Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow ተስፋዬ ብሩ ለቀረበባቸው ክስ መቃወሚያ አቀረቡ
ተስፋዬ ብሩ ለቀረበባቸው ክስ መቃወሚያ አቀረቡ Print E-mail
Sunday, 11 May 2008
በታምሩ ጽጌ

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተባቸው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅና 23 ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተከስስነው በተሻረና በተሰረዘ ሕግ በመሆኑ “ልንከሰስ አይገባም” በማለት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 1 ቀን 2000 ዓ.ም የክስ መቃወሚያ አቀረቡ፡፡ የቀረበው መቃወሚያ ሕጉን በሚገባ ካለማገናዘብ የመጣ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ መቃወሚያውን ውድቅ እንዲያደርግለት ዐቃቤ ሕግ ጠይቆ ለመቃወሚያው ምላሽ አቅርቧል፡፡

አቶ ተስፋዬ ብሩና የሥራ ኃላፊዎች ባቀረቡት የመቃወሚያ ነጥብ፣ ዐቃቤ ሕግ የተሻሻለውን ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ጠቅሶ ክስ ማቅረብ አይችልም፡፡ ምክንያቱም አዋጁ የተሻረ በመሆኑና ይህን አዋጅ የሚያየው ልዩ ፍርድ ቤት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 9/1980 ዓ.ም የተሰረዘ መሆኑን ባቀረቡት መቃወሚያ ገልፀዋል፡፡

ተከሳሾቹ የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ክስ በመቃወም ባቀረቡት መቃወሚያ፣ በ1996 የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ በአንቀፅ 2”ለ) “በ1974 ዓ.ም የወጣው የጊዜአዊ ወታደራዊ መንግሥት የተሻሻለው ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 214/1974” ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም ጀምሮ የተሻረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አንደኛ ተከሳሽ (አቶ ተስፋዬ ብሩ) ባቀረቡት መቃወሚያ እንደገለፁት በኮርፖሬሽኑ በኃላፊነት የቆዩት እስከ ግንቦት 21 ቀን 1998 ዓ.ም መሆኑን፣ የተከሰሱበት ድርጊት ከ1997 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ የዘለቀ በመሆኑ፣ ክሱ የቀረበው ጥር 1 ቀን 2000 ዓ.ም የወንጀል ሕጉ ተፈፃሚ ከሆነና የተሻሻለው የወ/መ/ሕ/አዋጅ ቁጥር 214/74 ከተሻረ ከ2 ዓመት ከ8 ወር በኋላ ነው፡፡

ተከሳሹ ኃላፊነታቸውን ከለቀቁ ከአንድ ዓመት ከ8 ወር በኋላ በመሆኑና የዋስ መብት የሚፈቅደው አዲሱ ሕግ እያለ የተሻረንና የዋስትና መብት የሚከለክል ሕግ ጠቅሶ ክስ ማቅረቡ (የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ) ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚጥስ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ክሱን ሰርዞ በነፃ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ ብሩ በመቃወሚያቸው እንደገለፁት ወንጀሉ ከመቼ እስከ መቼ እንደተፈፀመ፣ ተጎጂው ማንና እንዴት እንደሆነ፣ ክሱ በግልፅና በማያሻማ ሁኔታ ያልቀረበ በመሆኑ በየትኛው ሕግ መዳኘት እንዳለባቸውና ለማወቅና መልስ ለመስጠት አለመቻላቸውን ገልፀዋል፡፡

ከነበረባቸው ሃላፊነት አንጻር በእርዳታ የሚገኝ ገንዘብ እንዳይታጠፍ ተገቢ ነገር መፈፀማቸው፣ አስቸጋሪና ውስብስብ ሁኔታዎችን በማለፍ ወቅታዊ ውሳኔ መስጠታቸው የአመራር መሰረታዊ ባህሪ መሆኑን በመቃወሚያ ፅሁፋቸው ዘርዝረዋል፡፡

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ በፌዴራል አንደኛ ወንጀል ችሎት በወ/መ/ቁ 62805 ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ የመሰረተባቸው 24 ተከሳሾች በሙሉ፣ “የተከሰሥንበት ክስ ትክክል አይደለም፣ የሕግ መሰረት የለውም፣ ውድቅ ሊደረግልን ይገባል፣ በፍትሐብሄር መጠየቅ የሚገባውን የወንጀል ተጠያቂ ማድረግ በማንኛውም የሕግ ሥርዓት ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው” በማለት በዝርዝር የመቃወሚያ ነጥቦቻቸውን ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾቹ ላቀረቡት መቃወሚያ በሰጠው መልስ፣ የቀድሞው የኮርፖሬኑ ስራ አስኪያጅ (አቶ ተስፋዬ ብሩ) ከድርጅቱ የለቀቁበት ጊዜ ከተከሰሱበት ጉዳይ ጋር ሲነፃፀር ከግምት ውስጥ ሊገባ የሚችል አለመሆኑን ገልጾ፣ የተከሰሱት ኃላፊ ሆነው በሰሩበት ጊዜ በፈጸሙት ተግባር መሆኑ የሚካድ አለመሆኑን ገል”ል፡፡

ክስ የቀረበበት አዋጅ በአዲሱ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 5/1/ ላይ “በተሻረው ሕግ ወንጀል የሆነው ተግባር በአዲሱ ሕግ ወንጀል መሆኑ ከተደነገገና ወንጀሉ የተፈፀመው አዲሱ የወንጀል ሕግ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ ከሆነ፣ ክስ መቅረብ ያለበት በተሻረው/ በቀድሞ ሕግ/ መሆን እንደሚገባው በግልፅ የተደነገገ በመሆኑ፣ የተሻሻለው ልዩ የወንጀለኛው ልዩ ፍርድ ቤት ከ1980 ዓ.ም በኋላ ፈርሷል ለሚሉት የልዩ ፍርድ ቤት ስልጣን በአዋጅ ቁጥር 9/1980 አንቀፅ 32 /1/ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠ በመሆኑ የቀረቡት መቃወሚያ ነጥቦች ሕጉን በሚገባ ካለማገናዘብ የመጡ በመሆናቸው ፍርድ ቤቱ መቃወሚያውን ውድቅ እንዲያደርግለት ጠይቋል፡፡

የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ በምላሹ እንደጠቀሰው፣ ተከሳሾቹ “በግብረ አበር መከሰሳችን አግባብ አይደለም” ለሚሉት፣ የወንጀሉ ውጤት የተገኘው በእያንዳንዱ ተከሳሽ ውሳኔ ተሳትፎ በመሆኑና የወንጀሉ ክስ በተወሰኑት ተከሳሾች ላይ ተነጥሎ ቢመሰረት፣ የወንጀሉን መነሻና መድረሻ ስለማያመለክት፣ የሕጉን መንፈስ ተከትሎ በግብረ አበርነት በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ አግባብነት ያለው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የሁሉንም መቃወሚያ ውድቅ እንዲያደርግለት አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱ ወገኖች ያቀረቡትን ሰነድ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 27 ቀን 2000 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

 
< Prev   Next >