Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow “የደረስኩበት” መጽሐፍ ስህተት
“የደረስኩበት” መጽሐፍ ስህተት Print E-mail
Wednesday, 07 May 2008
አቶ ማሞ ውድነህ “የደረስኩበት” በሚል ርዕስ አዘጋጅተው ያሳተሙትን ክፍል ሁለት፣ አንብቤያለሁ፡፡ በመጽሐፋቸው ውስጥ ራሳቸውን ለደርግ የለውጥ ሐዋርያነት አዘጋጅተውና አስፈቅደው አጃቢዎች ተሰጥተዋቸው በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በወሎ ክፍለሀገር ባደረጉት “ዘመቻ” ከምክትል አስተዳዳሪው ተገለፀልኝ የሚሉትን የደርግን መንግሥት የተቃወሙትን ሰዎች ስም ዝርዝር ሲዘግቡ የአባቴን የደጃዝማች ብርሃነመስቀል ደስታን (ካሣ በማለት) ስም ጠቅሰዋል፡፡
ስለ ደጃዝማች ብርሃነ መስቀል የደርግ ተቃውሞ ምክንያት ሲያቀርቡ፣ “አብዮቱ አስበርግጓቸው” ሲሉ የድፍረት ግምታቸውን አስፍረዋል፡፡ የተጠቀሙበት ቃል ለተቃዋሚነት ያነሳሳቸውን ምክንያት ከራሳቸው ይልቅ አቶ ማሞ እንዳሰቡት የሚናገሩበት መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ደጃዝማች ብርሃነ መስቀል በተቀዋሚነት የተነሱት ከፍተኛ የንጉሠ ነገሥቱ ባለስልጣኖች ጥፋት ካለብን በሕግ ቅጣታችንን እንቀበላለን፤ ከሌለብንም ነፃ እንወጣለን፤ ብለው በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለሕግ የሰጡትን ሰዎች ደርግ ያለፍርድ በመፍጀቱ እንደነበር ከእኛና ከእርሳቸው በላይ አውቃለሁ የሚል ካለ ያስቃል፡፡

በደርግ ግድያ ውስጥ አጎታቸው፣ ታናሽ ወንድማቸው፣ የአጎታቸው ልጅ፣ ሌሎችም ዘመዶችና የሥራ ባልደረቦቻቸው ተገድለዋል፡፡ በዚህ ወቅት ምርጫቸው ምን መሆን ነበረበት ይላሉ? ለምን ተቃወሙ? እሳቸውስ ለምን እጃቸውን ሰጥተው አልሞቱም? የሚሉ ከሆነ ይህ የሳቸው ምርጫ አልነበረም፡፡ በደርግ ላይ ለሚነሳ ተቃውሞ ምክንያት ከደርግ ጋር የሚሰራ ሰው ብያኔ ለመስጠት ሲነሳ ጥቂት ማፈር ያለበት ይመስለኛል፡፡ ያለፍትህ የሰላማዊ ሰዎች መገደል፣ ለአቶ ማሞ ከተቃውሞ የሚያስነሳ ነገር ካልሆነ ያ ሌላ ነገር ነው፡፡

አውሮፕላኑ በመቃጠሉ ለሚቀርበው ሕጋዊ ጥያቄ በጊዜው ተገቢ መልስ ይሰጥበታል፡፡ አቶ ማሞ ራሳቸውን ብቻ ለአገር ንብረት ተቆርቋሪ ለማስመሰል ሌላ ሰው መወንጀል ከባድ ግምት ላይ ይጥልዎታል፡፡ እንዲህ አይነት አስተያየት የሚሰጥ ሰው ተቃውሞ ምን እንደሆነ፣ የትጥቅ ትግልስ ምን ማለት እንደሆነ፣ የሚያውቅ ቢሆን የተሻለ በሆነ ነበር፡፡

እዚህ ላይ ለፀሐፊው ላስገነዝብ የምፈልገው አባቴ ደጃዝማች ብርሃነ መስቀል ደስታ ለአገርና ለወገን ያላቸው ፍቅርና ለንብረቷም ለመቆርቆር በማንኛውም መስፈርት ቢለካ ከአቶ ማሞ ቢበልጥ እንጂ የማያንስ መሆኑን ነው፡፡ በተለይም ለማንኛውም ሰው የሚሰጡት አክብሮትና የታረመ አነጋገራቸው በህዝብ ዘንድ ልዩ መታወቂያቸው መሆኑን ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡

አባቴ በደርግ ላይ የነበራቸውን ተቃውሞ፣ አቶ ማሞ ከመስመራቸው ወጥተው ፈራጅና ከሳሽ ለመሆን መቃጣታቸው ሳያንስ፣ ሳያገኟቸው እንዳገኙዋቸው አድርገው መፃፋቸው ያስገምታል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ሳይጠይቋቸው ጥያቄያቸው ገብቷቸው መልስ ከመስጠት ፈርተው እንዳመለጡ አድርገው ለህዝብ ንባብ ማቅረባቸው ቤተሰብን ቢያሳዝንም የበለጠ አንባብያን ከፍተኛ ትዝብት እንደሚሰማቸው አልጠራጠርም፡፡

አቶ ማሞ፣ ለደጃዝማች ብርሃነ መስቀል ሰላምታ ለመስጠት እንደቀፈፋቸው ጽፈዋል፡፡ በደም ከሚዋኙ ሰዎች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ሳይቀፋቸው፣ ንጹህ ሰው ይቀፋቸዋል፤ ማለት ነው? ወይስ ለዚህ አገር ተቆርቋሪ እርሳቸው ብቻ እንደሆኑ ለማስመሰል የሚያደርጉት ጥረት ነው? ለሁሉም ሀሰተኛ ጽሁፍ መሆኑን ይህን ለሚያነቡ ሁሉ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡

ሲጠቃለል ደጃዝማች ብርሃነ መስቀል ወደ ትጥቅ ትግል የወጡት በርግገው ሳይሆን ፍትሕ የጐደለበትን፣ ሕዝቦች እንደ ከብት እየተነዱ የሚታረዱበትን፣ ሥርዓት ለመታገል አምነውበት ነው፡፡ በ1984 ሒልተን ሆቴል እንዳገኟቸውና ጥያቄያቸውን ጠርጥረው ሳያገኟቸው እንደሄዱ የፃፉትም ሐሰት ነው፡፡ ራሳቸው ለአገር ተቆርቋሪ፣ ሌላውን ተቃዋሚ አጥፊ ለማድረግ የተነሱበት መሰረት፣ ደም እንደ ጅረት በሚጎርፍበት፣ የአገሪቱ ሃብት ብቻ ሳይሆን የሰው ኃይል በሚወድምበት ጊዜ የተወሰደ ርምጃ ላይ መሆኑ በራሱ ሊያሳፍራቸው ይገባል፡፡

ስለ አውሮፕላኑ መቃጠል ርሳቸው የካድሬውን ገለፃ አምነው ለመፍረድ እንደሚቸኩሉት ሳይሆን በሕግ ለሚቀርብ ነገር ሁሉ እውነቱን ለማውጣት ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡

(ሒራሚ ብርሃነመስቀል ደስታ) 
 
< Prev   Next >