Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ እንደገና
ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ እንደገና Print E-mail
Wednesday, 07 May 2008
Imageበሔኖክ ያሬድ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ራስ መኮንን አዳራሽ ዓርብ ሚያዚያ 24 ቀን 2000 ዓ.ም አንድ ትዕይንት ቀረበ፡፡ በባህል ዙሪያ ያጠነጠነ ነው፡፡ ከአራት ዐሥርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረ የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ አስተባባሪ አሜሪካዊ ቻርልስ ሳተን በኢትዮጵያ ባህላዊ ልብስ እጀ ጠባብ ደምቆ ይታያል፡፡
አብረውት የቀድሞ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ባልደረቦች የነበሩት ጌታ መሳይ አበበ፣ መላኩ ገላውና ዮሐንስ አፈወርቅ እንደርሱው ሁሉ በእጀጠባብ ይታያሉ፡፡ ሁሉም ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን አንግተዋል፡፡

የተቋሙ ዳይሬክተር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ እንደተናገሩት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በራስ መኮንን አዳራሽ አንድ ፈረንጅ ተቀምጦ በአማርኛ በአንደበተ ርቱዕነት ሲናገር ማየት አስደናቂ ነው፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ምሁራን ከአማርኛ ይልቅ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ይቀናቸዋል፡፡ አሜሪካዊ ቻርልስ ሳተን ግን አማርኛን መርጧል፡፡ ለአማርኛ ክብር ሰጥቶታል፡፡

የመሰናዶው ትኩረቱ በቀድሞው የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ አባላት በተለይ የተዘጋጀው “ዞሮ ገጠም” በአሜሪካ ሕክምና ላይ በሚገኘው የኦርኬስትራው መሥራችና ዳይሬክተር ተስፋዬ ለማ ሲዲን ለማስመረቅ ነው፡፡ ሲዲው ቀደም ሲል በአሜሪካ ተሰራጭቶ ከዘጠኝ ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ማጠናከሪያ ተበርክቷል፡፡ በአዲስ አበባው ሽያጭ 10ሺ ዶላር ለማድረስና ለተቋሙ 100ሺህ ብር ለማበርከት ማለማቸውን ገልጸዋል፡፡ ሲዲው በተስፋዬ ለማ ዳይሬክተርነት በዐቢይ ሰሎሞን ስቱዲዮ በጥራት የተዘጋጀ መሆኑን የገለጸው ቻርልስ ሳተን በዕለቱ በአማርኛ በቁም ጽሕፈት ራሱ ጽፎ ራሱ ባነበበው ንግግሩ ምሽቱ ያለፈውንና የመጪው ትውልድ የሚገናኙበት፣ ከ45 ዓመት በፊት የተቋቋመው ኦርኬስትራ ኢትዮጵያን የማየት እድል ለነበራቸው በትዝታ ወደ ኋላ የሚጓዙበት፣ የአሁን ወጣቶች ደግሞ ከኦርኬስትራው ጋር ይበልጥ የሚተዋወቁበት መድረክ መሆኑን ገልጿል፡፡

ቻርልስ ሳተን ማሲንቆውን እየከረከረ ..የዛሬ ሳምንት.. የተሰኘውንና በፍቅር ላይ ያተኮረውን ፣መጨረሻውን እስክነግራችሁ፣ የዛሬ ሳምንት ደህና ላግኛችሁ፣ እያለ በጥዑም ዜማ ከአጃቢዎቹ ጋር ሲያቀርብ ልዩ ነበር፡፡ ከታወቁት የባህል ሙዚቀኞች አንዱና በሕይወት የሌለው አሰፋ አባተ ዘፈን “ሸጊዬ ሸጊቱ” ከታዳሚው ጋር እየተቀባባለ አዚሞታል፡፡

“ሸግዬ ሸግዬ ሸግዬ ሸጊቱ
ድንገት ሳላስበው መጣች ከማጀቱ
ዓሳ አበላሻለሁ ዓባይ ዳር ነው ቤቴ
ዶሮ መረቅማ ተወዴት አባቴ”

እዚህ መጥቶ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ማጥናት ለፈረንጅ በጣም ይከብዳል፡፡ እርሱ ግን ገብቶት እዚህ ደረሰ ያለው የማሲንቆ አስተማሪው ጌታ መሳይ አበበ አማርኛን አጥንቶ ዓለምን ዞሯል፡፡ ፊት ሳስተምረው ከመጀመሪያ ሚስተር ቻርልስ እንዴት ነው ስለው በመሰንቆ መምቻው ራሱ እየመታ ይህ ራሱ ደብደብ ነው ይል እንደነበር ትዝታውን አውግተዋል፡፡  

የክራር መቺውና ዋሽንት ነፊው መላኩ ገላውም የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ትውስታቸውን ሲገልፁ፣ ይህ ፈረንጅ እንዴት ማሲንቆ ይማራል? እያልን እናሾፍ ነበር፡፡ ቻርልስ ባህላችን ማሲንቆአችንን ብቻ ሳይሆን እንጀራችንን፣ ዳቦአችንን፣ ቆሏችንን፣ ቂጣችንን፣ በርበሬያችንን ለሁሉም የባህል ምግባችን አክብሮት አለው ብለዋል፡፡

በዋሽንቱ ዮሐንስ አፈወርቅም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቤተኪነጥበባት ወቴአትር ሥር የነበረው ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በገንዘብ ምክንያት ከዩኒቨርሲቲው እንዲባረር ሲደረግ ቻርልስ ከወደቀበት እንዲነሳ በማድረግ በ1961 ዓ.ም በአሜሪካ አድናቆት ያተረፉትን የባህል ጉዞ ሊፈጥር እንደቻለ ገልጿል፡፡

“ዘ ብሉ ናይል ግሩፕ” ረየዓባይ ልጆችሪ በሚል በ1961 ዓ.ም የተቀረጸው ሸክላ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ቤተ መንግሥት ሄደው ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መጠየቃቸውን ያስታወሰው ባለዋሽንቱ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ንጉሡ የቻርልስን ንግግሩንና አማርኛውን አዳምጠው ሳቅ ብለው “ፈቅደናል” ማለታቸውና በንግግሩ ቅልጥፍና ተመስጠው ይስቁ እንደነበር አስረድቷል፡፡ አያይዞም ለውጥ በመምጣቱ መለያየቱና መራራቁ ቢመጣም ጊዜውን ጠበቆ በሁለተኛው ለውጥ ለመገናኘት እንደበቁና “ዞሮ ገጠም” አንዱ መገለጫ እንደሆነ ገልጾታል፡፡

በዓርብ ምሽት ዝግጅት ከ40 ዓመት በፊት የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በዩናይትድ ስቴት አሜሪካ ስላቀረበው ዝግጅት “በኢዲ ሱሊቫን ሾው” በቴሌቪዥን ቀርቦ የነበረውና በወቅቱ የአሜሪካ 40 ሚሊዮን ሕዝብ የተከታተለው ትርዒት ቪዲዮው በዳይሬክተሩ ተስፋዬ ለማ ጥረት ተገኝቶ ለእይታ በቅቷል፡፡

በቪዲዮው መክፈቻ ላይ ጎልቶ ይሰማ የነበረው የቻርልስ
“እስቲ ተመልከቱ መሰንቆ ጨዋታ  
ቃሉ ቃልን ወልዶ ስሜት የሚነካ” ሲሆን፣ የተለያዩ የባህል ሙዚቃ መሣሪያዎች ክራር፣ ማሲንቆ፣ ዋሽንት፣ እምቢልታና መለከት ድምጽ የታጀበ ዳንኪራ ቀርቦበታል፡፡ ቻርልስ ሳተን አዲስ በተለቀቀው ሲዲው የውስጥ ሽፋን ላይ በአማርኛ ያስቀመጠው የእጅ ጽሑፍ አለ፡፡ ከፊሉ እንዲህ ይነበባል፡፡

“ትምህርቴን በዩኒቨርሲቲ ለመጨረስ በተቃረብኩበት ወቅት ነበር ከአሜሪካ የሰላም ጓድ ድርጅት ፣ተቀብለንሃል፣  የሚል ቴሌግራም የደረሰኝ፡፡ በቴሌግራሙ መሠረት የተደለደልኩበት አገር ኢትዮጵያ እንደሆነ እና የምላከውም ደግሞ . . . የሚሰጠውን ስልጠና ካገባደድሁኝ በኋላ እንደሚሆን ነበር የተረዳሁት፡፡ . . .  በሥልጠናው ወቅት ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና መልክዓ ምድር በሚገባ ከተማርኩና ከተረዳሁ በኋላ አገሪቷን ገና በዓይኔ ሳላያት በፍቅርዋ ወደቅኩኝ፡፡ በተለይም በሙዚቃዋ እጅግ ልቤ ተማረከ፡፡ በዚያን ጊዜ ከሙዚቃዋ አድናቂነት አልፌ፣ ተርፌ መሰንቆ አንግቼ ከዝነኛው የባህል ሙዚቃ ጓድ ከኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ጋር በመድረክ ተሰልፌ እጫወታለሁ የሚል ሐሳብ በሕልሜም በውኔም አልነበረም፡፡”
 
< Prev   Next >