| የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1.3... |
|
|
| Sunday, 11 May 2008 | |
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1.3 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አገኘበኃያል ዓለማየሁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመሠረታዊ የአሰራር የለውጥ ሂደት ባጠናቀቀበት በዘንድሮ የበጀት ዓመት በዘጠኝ ወር የሥራ ጊዜ ውስጥ ከቀረጥ በፊት 1.3 በሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፀ፡፡ የባንኩ የዘጠኝ ወር ያልተጣራ ትርፍ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ28 በመቶ ብልጫ ያስመዘገበ ሲሆን ካለፈው ዓመታዊ ያልተጣራ ትርፍም በ100 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡ የባንኩ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል በዚሁ በዘጠኝ ወራት የሥራ ጊዜ ውስጥ 15 ቢሊዮን ብር ለተለያዩ የኢኮኖሚያዊ አውታሮች ያበደረ መሆኑንም ገልጿል፡፡ ባለፈው ሙሉ ዓመት ባንኩ ለብድር ያዋለው 1ዐ ቢሊዮን ብር ብቻ ሲሆን በያዝነው የበጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ብቻ 15 ቢሊዮን ብር ማበደር መቻሉንና ይኸም በታሪኩ ከፍተኛ መጠን ካስመዘገቡት የብድር አገልግሎቶች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ ተጠቅሷል፡፡ ባንኩ በተጠቀሰው ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ያበደረው የብድር መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ56 በመቶ ብልጫ ማስመዝገቡም ታውቋል፡፡ በዚሁ ወቅትም ወደ አራት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ብድር መሰብሰብ መቻሉም ተጠቅሷል፡፡ እንደ ባንኩ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ገለፃ የባንኩ ጤነኛ ያልሆነ የብድር መጠንም ከ10 በመቶ በታች ሊወርድ ችሏል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የባንኩ ጤነኛ ያልሆነ የብድር መጠን ከ40 በመቶ በላይ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ ዜና ባንኩ በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የመሠረታዊ የአሠራር ሂደት ለውጡን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ጥረት መደረጉን የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የገለፀ ሲሆን ለሙከራ በተመረጡ ቅርንጫፎች የውስጥ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ ግብዓት የጥናት ውጤቱን “በተሳካ” ሁኔታ ሥራ ላይ ለማዋል በሚያስችል መልኩ እንዲቀዳጅ መደረጉን ጠቅሷል፡፡ በአዲስ መልክ የተዋቀሩት የባንኩ አሠራሮች የደንበኛ ሒሳብና የተረጋገጡ የክፍያ ሰነዶች እንዲሁም ተያያዥ አገልግሎቶች፣ የዓለም ዓቀፍ የንግድ አገልግሎትና የብድር አገልግሎቶች ናቸው፡፡ ባንኩ በመጪዎቹ ወራት አዲሱን አሰራር በሌሎቹ ቅርንጫፎቹ በስፋት መተግበር የሚጀምር ሲሆን በዚሁ አሰራር መሠረት አንድ ደንበኛ የሚፈልገውን ዓይነት አገልግሎት በአንድ ቦታ ማግኘት የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡ የለውጡ ውጤት የሥራ ፍሰቶችን በአዲሰ መልኩ ለመቅረፅ ከማስቻሉ ባሻገር ቅርንጫፎች ደንበኛ ተኮር አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻሉንም የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ገልጿል፡፡ በተለወጠው አሰራር ደምበኛው በአካል መገኘት የማያስፈልጋቸው ስራዎች በማዕከል የሚሠሩበት፣ የደምበኞችንና የባንኩን አገልግሎት መስጫ ጊዜና ወጪ የሚቆጥብ አሠራር (Central Processing Center/CPC) በተግባር ላይ የሚያውል መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እንደ ሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ገለፃ ይኸው አሠራር በተለይ ለውጭ አገር የባንክ አገልግሎቶችና ለብድር አገልግሎት የሥራ ሂደት ስኬት መሠረታዊና ከፍተኛ የሙያ ድጋፍ የሚሰጥና በቅርንጫፎች ላይ ያለው አላስፈላጊ ጫና የሚቀንስ ይሆናል፡፡ አዲሱ አሠራር ደምበኞች የተቀማጭ፣ የተንቀሳቃሽ፣ የሐዋላ፣ የቼክ መመንዘርና ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎቶችን በሙሉ ከአንድ ባለሙያ እንዲያገኝ ያስችላል፡፡ አዲሱ አሰራር ባንኩ ቀደም ሲል ይከተለው ከነበረው አሠራር ጋር ሲነፃፀር “እጅግ በጣም” አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ የብድር አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በለውጥ አሠራሩ በዓለም ዓቀፍ የንግድ አገልግሎት የሚጠቃለሉ የዓለም ዓቀፍ የንግድ አገልግሎቶች በውጭ ያሉ ዘመናዊ ባንኮች የሚሠሩበትን አሰራር ተከትለው በሰለጠነ የሰው ኃይልና አሠራር ደንበኛውን ማገልገል በሚችሉበት መልኩ አዲስ አሰራርን እንዲከተሉ ተደርጓል፡፡ በቀድሞው አሠራር ደንበኞች የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ከ2ዐ እስከ 45 ደቂቃ ወረፋ መጠበቅ ይገደዱ ነበር፡፡ እንዲሁም ከአንድ በላይ አገልግሎት ሲፈልጉ የተለያዩ የባንኩን ባለሙያዎች ማነጋገር የነበረባቸው ሲሆን በአዲሱ አሠራር በጥቂት ደቂቃዎች ለመስተናገድ ከመቻላቸውም በላይ የማፈልጉትን አገልግሎቶች በሙሉ በአንድ ቦታ የሚያገኙ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁን ሠዓት 4.2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያለው ሲሆን አጠቃላይ ሀብቱም 49 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኩ ቅርንጫፎች ቁጥርም በአሁን ሰዓት 199 ደርሷል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |