከሆነ እያንዳንዱ ሰውንም መውደድ አለብን፡፡ ነገር ግን ንግግራችንና ተግባራችን ይለያያል፡፡ "ኢትዮጵያ አገሬ. . ". ሲል የነበረ ሰው አገርን ሲቦረቡር፣ በሙስና ተጨማልቆ መውጪያ መግቢያ ሲያጣ ይታያል፡፡ አገሬን ሕዝቤን እወዳለሁ ሲል ቆይቶ ባሌስትራን ወርቅ ብሎ ይሸጣል፡፡ ቀይ አፈርን ከበርበሬ፣ ሙዝና ነጫጭ ነገርን ከቅቤ ጋር ደባልቆ ሸጦ የሰውን ዕድሜ ያሳጥራል፡፡ ከእውነተኛው ይልቅ አስመሳዩ ይበዛል፡፡ ውጭ አገር ትምህርት ላይ ቆይቷል፣ ቁልፍ ቦታ ነበር የተባለውም ዲያስፖራ እዚህ ይመጣና በተልካሻ ነገር ተሰማርቶ ታገኙታላችሁ፡፡ አገሬን፣ ሕዝቤን ሲል የቆየው ዲያስፖራ ለኢንቨስትመንትና ለመኖሪያ ብሎ ቦታ ይጠይቃል፡፡ ሕዝብን ያስነሳል፡፡ ሕዝብን አፈናቅሎ ለሕዝቡና ለአገሩ የሚጠቅም ኢንቨስትመንት መሥራት ሲገባው መሬት ንግድ ውስጥ ይገባል፡፡ የላሜራ ኪዮስኮችን ሰርቶ ማምታታትና ማጭበርበር ይጀምራል፡፡ ሕዝቡን ለማገልገልና ለማልማት ሳይሆን ለማጭበርበር እንደመጣ ግልጽ ይሆናል፡፡ ይሄኔ ተቃውሞው ይበረታበታል፡፡ ያኮርፋል፡፡ ከመከሰስ ይልቅ ይከስሳል፡፡ የራሱን ጉድፍ ትቶ የሌላውን ጉድፍ ይጎረጉራል፡፡ ኢትዮጵያውያን ቆም ብለን ስለ ራሳችን ማሰብ አለብን፡፡ ከተራው የታክሲ (የትራንስፖርት) ችግር አንስቶ እስከ ግዙፉ ድረስ መፍታት የምንችለው ደካማ ጎናችንን አስወግደን ጠንካራ ጎናችንን ስናጠናክር ነው፡፡ ማነው አገሩንና ሕዝቡን ከልብ የሚወድ? ከሰው መሃል አጥፊና ወንጀለኛ የትም አገር ይኖራል፡፡ ይኼ እውነት ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ግን የበዛ ይመስላል፡፡ በቀለበት መንገድ ላይ የተሰራው ብረት በሌሊት ቆርጦና ነቃቅሎ የሚሸጥ ኢትዮጵያዊ እውነት ይህ ሰው ሌባ ብቻ ነው? ከአንድ ዓመት በላይ አልተደረሰብኝም ብሎ ባሌስትራን ወርቅ ነው ብሎ የሚሸጥ፣ አገሩንና ሕዝቡን እየገደለ የሚከብር ኢትዮጵያዊ እውን ኢትዮጵያዊ ነው? ዘርዘር ስናደርገው የምንመዛቸው የተለያዩ ርዕሶች አሉ፡፡ ሥልጣን ላይ ያለውንም መመልከት ችንችላለን፡፡ የሚወጡ አዋጆች፣ መመሪያዎች እውነት ለአገርና ለሕዝብ እንዲጠቅሙ ታስበው ወይስ የሥልጣን ጊዜን ለማራዘም? ባለሥልጣኖች ለሕዝቡ ቃል በገቡትና በሚሉት መሠረት ይፈጽማሉ? ስንቱ ባለሥልጣን ነው ከጎጥ፣ ከጎሳ፣ ከዘር አባዜ ነፃ ሆኖ ለእናት ኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሎ የሚሠራው? በሥልጣኑ ተጠቅሞ ሕዝብ በሕዝብ ላይ አነሳስቶ ያፋጀ፣ "በሏቸው" ያለ፣ በሰው ደም እጁን የታጠበ ስንት ወንጀለኛ ባለሥልጣን አለ? ስለ ባሕሪይ ለውጥ ለማስረዳት ብዬ በጣም ራቅኩ፡፡ ማለት የፈለግኩት የገባችሁ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ከዚህ አንፃር ራሳችሁን ቤተሰባችሁንና ጓደኛችሁን መዝኑ፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጥፋት አለበት፡፡ ማድረግ የሚገባውን ያደረገ ከመቶ ምን ያህል እንደሆነ መገመት ይከብደኛል፡፡ ማጠቃለያው የባሕርይ ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል ነው፡፡ ከመገንባት ይልቅ ማፍረስ፣ ከማረም ይልቅ አቃቂር ማውጣት፣ ታግሎ ከማሸነፍ ይልቅ አኩርፎ መራቅ ይበዛልና ራሳችንን እንመርምር፡፡ እንመርመር፡፡ መልካም ጉዞ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |