| የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት... |
|
|
| Sunday, 11 May 2008 | |
|
የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት ረቂቅን ተቃዋሚዎች ተቃወሙ
በተሾመ ንቁ ያለፈው ሐሙስ በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀረበውን የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት ረቂቅ ሕግ ላይ ተቃዋሚዎች ጠንካራ ትችት አሰሙ፡፡ ረቂቁ በኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬሱንና የመረጃ ነፃነትን የሚያጠፉ እንዲሁም የዜጎችን ተፈጥሮዎችና ሕገመንግሥታዊ መብት የሚገድብ ሲሉ ተችተዋል፡፡ በዕለቱ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ረቂቁ “የዜጎችን ሃሳብን የመግለጽና የማሰብ መብት ሙሉ በሙሉ የሚገድብና በነፃነታችን ላይ ታልሞ የመጣ በመሆኑ እንቃወመዋለን” ሲሉ አቶ ተመስገን ዘውዴ ተችተዋል፡፡ አቶ ተመስገን ረቂቁ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 የተደነገገውን የዜጎችን በነፃነት የማሰብ የመመራመር፣ የመፃፍና ሃሳብን የመግለፅ መብት የሚፃረር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አቶ ተመስገን በረቂቁ የፕሬስ ድርጅት ለማቋቋም የሚፈልግ ዜጋ የምስክር ወረቀት ለማግኘት የአክስዮን ባለድርሻ አባላት ስም ዝርዝር እንዲሁም የኩባንያው የካፒታ ምንጭ ማሳወቅ እንዳለበት የሚያስገድድ መሆኑን ጠቅሰው፤ “የዜጎችን የግል ፕሬስ ማቋቋም መብት ለመገደብ ታስቦ የተደረገ ነው” ብለዋል፡፡ ረቂቁ የፕሬስ ሥራ ውስጥ የሚሳተፍ ሰው ኢትዮጵያዊ መሆን እንዳለበት መደንገጉ ገዳቢ መሆኑን አቶ ተመስገን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ሮበርት መርዶዳ የተባሉ እውቅ የሚዲያ ኢንቬስተር በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በካናዳና በአውስትራሊያ የሚዲያ ኢንቨስትመንት እንዳላቸው በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ተመስገን ረቂቁ ኢትዮጵያ ተወልደው የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ባለሃብቶች በሚዲያ ኢንቨስትመንት እንዳይሳተፉ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በረቂቅ ሕጉ “ገና ለገና የግል ፕሬሶች ችግር ይፈጥራሉ በሚል ገዳቢና አሳሪ ሕግ መውጣት የለበትም” ሲሉ ሞግተዋል፡፡ መረጃ በማግኘት በኩል አንድ ዜጋ መረጃ ለማግኘት እስከ 30 ቀናት የሚቆይበት ሁኔታ በረቂቁ መኖሩን በመጥቀስ ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ረቂቁ ሶስተኛ ወገን መረጃ ሊገድብ የሚችልበትን ሁኔታ እንደሚፈቅድና በዚህም አሰራር አንድ የመንግሥት አካል ሌላኛውን የመንግሥት አካል መረጃ ከመስጠት የሚያግድበት አሰራር የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ “ይህ አሰራር መረጃ የማግኘት ነፃነትን ማረጋገጥ ሳይሆን ጨርሶ ማጨለም ነው” ሲሉ አቶ ተመስገን አጣጥለዋል፡፡ ረቂቅ ሕጉን የማስታወቂያና ባህል ጉዳዮች እንዲሁም የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የሕዝቦችን ተፈጥሯዊና ሕገመንግሥታዊ መብት የሚገድቡ ሕግጋትን እንዲያሻሽሉ አሳስበዋል፡፡ የኦፌዴን ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ፉፋ በበኩላቸው በረቂቅ ሕጉ አንቀፅ 6 አንድ ዋና አዘጋጅ የፈለገውን መረጃ ብቻ እንዲያወጣ የሚፈቅድ እንጅ መረጃ ስላለማውጣቱ የሚጠይቅ አለመሆኑን አውስተዋል፡፡ በተመሳሳይ አንቀፅ 39 መረጃ የሚሰጥ አካል መረጃ አልሰጥም ቢል የሚጠየቅበትን መንገድ የማያቀርብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የረቂቁ ክፍል 3ትም እንዲሁ መረጃ በአንድ አካል በጎ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ የሚሰጥና የሚከለከል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ ረቂቅ ሕጉ፤ ከፕሬሱ ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ከወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ውጭ ቅጣቶችን የሚያስቀምጥ መሆኑን አመልክተው፤ “በአንድ አገር ውስጥ ሁለት ሕግ መኖሩን ያሳያል” ሲሉ ተችተዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ ረቂቅ ሕጉ “ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ዜጎች እንዳያውቁ ለማፈን የተረቀቀ መስሎ ነው የሚታየው” ብለዋል፡፡ ኦፌዴን በሀገሪቱ ውስጥ የሚዲያ ነፃነትና የመረጃ ነፃነት ለማስፈን ከተፈለገ ከሚመለከታቸው አካላት የተቋቋመ ቦርድ በመሰየም ረቂቁ እንደገና መታየት አለበት የሚል አቋም እንዳለው አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ ሕግ ለማዘጋጀት የተፈለገበትን ምክንያት መግቢያ ላይ ሲገልፅ ሕልውናቸው ከማስታወቂያ በሚገኝ ገቢ ላይ ያልተመሰረተ በርካታ የግል ሕትመት ሚዲያ ተቋማት በስውር ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ለሚደጉሟቸው ሕገ ወጥ የአገር ውስጥና የውጭ የፋይናንስ ምንጮች ሕገወጥ አላማ ማስፈፀሚያ ሆነው መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡ በዚህም በሕገመንግሥታዊና በዴሞክራሲያዊ ተቋማትና አሰራሮች እንዲሁም በተቋማቱ መሪዎችና በተለያዩ የሕብረተሰቡ አካላት ላይ ስልታዊ የማጥላላትና የማነሳሳት ጥቃቶች ይፈፀሙ እንደነበር አውስቷል፡፡ በተጨማሪም ለፕሬስ ነፃነት ተፃራሪ የሆኑ በርካታ ሕገወጥ ጫናዎች ሲፈጠሩ እንደነበርና ለብሄራዊ ፀጥታና ደህንነት አስጊ በሆኑ ሕገወጥ የጥፋት ተግባራት ላይ እስከመሰማራት የተደረሱባቸው ሁኔታዎች እንደነበሩ ያብራራል፡፡ ረቂቅ ሕጉ በእለቱ ስብሰባ 302 ድምፅ ድጋፍና በ34 ድምፅ ተቃውሞ እንዲሁም በ3 ድመፀ ተአቅቦ ለሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለማስታወቂያና ባህል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጋራ በዝርዝር እንዲያዩት ረቂቅ አዋጅ 34/2000 ሆኖ ተመርቷል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |