Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow የኢነርጂ ዘርፉበኀይል እጥረት...
የኢነርጂ ዘርፉበኀይል እጥረት... Print E-mail
Sunday, 11 May 2008
የኢነርጂ ዘርፉ በኀይል እጥረት እና በኤክስፖርት ምኞች መካከል

በፍሬው አበበ

የበልግ ዝናብ መዘግየት፣ የሙቀት መጠን መጨመር እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎቱ ባልተጠበቀ መልኩ እያደገ መሄድን ተከትሎ በወር ለ10 ቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል የማናገኝበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የዚህ ሁኔታ መከሰት እንደ እግር እሳት የሚያቃጥላቸው የመኖራቸውን ያህል አሁንም የባሰ እንዳይመጣ የሚፀልዩ የትየለሌ ናቸው፡፡
አቶ አስፋው ዲንጋሞ የውሀ ሀብት ሚኒስትር ሰባት ያህል ግድቦቻችን በ1999 የሞሉ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም ከጥር እስከ መጋቢት 2000 ዓ.ም የበልጉ አየር መዛባት፣ ማለትም የዝናቡ መጥፋት፣ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት መጨመር፣ ወደ ምድር የሚደርሰው የፀሐይ ጨረር መጨመር ወይም የምድር ግለት መጨመር እና የፍላጎት ማደግ ለኃይል እጥረቱ በምክንያትነት ይጠቅሷቸዋል፡፡

የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ በአምና ክረምት ሞልተው የነበሩ ግድቦቻችን የኢነርጂ ፍላጎቱ እያደገ ሲመጣ ጠርሙስ ውስጥ እንዳለ ውሀ እየቀነሱ፣ እየቀነሱ መጥተው ወሳኝ የሆነ ቦታ ላይ መድረሱን ይናገራሉ፡፡

የኃይል እጥረቱ ልማታችን ያመጣው በመሆኑ የሚፈታውም በዚሁ በልማታችን መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም የሚጠቅሱት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ 3000 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ አምስት ግድቦች ግንባታ በመጣደፍ ላይ መሆኑን ነው፡፡

አቶ አስፋው እንደቆቃ ያሉ ግድቦች የመቆያ ጊዜያቸው (Life time) ማጠናቀቃቸው ያሳስባቸዋል፡፡ አንድ ግድብ ቢበዛ የመቆያ ጊዜው እስከ 50 ዓመት ይሆናል፡፡ ቆቃም ከዚህ በላይ ዕድሜ ቆጥሯል፡፡ በተጨማሪም የደለል መጠኑ ከ28 - 30 በመቶ መድረሱም ሌላው አሳሳቢ ላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የኢነርጂ ፍላጎት በኢንዱስትሪዎች፣ በአገልግሎት ሰጪ ዘርፉ፣ በቤት ውስጥ ፍጆታ በ15 በመቶ ማደጉ ለኃይል እጥረቱ መከሰት ሌላው ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን አቶ አስፋው ይናገራሉ፡፡ የበልግ አየር መዛባት ተከትሎ እስከ 10 በመቶ የነበረው ትነት መጠን 20 በመቶ ገደማ መመዝገቡም አንድ ችግር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡


የኃይል ኤክስፖርት ዕቅድ


የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት በማድረግ ከጎረቤት አገራት ጋር መገናኘት (ኢንተርኮኔክትድ) ማድረግ በኢትዮጵያ አለመጀመሩን አንድ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊ ይናገራሉ፡፡ ዩናይትድስቴትስ አሜሪካ ከካናዳ ኃይል ትወስዳለች፡፡ አሠራሩ በአውሮፓ ተለምዷል፡፡ የደቡብ አፍሪካ አገራት በኃይል ኢንተርኮኔክትድ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከጅቡቲ ጋር በመገናኘት ሲተርፋት ለመሸጥ፣ ኃይል ሲያጥራት ደግሞ መልሳ ለመግዛት የሚያስችላት ሁኔታ ይፈጥርላታል በማለት ያስረዳሉ፡፡

አቶ አለማየሁ ተገኑ ባለፈው ሐሙስ ዕለት የኢትዮጵያ ፓርላማ የኢትዮ-ሱዳን የፓወር ኢንተርኮኔክትድ አስመልክቶ የ41 ቢሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ማፅደቁን በማድነቅ ከመዘግየቱ በስተቀር ትልቅ ነገር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ሀገር “ቅድሚያ የምንሰጠው ለዜጎቻችን ነው” የሚሉት አቶ አለማየሁ ኤክስፖርት ማድረግ፣ ሲያስፈልገን መልሶ መግዛት ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

አንዳንድ ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ወገኖች የኢነርጂ ዘርፍን በተመለከተ ከኤክስፖርት ይልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የሀገር ውስጥን ፍላጎት በበቂና በአስተማማኝ መጠን መመገብ መሆን አለበት ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ አሁን ኮርፖሬሽኑ በይፋ 80 ሜጋ ዋት አካባቢ የኃይል እጥረት ገጥሞታል፡፡ የአንድ ሲሚንቶ ፋብሪካ አነስተኛ የኃይል ፍላጎት ከ20 ሜጋ ዋት በላይ በሆነበት ሁኔታ ኤክስፖርት ከምኞት ያለፈ ስለመሆኑ ጥርጣሬያቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

የኃይል ፍላጎቱ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በገጠር ኃይል ማስፋፊያ ፕሮጀክት አማካይነት በከፍተኛ መጠን እያደገ ባለበት በዚህ ወቅት በጠቅላላው 3000 ሜጋዋት ገደማ የሚያመነጩ ፕሮጀክቶችን ይዘን ኤክስፖርትን ማሰብ የሚቻል አለመሆኑንም ይገልፃሉ፡፡

አቶ ምህረት ደበበ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አልፎ አልፎ ከፈረቃ ውጪ የኃይል መቋረጥ ማጋጠሙን በማመን “ሁኔታውን ግን ኮርፖሬሽኑ የሚፈልገው አይደለም፡፡ በፍጥነት ልናስተካክለው ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡንም ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡

ለችግሩ መፈጠር እንደ ምክንያት ከጠቀሷቸው መካከል በፈረቃ ኃይል በሚሰጡበት ወቅት አንዳንድ ተቋማት ኃይል ወዳለበት በመሄድ በመጠቀም ጫና መፍጠራቸው እና የቴክኒክ ችግሮች ይገኙበታል፡፡

አቶ ምህረት በኤሌክትሪክ አጠቃቀም የባህርይ ለውጥ የግድ አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ይሰጣሉ፡፡ በየመኖሪያ ቤታችን የምንጠቀምባቸው አምፖሎች ኃይል ቆጣቢ አይደሉም፡፡ ስለሆነም ኃይል ቆጣቢ ፍሎረሰንት አምፖሎችን በመጠቀም ገንዘባችንን ከመቆጠብ ባሻገር የኃይል አቅርቦቱ ላይ ጫና እንዳይፈጠር ማገዝ እንችላለን ይላሉ፡፡ ከዓለም ባንክ በተገኘ 10 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በቅርቡ ኃይል ቆጣቢ አምፖሎችን ገዝቶ የማከፋፈል ሥራ እንደሚከናወን፣ በተለይ ከገጠር ኃይል ማስፋፊያ ተግባራት ጋር ተጣምሮ ይከናወናል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል፡፡

አቶ አለማየሁ “በአሁኑ ወቅት በየቤታችን ያሉት አምፖሎች ቴክኖሎጂ 100 ዓመት ያስቆጠረ ነው፡፡ ኃይል ቆጣቢ አምፖሎችን መጠቀም እስከ 25 በመቶ ኃይል ይቆጥባል” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ አቶ ምህረት አቅሙ ያላቸው በየቤታቸው ኃይል ቆጣቢ ፍሎረሰንት አምፖሎችን እንዲጠቀሙ መክረዋል፡፡

 
< Prev   Next >