Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow የኦሮሚያ ባህል ማዕከል ግንባታ...
የኦሮሚያ ባህል ማዕከል ግንባታ... Print E-mail
Sunday, 11 May 2008
የኦሮሚያ ባህል ማዕከል ግንባታ በማጠናቀቂያው ጊዜ አልተጀመረም

በተሾመ ንቁ

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተለምዶ በመከላከያ ሚኒስቴር የማገገሚያ ማዕከል በመባል የሚታወቀው ሥፍራ ላይ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው የኦሮሚያ ባህል ማዕከል ግንባታ አለመጀመሩ ታወቀ፡፡
ማዕከሉ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል በሚል ጥር 6 ቀን 1998 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ቢቀመጥም እስከ አሁን አለመጀመሩ ታውቋል፡፡ የባህል ማዕከሉን የግንባታ ወጪ ሙሉ ለሙሉ ለመሸፈን 150 ሚሊዮን ብር እርዳታ ለማድረግ ቃል ገብተው የነበሩት ሼህ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲ 5 ሚሊዮን ብር ብቻ መስጠታቸውን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ አረጋግጠዋል፡፡

በ5.7 ሔክታር ቦታ ላይ ይገነባል የተባለው ይኸው የባህል ማዕከል ግንባታው መዘግየቱን ነገር ግን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊዬ ኡመር ለሪፖርተር ጋዜጣ አስታውቀዋል፡፡

አቶ አሊዬ ግንባታው የዘገየው በቦታው ላይ ሰፍረው ለነበሩት የሰራዊት አባላትና ቤተሰቦቻቸው ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መተኪያ ቦታ ከማዘጋጀት አኳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይላሉ ኃላፊው “ግንባታው መጀመሪያ የታሰበው በአዳማ ስለነበር የአዳማውን ፕሮጀክት ወደ አዲስ አበባ ሲዛወርም ጊዜ ፈጅቷል” ብለዋል፡፡

ኃላፊው በቦታው የነበሩትን የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ሌላ ቦታ የማዛወር ሥራ እንዲሁም በቦታው ላይ የነበረውን ግንባታ የማጽዳት ሥራ እስከ ጥቅምት 1999 ዓ.ም ድረስ መዘግየቱን አስረድተዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ለአዳማ የታሰበውን የፕሮጀክቱን ዲዛይንና ዶክመንት የመለወጥ ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል፡፡ እስከ 2000 ዓ.ም መግቢያ ድረስ ቦታውን የማመቻቸት ሥራ ሲሰራ እንደነበር አቶ አሊዬ አስታውሰዋል፡፡ ከመስከረም 2000 ዓ.ም ጀምሮ የግንባታ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን በአሁኑ ሰዓት ወደ ግንባታ ለመግባት አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ መጠናቀቁንና ግንባታው በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

አቶ አሊዬ ለግንባታው 135 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ 40 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡ ቀሪው የግንባታ በጀት ከተባባሪ ወገኖች ጋር በጋራ የሚፈላለግበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

አቶ አሊዬ ሼህ መሀመድ አልአሙዲ ቃል የገቡትን 150 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በተመለከተ፤ “ሼህ አልአሙዲን ብሩን አልሰጥም አላሉም፤ ክፍያው መዘግየቱ ግን እንደተነፈገ ሊቆጠር አይገባም” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ በተለያዩ የግል ምክንያት እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቦታውን ለግንባታ ሳያዘጋጅ በመቆየቱ ምክንያት እርዳታው መዘግየቱን ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ አቶ አሊዬ፤ የክልሉ ፕሬዚዳንት ከሼሁ ጋር ግንኙነት እንደሚያደርጉና አስፈላጊው ድጋፍ ሊገኝ እንደሚችል አረጋግጠዋል፡፡

“የግንባታው መዘግየት በፍፁም ከሼህ አልአሙዲ እርዳታ ገንዘብ ጋር አይያያዝም” የሚሉ አቶ አሊዬ፤ “ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ግንባታው መለወጡና ለግንባታው በተሰጠው ቦታ ላይ የነበሩትን ቅድመ ሁኔታዎች ከማሟላት አንፃር ዘግይቷል” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ኃላፊው ለግንባታው አስፈላጊውን ገንዘብ ከተለያዩ አማራጭ ምንጮች የማፈላለግ ሂደት እየተከናወነ መሆኑንና የባህል ማዕከሉ ግንባታ የማይቀር መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
 
< Prev   Next >