Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow "በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የእስከዛሬ...
"በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የእስከዛሬ... Print E-mail
Wednesday, 07 May 2008
Image"በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የእስከዛሬ መዳከም ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን"
አቶ ሚሊዮን በላይ፣ የመልካ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር

አቶ ሚሊዮን በላይ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ የተማሩት በአዲስ አበባ ነው፡፡ በባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬንት በቱሪዝም ኤንድ ኮንሰርቬሽን ተቀብለዋል፡፡

ኢንቫይሮመንታል ኤጅኩዌሽን ኢንተር ጄኔሬሽናል ለርኒንግ የፒኤችዲ ትምህርታቸውን እያጠኑ ነው፡፡ የመልካ ማኅበር ዋና ዳይሬክተርና የአፍሪካ ባዮ ዳይቨርሲቲ ኔትወርክ አስተባባሪ ናቸው፡፡ ብርሃነ ዓለሙ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ መልካ ማኅበር ምን ሠራ?

አቶ ሚሊዮን፡-
የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ይህን ያህል ተኪዶበታል ማለት ይከብዳል፡፡ እኛና ከእኛ ጋር ያሉ አሥራ ሦስት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እየተንቀሳቀስንበት ነው፡፡ መልካ በቀጥታም ባይሆን በተለያዩ አጀንዳዎች፣ በተለያዩ ቦታዎች፣ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ምንም ዓይነት ፕሮጀክት ከመካሄዱ በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እንዲደረግ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን አሰራሩ በጣም እየተዳከመ ሲመጣና አገራችንም ወደ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየገባች ስትመጣ፣ ኢንቨስትመንት ሲስፋፋ የሚጎዳው አካባቢን ነው፡፡ አካባቢ ምንም ሳይጎዳ ኢንቨስትመንት ይካሄድ ማለት ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ጉዳቱ እየበዛ ሲሄድ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ጀመርን፡፡ አንደኛ በደቡብ ክልል በሚገኝ ሸካ በሚባል ቦታ ሦስት ቦታዎች ላይ እንሠራለን፡፡ እዚያ አካባቢ የሚካሄዱ የሻይ ቅጠልና የቡና ኢንቨስትመንቶች አሉ፡፡ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት ትክክለኛ ኢንቨስትመንት ነው? እዚያ አካባቢ ያለው ብዝሐ ሕይወት ምንድነው? ባሕሉስ? ኢንቨስትመንቱ በብዝሐ ሕይወቱና በባሕሉ ላይ ያመጣው ተፅዕኖ ምንድነው? ሸካ አካባቢ ያለውን ጫካ መንጥረህ ሻይ ቅጠል ብታለማበት ነው የሚሻለው ወይስ እንዳለ ብትተወው? በሚል አስጠንተናል፡፡ ሸካ አካባቢ ያካሄድነው ጥናት እንደሚነግረን ከሆነ ሌሎች ተጨማሪ ጥቅሞችን ሳታስገባ ጫካው እዚያ ቦታ ላይ ቢኖር ያለው የብዝሐ ሕይወት፣ የቱሪዝም፣ ቅጠሎች ለመድሃኒትነት መዋላቸው፣ በአየር ለውጥ አማካይነት ዛፎች ካርቦን ስለሚወስዱ፣ የአየር መዛባት እንዳይመጣ ለማድረግ፣ አፈር እንዳይሸረሸር የሚያደርገውን ጥቅም ሳታስገባ ወደፊት የሚሰጠው ዋጋ አለ፡፡ አሁን የአንድ ጫካ ያለው ዋጋና ይህንኑ ጫካ ከ30 ዓመት በኋላ ያለው ዋጋ ይለያያል፡፡ የተለያዩ ጥቅሞችን ሳናስገባ ቀጥተኛው ጥቅም ብቻ ወስደን ብናነፃፅር ጫካው በግሬደር ተነስቶ ሻይ ቅጠል ተተክሎ አድጎ ሲሸጥ የሚያወጣው ገንዘብና ለዚያ አካባቢ ነዋሪ ለሣር፣ ለማገዶ፣ ለቤት መሥሪያ፣ ለቅመማ ቅመም የሚሰጠው ጥቅም ስናወዳድር ጫካው እንዳለ ቢሆን የሚገኘው ገንዘብ ይበልጣል፡፡ ብዙዎችን ጥቅሞች ሳትጨምር ውሱን የሆኑትን ብቻ ብታነፃፅር የጫካው መኖር የበለጠ ይጠቅማል፡፡ ይህንን ሁሉ አጥንተን ጫካው እንዳለ ቢሆን ይሻላል የሚለውን አገኘን፡፡ ነገር ግን አሁንም ኢንቨስትመንት ይካሄዳል፡፡ ኢንቨስትመንት እንዲካሄድ በዞን በወረዳ ደረጃ ያሉ የኢንቨስትመንት ቢሮዎችና የመንግሥት አካላት በከፍተኛ ተፅዕኖ ሥር ነው ያሉት፡፡   

ሪፖርተር፡- ተፅዕኖው ከየት ነው የሚመጣው?

አቶ ሚሊዮን፡-
ተፅዕኖው ከክልል፣ ከፌዴራል መንግሥት ሊመጣ ይችላል፡፡ ተፅዕኖው ጫካውን ለማጥፋት ተብሎ የመጣም አይደለም፡፡ ለዕድገት የመጓጓት ተፅዕኖ ነው፡፡ ቶሎ ምርት አምርተን ጂዲፒአችንን የማሳደግ ጉጉት ነው፡፡ ጉጉቱ ከአካባቢ አንፃር ስታየው ግን አደገኛ ነው፡፡ በማንኛውም መንገድ ዕድገት ይምጣ ከሚል ግፊት የተነሳ ጫካው እየተመነጠረ ነው፡፡ በዚህ ጉጉትና በአካባቢ መካከል ተፅዕኖውን ለመቆጣጠር ያለን መሣሪያ ሕገ መንግሥቱና የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሕግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ማንኛውም ሰው በመረጠው ንፁህ አካባቢ የመኖር መብት አለው ይላል፡፡ ሰዎች የማደግ መብት አላቸው ይላል፡፡ እነሱ የፈቀዱት ዕድገት ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የተሳትፎ መብት ይሰጣል፡፡ የባሕል መብት ይጠብቃል፡፡ ከዚህም አልፎ የራስን ዕድል በራስ እስከመወሰን መብት ይሰጣል፡፡ ማንኛውም ዓይነት ኢንቨስትመንት በሚካሄድበት ጊዜ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ መካሄድ አለበት ይላል፡፡ እዚያ ውስጥ በሕገ መንግሥቱ ያለው የተሳትፎ መብትም ተካቶበታል፡፡

የአካባቢው ኅብረተሰብ የመጠየቅ መብት አለው፡፡ ግን አሁን ታች ሄደህ ስታይ ሸካን ስታይ ኅብረተሰቡ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ተጠይቆ እሺ ብሏል ወይ? ስትል ታሪኩ ሌላ ይሆናል፡፡ ቅድም እንዳልኩት በጉጉት የተደረገ እንጂ በደንብ ኅብረተሰቡን ያማከረና በደንብ የተጠና አይደለም፡፡ አሁን ደግሞ አደገኛ የባዮ ፍዩል ጥያቄ መጥቷል፡፡ ባዮ ፍዩል ከማለት አግሮ ፍዩል ማለትን ይመርጣሉ፡፡ ማገዶን አንድደህ እንጀራ ብትጋግር ባዮ ፍዩል ነው፡፡ ሰላሳ፣ አርባና አንድ መቶ ሺህ ሄክታር በጣም ትልቅ ቦታ ነው፡፡ ያ ቦታ ሲሰጥ ባዶ አይደለም፡፡ የያዛቸው በርካታ ዕፅዋት አሉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች አሉ፡፡ የባሕሉ፣ የሰዎች የመብት ጥያቄ፣ የብዝሐ ሕይወት ጥያቄ አለ፡፡ ብዙዎቹ የባዮ ፍዩል ተክሎች ውሃ በብዛት ስለሚወስዱ የውሃ ጥያቄ ይመጣል፡፡ ሞኖ ካልቸር የሚባል አለ፡፡ አንድ ዓይነት ዝርያ ለምሳሌ ጃትሮፋ ወይም ካስትሮኢይል ብትዘራ አንድ ዓይነት ዕፅዋት ነው ሰላሳ ሺህ ሄክታር ላይ የሚሆነው፡፡ ያን ያህል ዕፅዋት አጥፍተህ ማለት ነው፡፡ ይህን የሚያመጣው ተፅዕኖ ለማስወገድ ብዙ ጥናት፣ ብዙ ምክክር ያስፈልጋል፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሳይካሄድ ነው ልማት ተብሎ የሚለማው፡፡ ለዚህ ነው መልካ ማኅበር አካባቢና ባሕል ላይ የሚሠራው፡፡ አካባቢና ባሕልን ለማስታረቅ ነው የሚሞክረው፡፡

ሪፖርተር፡- አካባቢን በሚመለከት ኃላፊነት የተሰጣቸው የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና የክልል ቢሮዎች ኃላፊነታቸውን መወጣት አልቻሉም?

አቶ ሚሊዮን፡-
ወደ ተቋማት ከመሄዳችን በፊት ወደ አስተሳሰባችን ብንሄድ ይሻላል፡፡ የአገሪቷ አስተሳሰብ ምንድነው? የአገሪቱ የፖለቲካ ሥራ አስፈፃሚዎች አቅጣጫ ምንድነው? የሚለው ቀድሞ መታየት አለበት፡፡ በክልሎች ስታይ በየመሥሪያ ቤቶች ተወሽቀው ነው የሚገኙት፡፡ ኢንቨስትመንትን የሚደግፉ ቢሮዎች ተደራጅተው ይገኛሉ፡፡ ይኸ የአገሪቱና የፖለቲካ መሪዎች ፍላጎትና አስተሳሰብ አቅጣጫ ነው፡፡ ለዕድገት ማንኛውም ዓይነት ዋጋ ይከፈል የሚል ነው፡፡ አካባቢው ተጎሳቆለ፣ የኅብረተሰቡ ባህል ተነካ ወዘተ. የሚለው ሁለተኛ ጉዳይ ነው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በአደረጃጀት ደረጃ ጥርስ ያለው ድርጅት ነው ወይ? ለባለሥልጣኑ ከሚመደበው በጀት አብዛኛው ለሠራተኛ ደመወዝ የሚከፈል ነው፡፡ በአካባቢ ባለሥልጣን የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ተብሎ የተቋቋመው ዩኒት በሰው አደረጃጀት፣ በማቴሪያል፣ ድምፅ በማሰማት ብቃት በጣም የተዳከመ ነው፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሕግ እንደወጣ ከኢንቨስትመንት ቢሮ ለአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዶክመንቶች ይላኩ ነበር፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሕግ ከወጣ ከተወሰነ ዓመት በኋላ የሚጣረስ የኢንቨስትመንት ሕግ ወጣ፡፡ አንድ ኢንቨስተር የኢንቨስትመንት ፈቃድ ካገኘ በኋላ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ማካሄድ ይችላል፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሳያካሂድ ነው ፈቃዱን የሚያገኘው፡፡ ኢንቨስትመንት ቢሮ የአገሪቱን ሕጎች በሙሉ አክብሬ እሠራለሁ ብሎ ይፈርማል፡፡ ከሚያከብራቸው ሕጎች አንዱ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ነው፡፡ ኢንቬስተሩ ኢንቨስት ከማድረጉ በፊት ግምገማ ማድረግ አለበት ይላል፡፡ ነገር ግን የኢንቨስትመንት ፈቃዱ ከተሰጠው በኋላ ያ ሰውዬ ግምገማውን አካሂዶ ነው ኢንቨስትመንት የጀመረው ወይስ ሳያካሂድ ነው ብሎ የሚከታተል የለም፡፡ ከፍተኛ ክፍተት ነው ያለው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በውሃ፣ በእርሻ፣ በማዕድን፣ በአበባ ወዘተ. ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ዶክመንቶችን ማየት የሚችሉ ኤክስፐርቶች የሉትም፡፡ ፓርላማ ስንሄድ ደግሞ የተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎች ለፓርላማ ሪፖርታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አንዱ የአካባቢ ቋሚ ኮሚቴ ነው፡፡ ይህ ቋሚ ኮሚቴ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን በዚህ ዓመት ስንት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ቀረበላችሁ? ለስንቱ ፈቀዳችሁ? ለስንቱ ከለከላችሁ ብሎ ጠይቆ አያውቅም፡፡ ይኸ ራሳቸው የተቀበሉት ነው፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እንደ አንድ አባል አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ ኮሚትመንት ባለው አካል ስር ቢሆን የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንም የአካባቢ ተቆርቋሪ ይሆናል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ብዙ ነገሮችን ማስተካከልና መሥራት አለበት፡፡ ድጋፍ ማግኘት አለበት፡፡ ሕጉንም ተፈፃሚ ለማድረግ የኅብረተሰቡ ተሳትፎን ይጠይቃል፡፡ የባለድርሻዎች ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ አንዱ ባለድርሻ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የእስከ ዛሬ መዳከም ሁላችንም እኛም ተጠያቂዎች ነን፡፡ አንድ ኢንቨስተር ኢንቨስት አደርጋለሁ ብሎ መጥቶ አበላሽቶ ሲሄድ ማጋለጥ መቻል አለብን፡፡ አካባቢ ያበላሹትን በስም ጠቅሶ በመገናኛ ብዙሃን እስከማውጣት መደረስ አለበት፡፡ ጋዜጠኞችም ኢንቨስተሮችን የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ትከታተላላችሁ አላሳያችሁም፡፡

ሪፖርተር፡- የሸካን የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እንዴት ተወጣችሁት?

አቶ ሚሊዮን፡-
በሸካ አካባቢ የምናደርገው ሕዝቡን ማስተባበር ነው፡፡ ባለፈው የተሻሻለ የደን ሕግ ወጥቷል፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ሄደን የሚመለከታቸውን የፍትሕ አካላት (ዳኞችን፣ ፖሊሶችን፣ የአስተዳደር አካላትን ወዘተ". ሰብስበን ለሦስት ቀን ትምህርት ሰጥተናል፡፡ ያኔ የተነሳው በፌዴራል መንግሥት ሕግ ወጥቷል ክልሎች ላይ ግን አልወጣም፡፡ እኛም አናውቀውም የሚል ነው፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሕግ ሸካ ያለ የፍትህ አካል፣ የኢንቨስትመንት ቢሮ ያውቁታል ወይ? እነሱ ካላወቁት ተግባር ላይ እንዲውል የሚከታተለው ማነው? ኅብረተሰቡስ ያውቃል ወይ? መጠይየቅ አለበት፡፡ መንግሥታዊ ያልሆንን ድርጅቶች ወደፊት ትልቁ ድርሻችን ኅብረተሰቡ፣ የፍትህ አካላት፣ አስተዳደሩ እንዲያውቁ ማድረግ አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ኃላፊነትን ለመውሰድ ከጋዜጠኞች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከፓርላማ ወዘተ. ይለቅ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አይቀርብም ወይ? ኅብረተሰቡ ካልተቀሰቀሰ፣ ስለ ጉዳቱ ትምህርት ካልተሰጠው ካላሳዩት እንዴት ሊያውቅ ይችላል? በየዘርፉ ያሉትን ጉድለቶች ለመለየት ለጋዜጠኛውስ የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት አያስፈልግም ወይ?

አቶ ሚሊዮን፡-
በሸካ ዞን ሁለት ወረዳዎች ላይ የአስተዳደሩ አካላት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማን እንዲያውቁ እያደረግን ነው፡፡ ከቀበሌ ጀምረን የቀበሌ አስተዳደር፣ የወረዳ፣ የዞንና የክልል ካቢኔ አባላት፣ የክልልና የፌዴራል ፓርላማ ሕግ አስጠንተናል፡፡ ከማኅበረሰቡ 16 ወንድና 16 ሴት ወጣቶች፣ 5 የጎሣ መሪዎች መናገሻ ሱባ ድረስ አምጥተን ለስድስት ቀናት ሕግ አስጠንተናል፡፡ ከተመለሱ በኋላም ድጋፍ ሰጥተናቸው ወደ ኅብረተሰቡ እየገቡ ስብሰባ እየጠሩ፣ ቤት ለቤት እየዞሩ ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ ለጎሣ መሪዎች የሦስት ቀን አውደ ጥናት ሰጥተናል፡፡ ኅብረተሰቡ ውስጥ ገብተው እያስተማሩ ነው፡፡ ሸካ ሞዴል እየሆነችን ነው፡፡ ሰው ተለውጧል፡፡ እምቢ እያለ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብት ስላላቸው ምርጫ ውስጥ ገብተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባም ተበክላለች፡፡ አዲስ አበባን አልፋችሁ ሸካን ለምን መረጣችሁ?

አቶ ሚሊዮን፡-
ብዙ ምክንያቶች አሉን፡፡ አዲስ አበባ ላይ የሚሠሩ ብዙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሉ፡፡ ምን ያህል ውጤታማ ናቸው ለሚለው የራሳቸውም ችግር አለባቸው፡፡ ብዙ ወጣት ማኅበራት፣ ት/ቤቶች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት የአካባቢ ክበብ አለው፡፡ ሸካ የደን መጠን እየቀነሰ ከመጣባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ አንድ ያለን ዓይን ሸካ ነው፡፡ አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም ቢባልም እኛ በአፈር እየተጫወትን ነው፡፡ ሸካ የሄድነው አንድ ዓይን ስላለን በአፈር አንጫወት ለማለት ነው፡፡ በባሕልም ደረጃ እየተሸረሸረ ስለሆነ እሱንም ለመጠገን ነው፡፡ ብዙ የሚመለክባቸው ጫካዎችና ትልልቅ ዛፎች አሉ፡፡ ከሚቆረጡ ቢመለክባቸው ይሻላል፡፡ ውስጡ በጣም ያምራል የቱሪዝም ምንጭ ነው፡፡ ቀፎ የሚሰቀልበት ዛፍ በመብዛቱ የማር ማምረቻ ፋብሪካ ይመስላል፡፡

ሪፖርተር፡- በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የፖለቲካ አመራሩ ምን ያህል ግንዛቤ አለው?

አቶ ሚሊዮን፡-
መጀመሪያ ስንገባ ችግር ነበር፡፡ ኢንቨስትመንት ለማቆም፣ ችግር ለመፍጠር የገባን ነው የመሰላቸው፡፡ የመጀመሪያውን አውደ ጥናት ያደረግነው ለወረዳና ለዞን ካቢኔ አባላት ነው፡፡ የምናወራው ስለ አገሪቱ ሕጎች፣ ስለ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ አሁን እጅና ጓንት ሆነን በመሥራት ላይ ነን፡፡  

ሪፖርተር፡- እናንተ ሸካ አካባቢ ደርሳችኋል ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችስ?

አቶ ሚሊዮን፡-
የሸካ ደን ጥምረት የጀመርነው ለዚህ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ሁሉንም ቦታ አዳርሰናል ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ቁጥር ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ኢምንት ነው፡፡ ኬንያ ውስጥ 30 ሺህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሉ፡፡ መሠረተ ልማቱ ተሟልቷል፡፡ ሸካ ደርሶ ለመምጣት ግን አራት ቀን ያስፈልጋል፡፡ መሠረተ ልማቱ ብዙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አይስብም፡፡ በቅርቡ ከአባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር አንድ የኔዘርላንድ አማካሪ ድርጅት እዚህ ቢሮ መጥቶ ነበር፡፡ በኔዘርላንድና በሌሎች አንዳንድ መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማን ሲስተም የማጠናከር ሃሳብ አለ፡፡ ታች ድረስ ይወርዳል ብለን ተስፋ አድርገናል፡፡ ሌላው ተስፋ የኢንቫይሮንመንታል ካውንስል ተፈጥሯል፡፡ በካውንስሉ ውስጥ የክልሉ መሪዎች አሉ፡፡ በአስተባባሪነት የያዘው ባለሥልጣኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው አውደ ጥናታችሁ ላይ ተሰብስቦ አያውቅም የተባለው ካውንስል ነው?

አቶ ሚሊዮን፡
- በቅርቡ ተሰብስበዋል፡፡ ስብሰባቸው ላይ ይህንን አንስተውታል ብለን እናምናለን፡፡ የልብህን ንገረኝ ካልከኝ ግን የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ የባህል፣ የአካባቢና ሌሎች ኤክስፐርቶች አንድ ቦታ ሄደው አንድ ፕሮጀክት ኢምፕሊመንት ከተደረገ በኋላ ሊሆን የሚችለውን መገመት ይችላሉ ነው የሚለው፡፡ ግልገል ጊቤን ብንወስድ ከግድቡ በታች የሚኖሩ ብዙ ሺህ ሰዎች አሉ፡፡ ግድቡ ሲሞላ ወደ ጎን የሚተርፍ ውሃ አለ፡፡ ግድቡ ሲሠራ የሚወጣ አፈር አለ፡፡ ያ ሁሉ ከተወሰነ ዓመት በኋላ ሊኖረው የሚችለው ተፅዕኖ ይሄ ነው፣ ይህን ያህል ጉዳት ያመጣል፣ አያመጣም ብሎ መገመት ይቻላል? ሁለተኛ ከፋዩ ማን ነው? ከፋዩ ባለሃብቱ ነው፡፡ ኤክስፐርት የተባለውን ሊጠመዝዘው አይችልም ወይ? በአገራችን ያለው ትልቁ ቀውስ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አንድ እንኳ አለመኖሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሕግ ወጥቶለት ተግባራዊ ያልሆነበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ሚሊዮን፡-
የችግር ምንጭ የሆነን አስተሳሰብ ካላስተካከልክ መፍትሄ ከየትም ሊመጣ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ብቻ ካደገች የአካባቢን ነገር ቀስ ብለን እናየዋለን የሚል አስተያየት እየሰማን ነው፡፡ በቅርቡ አንድ ባለሥልጣን ለተጠየቁት ሲመልሱ አንዳንድ ወገኖች ድሃ ሆነን ሀገራችንን በኢኮኖሚ ማሳደግ ሲገባን እነርሱ ግን ውጭ ካሉ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ሆነው ነገሩ ያልገባቸው ፕሮጀክታችንን ይተቻሉ ብለው ነበር፡፡ እዚህ ጋ ነው ችግሩ፡፡ ይህንን ከፈታህ ብዙ ነገር ይስተካከላል፡፡ መንግሥት የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ይፈልጋል፡፡ ጎን ለጎን የአካባቢ ጥበቃ፣ የሰው መብት ተቆርቋሪዎች ወዘተ. የሚሉት ነገር ይኖራል፡፡ ሁልጊዜ ይኼ አለ፡፡ ዋናው ይህንን አስተሳሰብ አቻችሎ የሚሄድ የፖለቲካ አመራር እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ይኼ ዝም ብሎ የሚመጣ አይደለም፡፡ ወደፊት ከታች ጀምሮ እስከ ላይ ያሉትን አመራር አባላት ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በዋናነት አካባቢን የሚበክሉ ምንድናቸው?

አቶ ሚሊዮን፡
- ከተሞች እየተስፋፉ ነው፡፡ ከተሞች ሲስፋፉ የሚመጡ ችግሮች አሉ፡፡ ከተሞች የሚፈጥሩት ኅብረተሰብ አለ፡፡ እዚህ የሚኖረው ሸማች ሁልጊዜ ገዢ ነው፡፡ የከተማው ባህሪ ወደ ገጠሩ የገባል፡፡ ቀስ በቀስ ገጠሬውም እንደ ከተሜው ቆሻሻ ጣይ፣ በካይ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው የባዮ ፍዩል ጥያቄ ነው፡፡ ትልቅ እርሻ ላይ ብዙ የተባይ ማጥፊያ ኬሚካል ይረጫል፡፡ የአየር ብክለት ይመጣል፡፡ የውሃ ብክለት ይመጣል፡፡ ይሄ በየወንዙ እየገባ ብዙ አደጋን ያስከትላል፡፡ ባዶ የሆኑ ቦታዎች ለትላልቅ እርሻዎች እየተሰጡ ትልቅ አደጋ ነው የሚሆኑት፡፡ ምግባችን፣ አካባቢያችን ላይ፣ ኅብረተሰቡ ላይ፣ ውሃ ሃብት ላይ ተፅዕኖ ያመጣል፡፡ ምክክር፣ ስምምነት የለንም፡፡ ባለሃብቶች ለእርሻ ብለው የሚወስዱት ሄክታር ያስደነግጣል፡፡ የኅብረተሰቡ ዕወቀት እየተሸረሸረ መምጣቱም አደጋ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዘር ሃብት ይታወቃል፡፡ ብዙ ዓይነት ጤፎች፣ ማሽላዎች፣ እንስቶች ወዘተ. የሚገኝባት አገር ናት፡፡ እነዚህን ዓይነቶች ልጆች ያውቋቸዋል ወይ? የትምህርት ሥርዓታችን ይህን እንድናውቅ አያደፋፍርም፡፡ ከአባባቢያችን ጋር የተጣጣመ አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡ ለመድሃኒትነት የሚጠቀምባቸው ብዙ ዓይነት ቅጠሎች ልጆች አያውቁም፡፡ እኛም አናውቃቸውም፡፡ ከኢንቨስትመንት፣ ከከተሞች መስፋፋት ጋር የሚመጣ ችግር ነው፡፡ የሰው ቁጥር መብዛት፣ የተራሮች መሸርሸር፣ የዛፎች መቆረጥ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ባለንበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ምክንያት የሚመጣ ችግር አለ፡፡ የአየር ለውጥ ችግር አለ፡፡ ዓለምንም እኛንም እያስጨነቀ ነው፡፡ ከአገር ደህንነት ጋር የሚመጡ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡
 
< Prev   Next >