| ጤና |
|
|
| Wednesday, 07 May 2008 | |
|
በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ መስጠት የተጀመረው በአፄ ልብነ ድንግል ዘመን ከፖርቱጊዝ የዲፕሎማቲክ ሚሲዮን ጋር አብሮ በመጣውና ንጉሡን ከ1512-1527 ሲያገለግል በቆየ ሐኪም አማካኝነት ነበር፡፡ እስከ አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ድረስ በተለያዩ ጊዜያት በተመሳሳይ ሁኔታ የውጭ ሀገር ሐኪሞች እየመጡ ነገሥታቱን ሲያገለግሉ እንደነበር የተገኙት የጽሑፍ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
በተቋም ደረጃ ዘመናዊ የጤና አገልግሎት መስጠት የተጀመረው በ1889 በአድዋ ጦርነት ወቅት የቆሰሉ ዘማቾችን በሕክምና ለመርዳት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የሩሲያ ቀይ መስቀል ቡድን አባላት በቀበና ወንዝ አካባቢ የሩሲያ ቀይ መስቀል ሆስፒታልን በመሠረቱበት ወቅት ነበር፡፡ በአገሪቱ የመጀመሪያው ዘመናዊ የመንግሥት የጤና ተቋም እንደሆነ የሚነገርለት የዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል የሩሲያ ቀይ መስቀል ሆስፒታል በነበረበት ቦታ ላይ በ1901 ተቋቋመ፡፡ አፄ ምኒሊክ መንግሥታቸውን በዘመናዊ ሁኔታ ለማደራጀት በነበራቸው ፍላጐት 12 ሚኒስቴር መ/ቤቶችን ሲያዋቅሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ያልሰየሙ ቢሆንም በ1901 ዓ.ም የተመሠረተውና በሊቀ መኳስ ከተማ የበላይ ኃላፊነት ይመራ የነበረው የአገር ግዛት ሚኒስቴር የሰው ጤና የመጠበቅ ኃላፊነት ተሰጥቶት እንደነበር በወቅቱ በወጣው ደንበ ቁጥር 4 ሰፍሮ ይገኛል፡፡ (ልማት በኢትዮጵያ፣ 2000) ጉባኤ ቃና ሳሙና የሚሆን ስንት ዕፅ ተቀምጦ፣ ምነው ቅይጥ ተባይ በላና መጥምጦ፡፡ * * * የጓሮ ጐመኔ አትከስሸ ጉቦ፣ አትቅጠኝ አትክሽ፣ አንቺነሽ አበሌ፣ ለለት እራት ቀንጠብ፣ የማደርግልሽ፡፡ * * * አውሬ ይበላላል፣ ለምን ትላላችሁ፣ ሰውስ ሰው መብላቱን መቼ ተወላችሁ፡፡ * * * እበት ትል እንዲወልድ፣ ዘመኑ ጅል ወልዶ፣ በቀለም ያመልካል፣ ሰው ራሱን ወዶ፡፡ (ከበደ ካሳ፣ እንዲህ ነው፣ 1957) በአእምሮ ዓይን በዐይናችን የምንመለከተውን ግዙፍ ነገር ደኅና አድርገን ብንመረምረው፣ ከጥሩው ብዙ መጥፎ፣ ከመጥፎውም ደግሞ ብዙ ጥሩ ነገር ልናገኝበት እንችላለን፡፡ እስቲ መጥፎ ነበር ብለን የምንገምተውን የዱሮን ሰው ሁኔታ እናስታውስ፡፡ የአቶምን ጉልበት ወይም ጐጂነቱን፣ የጄትን ድምፅ ወይም ፈጣንነቱን መረዳት ቀርቶ፣ የገዛ በጉን ፀጉር ምናልባት ለማቅ ከሚያገለግለው በስተቀር ባረጀ ጨርቅ ጠቅለል አድርጎ ለጐድኑ ጉዝጓዝ እንደሚጠቅመው እንኳ የማያውቀውን የዱሮውን ገበሬ በአእምሮ ዓይናችን እስቲ እንመልከተው፡፡ የዚህ ገበሬ የኑሮ ሁኔታ የሚያስደንቀው ምንድነው? የዕለት ጉርሱን ካገኘ ተደስቶ መኖሩን፣ ሀብት ለማከማቸት አንጐሉ እስኪበጠበጥ ድረስ አለመጨነቁን፣ የጐረቤቱን የቀንድና የጋማ ከብት ብዛት ዐይቶ በመቅናት የጨጓራ በሽታ የልብ ድካም አለመሸመቱን፣ ባቋራጭ ለመክበር በመመኘት የብሔራዊ ሎቶሪን መግዣ ለመለመን ወይም ለመስረቅ አለመሄዱን ስናስብ እንገረማለን፡፡ ገበሬው ሥራውን በደንብ ያውቃል፣ ያከብራልም፡፡ የዕድሉን ዳር ድንበር፣ የኑሮውን ንድፍ አስቀድሞ የተረዳው ይመስላል፡፡ የአእምሮው ሰላም ለአካሉ ጤና ይሰጠዋል፡፡ (ነጋሽ ገብሬ፣ ሕያው ድምፆች፣ 1993) ወሬ (ወርኅየ) በሁለት የሚተረጐም ዐማርኛና ኅብር ንግግር፡፡ የኔወር ማለት ነው፡፡ ሴቲቱ ባሏን ቂጥኝ ይዞኻል አሉ ብትለው ወሬ ነው አላት፡፡ እሷ ቂጥኙ በወጣባት ጊዜ ምነው እንደዚህ አድርገኸ አታለልከኝ አለችው፡፡ እሱም ወሬ ነው ብዬሽ አልነበረምን አላት ይላሉ፡፡ (ግጥም) አፌ አልተናገረ በዦሮዬ አልሰማኹ፤ እንዲያው ታሰርኩና በወሬ ተፈታኹ፡፡ ምንጃር ምረቴ የሰው ስም ባጡ ምኒልክ ዘመን በምንጃር የነበረ አልቃሽ ዐይነ ስውር፡ ባውዳመት ቀን ሰው የሰጠውን ዳቦ ሌቦች በበሉበት ጊዜ ሰዎች እከሌ ቤት ብታስቀምጠው አይሰረቅም ነበር ቢሉት የገጠመው (ግጥም) "ከመከራ ኋላ ምክር መገኘቱ፣ ዳቦዬ ተበላ አበላሉ ከንቱ፡፡" ዳር አገር ሰው ሞተና በበቅሎ ላይ ምዋል ተደረገ፡፡ ምንጃር ውሎ ሲዋል፣ "ወይ እነ ምንጃሮች ብልጥ እናንተ ብቻ፣ እኛ ዐጣነውና ባዶውን ኮርቻ፡፡" በምንጃር ኹለት ሐርበኞች ነበሩና አንዱ ሌላውን በሴት ምክንያት ገድሎት ቢጠፋ ጊዜ "አገሩ ባዶ ነው ያም ኺዶ ያም ሞቶ፣ የፈለጉት ነገር እቤታቸው ሞልቶ" አለ ይባላል፡፡ (ደስታ ተክለወልድ፣ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፣ 1962) ሦስት ጥያቄዎች ስለ ትምህርት የሚናገር ሰው ሁሉ ሦስት ጥያቄዎችን ለመመለስ አስቀድሞ መዘጋጀት አለበት፡፡ ያለዚያ ነገሩ ፍሬ ቢስ እንደሚሆንበት ያስፈራዋል፡፡ እነዚህ ሦስት መሠረታውያን ጥያቄዎች የሚቀጥሉት ናቸው፡፡ ምን፤ ለምን፤ እንዴት፤ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በመካከላቸው ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ ትምህርት ሲባል ምንድር ነው፤ ለምን ወይስ ምን ዓላማ ማገልገል ይገባዋል፡፡ እዚህ ሁለት ጥያቄዎች ሰው ምን መሆን እንደሚገባው እንመራመር ዘንድ ስለሚያሳስቡን በቀጥታ ወደ ሥነ ምግባር ፍልስፍና ሠፈር ይመሩናል፡፡ ስለዚህ የትምህርትን ባሕርየና ዓላማ በትክክል አይቶ ለመወሰን በፍልስፍና ሲስተሞች ውስጥ ገብቶ ማሰብ ግድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ነገሩን እንደምንበድለው አያጠራጥርም፡፡ (እጓለ ገብረዮሐንስ፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ 1956) ደስታ "... የደስታ ምንጭ የምትሞላውና ሳታቋርጥ የምትፈሰው ከውስጣችን በሚፈልቁ ብሩህ አስተሳሰቦችና ስሜቶች ነው....".ይህን ነጥብ ዛሬውኑ በለጋነታችሁ ዘመን ልብ በሉት፡፡ ዘለቄታ ያለው ደስታን ለማግኘት ከፈለጋችሁ አዕምሮዋችሁን በብሩህ አስተሳሰቦች አበልጽጉ፤ ምክንያቱም ባዶ ጭንቅላት ጨለማ የዋጠውና በቀላሉ የሚፈራርስ ቀፎ ነው፡፡ ባዶ ጭንቅላት ከደስታ ይልቅ ፈንጠዚያ ላይ ያተኩራል፡፡...." "ገና ከጠዋቱ ብሩህ አስተሳሰቦችን ማሰላሰል ከያዝን በዕድሜ እየገፋን ስንሔድ ደስታችንም እየመጠቀ ይሄዳል፡፡ ሕይወትን በሥርዓት መምራት ማማ እንደመውጣት ይቆጠራል፡፡ ከማማው አጋማሽ ላይ ስንደርስ እይታችን ከቀድሞው ሰፋ ይላል፤ አሻቅበን በተጓዝን መጠንም የምናየው የበለጠ እየጠራና እየሰፋ ይመጣል፡፡ "ይህ ነው የትምህርት ዋነኛ መሠረቱ፡፡ የበሰለ ትምህርት ስብዕናን ያዳብራል፡፡ አዕምሮን ያበለጽጋል፡፡ ደስታንም ያጐናጽፋል፡፡". ለእርጅና ዘመናችን መድኅን ለደከመ ጉልበታችን አለኝታ የሚሆነንና ከአውሬነት ባሕርይ የሚያላቅቀን ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ በወጣትነት ዘመኑ ዕውቀትን የሚያካብትና ጥበብን የሚካን ሰው ሕሊናውን አዳብሮ ግድግዳዎቹ በተዋበ ሥዕሎች ባሸበረቁ የአዕምሮ ጓዳ ውስጥ ለመኖር በመቻሉ ዕድለኛ ነው"""" የሚል ነበር ትምህርቱ፡፡ (መንግሥቱ ወ/ማርያም፣ ብልጭታ፣ 1982) እኔና እሷ በልብ ስር ምሽግ በጦርነት ሜዳ፣ አመሏን ሳልመዝን ሀይሏን ሳልረዳ፣ ፍቅሯን ተፋልሜ ልጥላት ገጥሜ፣ አለምሁ ተንበርክኬ ተኮሰች ተኝት፣ ምኗን እንደሁ ሳትሀ ምኔ እንደሁ ተመታ ማረከችኝ ስቃ እጄን ሰጠሁ በቃ፤ ግን ድሏም አልቆዬ ሽንፈቴም አልጠና፣ ሴትነቷ ለዬ ወንድነቴ ቀና፣ ተጣጣን በጠባይ ተታታውን በደህና፣ እኔም እኔ ሆኜ እሷም እሷ ሆና"" (ጌትነት እንየው፣ 1994) ገራገር የሶስት ዓመቷ ሕፃን መኪና ስታሽከረክር ተያዘች በቡልጋሪያ አንዲት የሦስት ዓመት ሕፃን በተጨናነቀ የገበያ ቦታ የአባቷን መኪና ስታሽከረክር መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ አባቷ የመኪናውን ቁልፍ ረስቶ የገበያ መደብር ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ሕፃኗ ግማሽ ማይል የሚሆን ርቀት ማሽከርከሯ ተጠቁሟል፡፡ ሕፃኗ መኪናውን ስታሽከረክር የአክስቷ ልጆች የሆኑ የአራትና የስድስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው የአክስቷ ልጆች እንደነበሩ ታውቋል፡፡ መኪናው ከግማሽ ማይል ርቀት በኋላ በአካባቢው ካለ አንድ ወንዝ አቅራቢያ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ውስጥ ተቀርቅሮ የቆመ ሲሆን ጉዳት አለመድረሱ ፖሊስ ገልጿል፡፡ በዘጠኝ መቀስ ፀጉር መቁረጥ ዳይሞና በተሰኘች የእስራኤል በረሃማ ከተማ ውስጥ በአንድ የውበት ሳሎን ዳኒ ገርጊል የተባለ እስራኤላዊ የአንዲት ሴትን ፀጉር በአንድ ጊዜ በዘጠኝ መቀሶች ቆረጠ፡፡ በአሥር መቀሶች በአንድ ጊዜ ፀጉር ለመቁረጥ የተያዘውን የዓለም ሪኮርድ ለመስበር በዝግጅት ላይ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ "በአስር መቀስ ፀጉር በመቁረጥ የተያዘውን የዓለም ሪኮርድ በመስበር እስራኤል የነፃነት ስልሳኛ ዓመት ክብረ በዓል መታሰቢያ ማድረግ እፈልጋለሁ" ብሏል ዳኒ፡፡ የ92 ዓመቷ አሮጊት ተራራ ወረዱ የ92 ዓመቷ አይነ ስውር አሮጊት በገመድ ታግዘው ተራራ በመውረድ የዓለም በእድሜ ትልቅ ተራራ ወራጅ በመሆን የዓለም ሪኮርድ ሰበሩ፡፡ ኢቭ ሞብ የተሰኙት እኒሁ አሮጊት ተራራውን ለመውረድ ወደተዘጋጀው ቦታ ከወጡ በኋላ ትርኢታቸውን እንዳሳዩ አርግስ የተሰኘ ጋዜጣ አስታውቋል፡፡ በገመድ በመታገዝ ተራራውን ወርደው ከጨረሱ በኋላ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ "መገመት ከምችለው በላይ በጣም አስደሳች ነበር፡፡ ትርኢቱን እንደገና ልፈፅመው እችላለሁ" ብለዋል፡፡ ሚስስ ሞከ አንድ ዓይናቸው በጣም በትንሹ የሚያይ ሲሆን የሪኮርድ ትርኢቱን ያሳዩት ዌስት ሱሴክስ ለተሰኘ የዓይነ ስውራን ማኅበር የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አንዱ አካል መሆኑ ታውቋል፡፡ በግላኮማ በሽታ አይናቸውን ያጡት አሮጊት (ከአስር ዓመት በፊት የዲግሪ ትምህርታቸው ተከታትለው ተመርቀዋል፡፡ ድልድይ ላይ የነዱ ተቀጡ የመንገድ ርዝመትን ለመቀነስ ታስቦ በቻይና በተገነባው የዓለማችን ትልቁ ባህር አቋራጭ በሆነው ድልድይ ሹፌሮች እየተዝናኑ በማሽከርከራቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሹፌሮች መቀጣታቸው ተገለፀ፡፡ የቻይና የወደብ ከተማ በሆነችው ኒግቦና ሸንጋይ ከተማ መካከል የ4 ሰዓት የጉዞ ርቀት ወደ ሁለት ሰዓት ከ30 ደቂቃ ዝቅ ለማድረግ ታቅዶ መገንባቱ ተመልክቷል፡፡ ድልድዩ ለትራፊክ ክፍት ከሆነ የስድስት ቀናት እድሜ ቢኖረውም 300 አሽከርካሪዎች ከተፈቀደው ፍጥነት በታች በማሽከርከር ተቀጥተዋል፡፡ አሽከርካሪዎቹ ባሕሩን በመመልከት፣ ፎቶ በማንሳት ጊዜያቸውን እንደሚያጠፉ በአካባቢው የሚገኝ የዜና ወኪል አስታውቋል፡፡ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ አሽከርካሪ ለዜና ወኪሉ ሲገልፅ "ባሕሩ ይማርካል፡፡ በውበቱ በመማረኬ እየተዝናናሁ በማሽከርከሬ ልቀጣ አይገባኝም" ብሏል፡፡ |
| Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |