Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Thursday
Nov 20th
Home arrow Sections arrow የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን...
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን... E-mail
Friday, 11 January 2008

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአገር ወይስ ለነገር? የሕዝብ ወይስ የግለሰብ?

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአገር ወይስ ለነገር? የሕዝብ ወይስ የግለሰብ? ለኳስ ወይስ ለመካሰስ? ለግጥሚያ ወይስ ለቅሚያ? ለስፖርት ወይስ ለሃብት? የመሳሰሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ሕዝብ እየተነጋገረባቸው ነው፡፡ አስቸኳይ መፍትሄም ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡

በየትኛውም አገር በአገራችንም ጭምር አንድ መስሪያ ቤት ወይም ድርጅት ወይም ማኅበር በአጠቃላይ የሆነ ተቋም ሲቋቋም አንድ ዓላማ ለመተግበርና ከግብ ለማድረስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሲቋቋምም በኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዲያድግ ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ውድድሮች አሸናፊ ሆና እንድትወጣ ለማድረግ ነው፡፡ በተጨባጭ እየታየ ያለው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴ ግን ከዚህ ዓላማ በእጅጉ የራቀና የአገርና የህዝብ መሆኑ ቀርቶ የግለሰቦች የነገር፣ የቅሚያ፣ የተንኮል፣ የመካሰስ፣ የመጠላለፍ ፌዴሬሽን ሆኗል፡፡ የሁሉም ጎጂና አስፈላጊ ያልሆኑ ጠባዮች፣ አመለካከቶች፣ ተግባራትና ሥራዎች ፌዴሬሽን ሆኗል፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ መሆን ያቃተውመሆንን ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ፌዴሬሽኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንኳን ሊያሳድግና ወደፊት ሊያራምድ ጭራሽም ወደ ኋላ ጎታችና በታኝ ሆኗል፡፡ ለምን እንደዚህ ሆነ? መልሱ እጅግ በጣም ቀላል ነው፡፡ የግለሰቦች ስለሆነ፡፡ ፌዴሬሽኑን በኃላፊነት በመምራት ላይ ያሉት ሰዎች ስለ ግላቸው ክብር፣ ዝናና ጥቅም እንጂ ስለ አገር አያስቡም፡፡ ለእኔ የማይጠቅም ፌዴሬሽን ገደል ይግባ የሚል አመለካከት የተጫነው ፌዴሬሽን ስለሆነ ነው፡፡

የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት በዘመድ አዝማድ የተሞላ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ በቡድን በተከፋፈሉ ግለሰቦች የተወጣጠረ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ በአንድ በኩል አምባገነን በሌላ በኩል ለአምባገነን የሚሰግዱ ኃላፊነት በማይሰማቸው፣ ግለሰቦች የተሞላ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ውስጥ ግትርነት መናቆር የራስ ዝና ማስቀደም እንጂ የኢትዮጵያን ክብርና ዝና የሚያዩ አይመስሉም፡፡

በተለይም መንግስት ይህ መሆኑን እየተነገረውና ..እይ.. የሚል ማስረጃ እየቀረበለት ለማየት ፍላጎት ስለሌለው፣ የፌዴሬሽኑ መሪዎች የልብ ልብ እየተሰማቸው ፌዴሬሽኑን ጭራሽ ወደ ገደል ከተውታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የፌዴሬሽኑ የበላይ አመራር አባላት በገዛ ፈቃዳቸው ሥራ እየለቀቁና ከቦርድ እየወጡ ናቸው፡፡ ሰሞኑንም ሁለት በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡ ቀስ በቀስ ፌዴሬሽን ማለት ግለሰብ እየሆነ መጥቷል፡፡ ግለሰቡ ለፌዴሬሽኑ ከሚስማማ ይልቅ ፌዴሬሽኑ ለግለሰብ እንዲስማማ ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡ በልክ የተሰፋ ጃኬት ሆኗል፡፡ ግለሰብ እንጂ ሌላ ሊለብሰው የማይችል ጃኬት ይህም የፌዴሬሽኑ የመጨረሻ የውድቀት ደረጃ ምልክት ሆኗል፡፡

የእኛ ዓላማ እንትና ከእገሌ ይሻላል ለማለት አይደለም፡፡ የቦርድ አባላትን አወዳድረን ደረጃ ለመመደብ አንፈልግም፡፡ አቶ ተክሌ አቶ እከሌን ቢተኩ ኖሮ ፌዴሬሽኑ ጠንካራ ይሆን ነበር ለማለት አንፈልግም፡፡ ለማለት የምንፈልገው ሊቀመንበሩም ሥራ አስኪያጆቹም ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም የእግር ኳስ ሥራ ካልሰሩ ሁሉም ከኃላፊነታቸው ይነሱ፡፡ ፌዴሬሽኑ አዲስ መመሪያ ይውጣለት፣ እንደገና ይዋቀር፣ ክትትልና ቁጥጥር ይደረግበት፣ ተጠሪነትና ተጠያቂነት ይኑር፣ ..ቅጥርና አሰራር..  ግልጽና ግልጽ ይሁን ነው፡፡ 

አዲስ ኃይል፣ አዲስ አመለካከት፣ አዲስ ሙያና የአገር ፍቅር ይግባበት ነው የምንለው፡፡  እንደሌለ ተቆጥሮ እንደ አዲስ ይዋቀር፣ ይስተካከል፣ ነው የምንለው፡፡ መንግሥት ልዩ ትኩረት ይስጥ ነው የምንለው፡፡

ለኳስ ይህን ያህል ትኩረት ያስፈልጋልን? ለኳስ ተብሎ ርዕሰ አንቀጽ ይፃፍ? እንዴታ..

ኳስ ክብ ነው፡፡ ቆዳ ነው፡፡ የሚፈታና የሚፈነዳ ነው፡፡ የሚተረተርም ነው፡፡ የመተርተሩ ስልት አይደለም አጀንዳው፡፡ ቁም ነገሩ ስፖርት መሆኑ ነው፡፡ ስፖርቱ ደግሞ የሰማንያ ሚሊዮን ሕዝብ አጀንዳ ነው፡፡ ፍቅር፣ መግባባት፣ ጤና፣ ብቃት የምናፈራበትና የምናይበት መድረክ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ አገራችን በዓለም ይቅርና ከአፍሪካ የእግር ኳስ ካርታም እየጠፋችና እየተፋቀች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ ሰባተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ስትወስድ ፌዴሬሽንና ክለብ የሚባል ነገር ያልነበራቸው አገሮች አሁን ኢትዮጵያን በረዥም ርቀት አልፈው ሄደው በአፍሪካና በዓለም የእግር ኳስ ውድድሮች እየተሳተፉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የለችም፡፡

በእግር ኳስ ፍቅሩና ደጋፊነቱ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲጨንቀው የአርሴናል፣ ማንችስተር ዩናይትድ፣ ቼልሲና ሊቨርፑል ደጋፊ እየሆነ ሲናደድ፣ ሲወራጭና ሲጣላ ያመሻል፡፡ የራሱን ስላጣ የሌላን ማፈላለግ ጀመረ፡፡ የራሱ ክለቦች ሊጠናከሩለት ስላልቻሉ ሌላ ጠንካራ ቡድን መደገፍ ጀመረ፡፡ በርግጥ የውጭ ክለብና ስፖርት ማድነቅና መደገፍ አለ፡፡ ወደ ውስጥ እንድናይ የሚያደርግ ስናጣ ወደ ውጭ ለማፈላለግ ተገደናል፡፡

ፌዴሬሽናችን ጥሩ ክለብ አልፈጠረም፡፡ የፈጠረልን አድካሚ የእግር ኳስ ሕግ እየጣስን ሽንፈት ሲያጋጥም ..ይደገማል.. በሚል ፌዝ የሚመራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የቀለደው ፌዴሬሽን፣ በእግር ኳስ ሕግም ቀልዶ በአገር ላይ እንዲቀለድ እያደረገ ነው፡፡   

ይህ ፌዴሬሽን በአስቸኳይ ሊፈርስና ያሉት ኃላፊዎች ወርደው ሌሎች ሊተኩ ይገባል፡፡ መንግሥት ኃላፊነት አለበት፡፡ ልማት ሲባል ስፖርትም የአእምሮና የአካል ልማትን ይፈጥራል፡፡ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያስገኛል፡፡ ጤናማ ዜጋን ይፈጥራል፡፡ ፌዴሬሽኑ የነገርና የግለሰብ ከሆነ መንግስት የእግር ኳስ ፌዴሬሽንን የአገርና የሕዝብ ያድርገው፡፡ በአስቸኳይ..

 
< Prev