Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow ማስተካከያ
ማስተካከያ Print E-mail
Sunday, 11 May 2008
በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ሚያዚያ 29 ቀን 2000 ዓ.ም “ተመስገን ዘውዴ ካልተዘጉ ሒሳቦች የተገኘው ገንዘብ እንዲጣራ ጠየቁ” በሚለው ዜና ውስጥ “ቅንጅትን በመወከል” የሚለው ሐረግ ትክክል እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡
ስለሆነም ፓርቲ እስኪመሰርቱ ድረስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴና በቀድሞው ቅንጅት የተመረጡ 47 የሕዝብ ተወካዮች የፓርላማ ተጠሪ መሆናቸው ታውቆ በዚህ መልኩ እንዲስተካከል  አቶ ተመስገን ጠይቀዋል፡፡

(ከዝግጅት ክፍሉ)

ፍተሻው ተጠናክሮ ይቀጥል

ሚያዚያ 26 ቀን 2000 ሪፖርተር ጋዜጣ መጀመሪያ ገጽ ላይ “የፓርላማ አባላት በመግቢያ ፍተሻ ተማረዋል” በሚል ርዕስ የተጻፈውን ዜና አንብቤያለሁ፡፡ የፓርላማ አባላት በመግቢያ በር ላይ ላለመፈተሽ ያቀረቡት ሃሳብ አሳፋሪና መነሳት የሚገባው ጉዳይ አይደለም፡፡ የፓርላማ አባል ስለሆኑ ብቻ ከሕግና ከደንብ ውጪ ሊንቀሳቀሱ አይገባም፡፡ ፍተሻ ለጋራ ደህንነት ሲባል እንጂ አባላቱን ለማዋረድ ወይም ደረጃቸውን ዝቅ ለማድረግ አለመሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ስለሆነም በመግቢያ በር ላይ የሚደረገው ፍተሻ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

(በቀለ አበበ፣ ከሽሮሜዳ)  

አገልግሎት አሰጣጡ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል

በአዲስ አበባ አስተዳደር የክፍለ ከተሞችም ሆነ የቀበሌዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ህዝቡን እንዳማረረ ነው፡፡ ከማሟያ ምርጫውና ከርክክቡ ጋር ተያይዞ ከመጋቢት ጀምሮ ተገልጋዮች አገልግሎት ማጣታቸውን በሪፖርተር ሚያዚያ 26 ቀን 2000 ዓ.ም በወጣው ዕትም ዜና አምድ ያነበብኩ ቢሆንም፣ ቅሬታው አዲስ አይደለም፤ ሥር የሰደደ ችግር በቀበሌዎችና በክፍለ ከተሞች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አለ ባይ ነኝ፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ሞልቶላቸው ህዝቡን በአግባቡ ያስተናግዳሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ተገልጋዩም ሁሌ እንደተበሳጨ ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪዎቹም “ሰው ጤፉ” ናቸው፡፡ ተገልጋዩ በተደጋጋሚ ቢመላለስ፣ ጉዳዩ ቢፈፀም ባይፈፀም የእነሱ ችግር አይደለም፡፡ ከሥራቸው ይልቅ ለግል ጉዳያቸው ቅድሚያ የሚሰጡ፤ ነገር ግን በአገልግሎት መስጫ ዴስክ የተቀመጡ የክፍለ ከተማና ቀበሌ ሠራተኞች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በከንቲባ አርከበ ጊዜ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በአብዛኛው ተፈትተው የነበረ ቢሆንም በሽግግሩ አስተዳደር ግን አገልግሎት አሰጣጡ ቅጥ ያጣ ሆኖ ነበር የከረመው፡፡ ስልጣኑን በቀጣይ የሚረከበው የኢህአዴግ መንግሥት እነዚህ የተበላሹ አሰራሮችን ለመቀየር ሠራተኞችን ከማሰልጠንና አስገዳጅ መመሪያዎችን በማስቀመጥ ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

(ቃልአብ፣ ከሽሮሜዳ)

እስራኤል ምን አመጣት?

ጋዜጣችሁ በሚያዚያ 26 ቀን 2000 እትሙ “ተስፍሽና ገብርሽ” በተሰኘው የካርቱን ገጹ የኤርትራውን መሪ ኢሳይያስ አፈወርቂን ለመተቸት የተጠቀመበት ከእስራኤል ጋር የተዛመደ ዘይቤ ብዙም አላስደሰተኝም፡፡ እሥራኤላውያን፣ መላው ፍልስጥኤማውያንን ከሐማስ ጋር ደምሮ ማቅረብና የሕዝብ ጠላት አድርጎ መግለጽ ድምዳሜው አያስኬድም፡፡

የፋታህ ፓርቲ ተከታዮች የእስራኤልን ኅልውና የሚያውቁ ሰላማዊ ፍልስጤማውንን ያቀፉ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡

ፈገግታ የምትጭረው “ተስፍሽና ገብርሽ” እንዲህ ያለ አጋጣሚዎች እንዳይፈጠርባት ጥንቃቄ ቢደረግ እላለሁ፡፡

(እሥራኤል ያዕቆብ፣ ከጉለሌ)

መንግሥት የማያዳግም ቅጣት እንዲጥል ይረዳል

በእሁድ ሪፖርተር ጋዜጣ ሴት ገጽ ላይ በአባቷ ስለተደፈረችና በዚህም ለሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ስለተዳረገች አንዲት ታዳጊ የቀረበውን ጽሁፍ ተመልክቼዋለሁ፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በቅርብ ዘመድ ወይም በወላጅ አባቶቻቸው ስለተደፈሩ ሕፃናትና ታዳጊዎች በተደጋጋሚ እየሰማን ነው፡፡ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት አሰቃቂ ድርጊት በሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይ የማያዳግምና ለብዙዎች አስተማሪ ሊሆን የሚችል ቅጣት እንዲጥል የዚህ አይነት ጽሁፎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በዚሁ ዕለት ጋዜጣችሁ ሴት አምድ ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ኦስትሪያ ውስጥ ሴት ልጁን ለ24 ዓመታት በማገት ወሲባዊ ጥቃት ስለፈፀመ አባት የቀረበው ዜናም ተመሣሣይነት ሰላለው ጥሩ ሊባል ይችላል፡፡

(ብሌን፣ ከላፍቶ)

የምበላው ሳጣ ልጄ ጥርስ አወጣ

በአገራችን እየታየ ባለው የዋጋ ግሽበትና የምግብ እህሎች ውድነት ምክንያት ኅብረተሰቡ ማጣፊያው ካጠረው ቆይቷል፡፡ አንድ ኩንታል ጤፍ ስምንት መቶ ብር በደረሰበት በአሁኑ ወቅት ምን ያህሉ የኅብረተሰብ ክፍል በዚህ ዋጋ ገዝቶ መብላት ይችላል የሚለውን ስናስብ ራስ ምታት ያስነሳል፡፡

እንዲህ ባለው አጣብቂኝ ውስጥ እያለን በህገ ወጥ መንገድ ጤፍ ወደ ውጭ ለመላክ መሞከር ምን ያህል ጨካኝነት እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ይሄንን እንድል ያስቻለኝ ባለፈው ሳምንት ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ጤፍ ወደ አሜሪካ በህገወጥ መንገድ ሊላክ ሲል ተያዘ በሚል የተፃፈው ዜና ነው፡፡ የምንበላው አጥተን እየተራብን በህገ ወጥ መንገድ እህል ለመላክ መሞከሩ “የምበላው ሳጣ. . “. የሚያሰኝ ሆኖብኛል፡፡

ዜናው ላይ እንዳነበብኩት የተያዘው ጤፍ ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ ነው፡፡ ይህ ጤፍ ምን ያህል ድሆችን መግቦ ሊያድር እንደሚችል መገመት ህገወጦች ምን ያህል ስለ ህዝቡ ችግር እንዳልተጨነቁ  ማወቅ ይቻላል፡፡ የህገወጦችን ድርጊት በቀጣይም ለመቆጣጠር መትጋት ያስፈልጋል እላለሁ፡፡

 (ዘካሪያስ፣ ከጨርቆስ)

የሚመለከተው የመንግሥት አካል ዝምታ አልገባኝም

የብሔራዊ ባንክ በሽታ መፍትሄው ፓራሲታሞል ወይስ ቀዶ ጥገና በሚል ርዕስ እሁድ ሚያዚያ 26 ቀን 2000 ዓ.ም በሪፖርተር ጋዜጣ የወጣውን የግል አስተያየት አንብቤያለሁ፡፡ የጽሁፉ መልዕክት ትኩረቴን የሳበው ከዚህ በፊት ብሔራዊ ባንክ ባሌስትራ ወርቅ ነው እየተባለ ሲመዘበር እንደነበረ የሚወጡ ጽሁፎችን ያነበብንበት ጊዜ ሳይረሳ እንደገና የብሔራዊ ባንኩ ሠራተኞችና የባንኩ ገዥ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ባደረጉት አጠቃላይ ስብስባ ከገንቢ ጎኑ ይልቅ በአፍራሽ ውይይቶች መጠናቀቁ እጅጉን አሳዝኖኛል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በሌላ በኩል ብሔራዊ ባንክ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ዋልታና ማገር መሆኑ እየታወቀ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጉዳዩን ዳር ሆኖ ተመልካች መሆኑ ገርሞኛል፡፡

(ኑር ሑሴን፣ ከለገሐር)

አዳዲስ የመፍትሔ ሃሳቦች

የምግብና የሸቀጦች ዋጋ አሁንም እየጨመረ ስለመሆኑ በረቡዕ እትማችሁ ላይ አንብቤያለሁ፡፡ ይህ ሂደት ችግሩ ሥር እየሰደደ ከቁጥጥር ውጪ ስለመሆኑም አመላካች ስለሚሆን አዳዲስ መፍትሄዎች ያስፈልጋሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

እስካሁን ገበያውን ያረጋሉ ተብለው የተወሰዱት እርምጃዎች ሁሉ መፍትሄ እንዳላመጡ በመረዳት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈለግ ካልተደረገ ለአለመረጋጋት መንስኤ ስለሚሆን መንግሥት ከምንም በላይ ዋጋን በማረጋጋት ሥራ ጊዜውን ቢሰጥ ይመረጣል፡፡

(ጋሻው በላይ፣ ከቄራ)
 
< Prev   Next >